ባንካችን ኸርት ቱ ኸርት ለተሰኘ ተቋም የብር 4.5 ሚሊዮን የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

ባንካችን ኸርት ቱ ኸርት ለተሰኘ ተቋም የብር 4.5 ሚሊዮን የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

ባንካችን አቢሲንያ ኸርት ቱ ኸርት (Heart to Heart Children’s Aid) ለተሰኘ በልብ ሕመም የሚሰቃዩ ሕፃናትን በነጻ ለማሳከም ለሚተጋ ተቋም የብር 4.5 ሚሊዮን የገንዘብ ድጋፍ አደረገ፡፡

ዛሬ ጥቅምት 19 ቀን 2019 ዓ.ም በባንካችን ዋና መ/ቤት አዳራሽ በተካሄደ ሥነ-ሥርዓት ላይ የባንካችን ቺፍ ከስተመር ማኔጅመንት ኦፊሰር አቶ ደሳለኝ ይዘንጋው ድጋፉን ለኸርት ቱ ኸርት  የቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ መኮንን ሰሙ አስረክበዋል፡፡

ድጋፉ በሃገራችን የመንግሥት የጤና ተቋማት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ የልብ ሕሙማን ሕፃናት በኢትዮ-ኢስታንቡል አጠቃላይ ሆስፒታል እና ከጣሊያን ሃገር በሚመጡ የሕክምና ባለሙያዎች ነጻ የልብ ቀዶ ጥገና ለመስጠት ይቻል ዘንድ ለሕክምናው አስፈላጊ ግብዓቶች ለማሟላት የሚውል እንደሆነ ታውቋል፡፡

ኸርት ቱ ኸርት በልብ ሕመም የሚሰቃዩ ሕፃናትን በነጻ ለማሳከም ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን፣ በአሜሪካ ባከናወነው የገቢ ማሰባሰቢያ እንዲሁም በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከኢትዮ-ኢስታንቡል ሆስፒታል እና ከሌሎች የመንግሥት ሆስፒታሎች ጋር በመተባበር በአጭር ጊዜ በአጠቃላይ ለ321 ሕጻናት ነፃ የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና መስጠቱ ተገልጿል፡፡            

ባንካችን አቢሲንያ በጤናው ዘርፍ ያሉ የኅብረተሰባችንን ችግሮች ለማቃለል የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ያለ ተቋም ሲሆን፣ ለአብነትም ለዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ለኩላሊት ታካሚዎች ያደረገው የኩላሊት እጥበት ማሽን ልገሳ እና ለፓርኪንሰን ሕሙማን እየተደረገ ያለ ድጋፍ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

Call Now Button