ባንካችን አቢሲንያ ለአመራሮች በሥነ-ምግባራዊ ውሳኔ አሰጣጥና በጥቅም ግጭት ዙሪያ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል

ባንካችን አቢሲንያ ለአመራሮች በሥነ-ምግባራዊ ውሳኔ አሰጣጥና በጥቅም ግጭት ዙሪያ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል

ባንካችን አቢሲንያ ለዋና መ/ቤት፣ ለቅርንጫፍ እንዲሁም ለዲስትሪክት አመራሮች “ሥነ-ምግባራዊ ውሳኔ አሰጣጥ እና የጥቅም ግጭትን መከላከልና ማስተዳደር” በሚል ርዕስ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
ይህ ስልጠና የባንካችን ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መምሪያ በባለሙያዎቹ ከሚሰጣቸው ስልጠናዎች በተጨማሪ፣ ከፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን እና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር በመተባበር የሚያከናውነው ስልጠና ነው።

በያዝነው የ2019 ዓ.ም. የበጀት ዓመትም ስልጠናውን በአምስት ዙር ለመስጠት ዕቅድ ተይዞ በመተግበር ላይ ይገኛል።ይህ አንድ ቀን የሚቆይ ስልጠና በዋናነት በሥነ-ምግባራዊ ውሳኔ አሰጣጥና በጥቅም ግጭት፣ የዘርፎች የጥቅም ግጭት ተጋላጭነት፣ የጥቅም ግጭት መከላከልና ማስተዳደር እንዲሁም ተያያዥ የሕግ ማዕቀፎች ላይ ያተኩራል።

በዚሁ መሠረት፣ የመጀመሪያው ዙር ስልጠና መስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም. በአያት ሪጀንሲ ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል። ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የባንካችን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ በቃሉ ዘለቀ ስልጠናውን ሲከፍቱ፣ የባንኩ አንዱ ዋና ስትራቴጂ የሰው ሀብትን በቀጣይነት በስልጠና ማብቃት መሆኑን ገልጸዋል። የባንክ አሠራርና ቴክኖሎጂ በፍጥነት በሚለዋወጡበት ወቅት፣ ስልጠናዎችም ከለውጡ ጋር መራመድ እንዳለባቸው ጠቁመው፣ ሥነ-ምግባር ግን ከሰው ባህሪ ጋር የሚቀጥልና ሁሌም ትኩረት የሚሻ መሠረታዊ እሴት መሆኑን አስረድተዋል።አቶ በቃሉ አክለውም፣ ባንኩ ከፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መምሪያን በማቋቋም በሥነ-ምግባርና በፀረ-ሙስና ስራዎች፣ በተለይም በስልጠና ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ አመራሮች ስልጠናውን በትኩረት ተከታትለው በሥራ ላይ እንዲተገብሩ አሳስበዋል። የጥቅም ግጭት መከላከልና ማስተዳደር ስራውም ከኮሚሽኑ ጋር በመተባበር በቀጣይነት እንደሚጠናከር ጠቁመዋል።

ከኮሚሽኑ የተወከሉት አቶ ኪዳነ ምህረት በበኩላቸው፣ ስልጠናው “ሥነ-ምግባራዊ ውሳኔ አሰጣጥ እና የጥቅም ግጭትን መከላከልና ማስተዳደር” ሆኖ “ትውልድ በሥነ-ምግባር፣ ተቋም በአሠራር” በሚል መሪ ቃል ከ2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለበርካታ አመራሮች ሲሰጥ መቆየቱንና አሁን ለመካከለኛ አመራሮችም መድረሱን ገልጸዋል። በተጨማሪም ባንኩ ለስልጠናው የሰጠውን ትኩረትና የዋና ሥራ አስፈጻሚው በመክፈቻው ላይ መገኘታቸውን አድንቀው ምስጋና አቅርበዋል።

ስልጠናውን እየሰጡ ያሉት ከኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ሂርጳሳ ነው።
ይህ ስልጠና በአራት ዙር በኢንተር ለግዠሪ ሆቴሎች የሚቀጥል ሲሆን፣ በስልጠናው ማጠቃለያም የስልጠናውን ውጤታማነትና ተገቢነት ላይ የሚያተኩር ግብረ-መልስ ይከናወናል።

ምንጭ፦ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መምሪያ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button