ባንካችን የባለአክሲዮኖች 30ኛ መደበኛ እና 17ኛ አስቸኳይ ጉባዔውን አካሄደ

ባንካችን የባለአክሲዮኖች 30ኛ መደበኛ እና 17ኛ አስቸኳይ ጉባዔውን አካሄደ

ባንካችን አቢሲንያ የባለአክሲዮኖች 30ኛ መደበኛ እና 17ኛ አስቸኳይ ጉባዔውን ዛሬ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም በዓድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሽ አካሄደ፡፡

ጉባዔውን የባንካችን የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መኮንን ማንያዘዋል በንግግር የከፈቱት ሲሆን፣ በመቀጠልም የባንካችን የ2025/26 (እ.ኤ.አ) በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ በጉባዔው ተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በሪፖርቱ መሠረት ባንካችን በበጀት ዓመቱ በሁሉም የአፈፃፀም መለኪያዎች አመርቂ ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን፣ ለአብነትም የባንካችን ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የብር 16.17 ቢሊዮን ዕድገት በማሳየት ጠቅላላ ገቢው ብር 55.24 ቢሊዮን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በሌላ በኩል ባንካችን እ.ኤ.አ በ2025/26 በጀት ዓመት ካለፈው ዓመት ክንውን የ56.91 በመቶ ከፍተኛ ጭማሪን በማስመዝገብ ብር 15.85 ቢሊዮን ያልተጣራ ትርፍ እንዳገኘም በጉባዔው ላይ ተገልጿል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የባንካችን የ2025/26 በጀት ዓመት አጠቃላይ ሃብት ብር 381.50 ቢሊዮን ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የብር 95.27 ቢሊዮን ወይም የ33.28 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በተመለከተም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 966.64 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ45.79 በመቶ ብልጫ እንዳለው ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ባንካችን በ981 ቅርንጫፎቹ እና ከ10,500 በላይ በሆኑ ሰራተኞቹ አማካኝነት ደረጃውን የጠበቀ የባንክ አገልግሎት የሰጠ ሲሆን፣ በተለይም ለዲጂታል ባንክ ከፍተኛ ትኩረት በመሰጠቱ ባንካችን በ2025/26 ካከናወነው አጠቃላይ ትራንዛክሽን 82 ከመቶ የሚሆነው በዲጂታል መንገድ የተከናወነ እንደነበር በመድረኩ ተገልጿል፡፡

በጉባዔው ማጠቃለያ ላይም ባንካችንን በቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚያገለግሉ 12 የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የተመረጡ ሲሆን፣በተጨማሪም ጉባዔው በዳይሬክተሮች ቦርድ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተወያይቶ የባንኩን የተፈረመ ካፒታል ለማሳደግ ወስኗል፡፡

Call Now Button