የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ለደንበኛው ትልቅ ምቾት ቢሰጥም፣ የመረጃ እና የገንዘብ ደህንነት ጉዳይ ግን በእጅጉ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው። ምክንያቱም የኤ.ቲ.ኤምም ሆነ የሞባይል ባንክ የሚስጥር ቁጥር (PIN) ወይም የይለፍ ቃል (Password) በሌላ ሰው እጅ ከገባ፣ የደንበኛው ሂሳብ ሊጭበረበር ስለሚችል ደንበኞች የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶችን ሲጠቀሙ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። ቀጥሎ እያንዳንዱን በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን።
- ኤ.ቲ.ኤም
የሚስጥር ቁጥር (PIN) እንደ ቤት ቁልፍ ሊታሰብ የሚችል ሲሆን፣ ቁልፋችንን ለማንም ሰው እንደማንሰጥ ሁሉ የሚስጥር ቁጥራችንን ለሌላ ሰው አሳልፈን መስጠት የለብንም። ስልክ ተደውሎ የባንክ ሰራተኛ ነኝ፣ ጓደኛ ወይም ዘመድ ነኝ … ወዘተ ለሚል ሰው እንኳን በፍጹም መስጠት አይገባንም።
ከኤ.ቲ.ኤም አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ደንበኞች የሚከተሉትን ዘርዘር ያሉ ጥንቃቄዎች ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል፡-
- የሚስጥር ቁጥር(PIN) ን በካርዱ ላይ አይጻፉ
- የሚስጥር ቁጥር(PIN) ን በስልክ Contacts ውስጥ በግልጽ ስም አያስቀምጡ
- የተወለዱበትን ዓመት፣ የስልክ ቁጥር …ወዘተ ወይም በቀላሉ ሊገመት የሚችል ቁጥር እንደ የሚስጥር ቁጥር(PIN) ከመጠቀም ይቆጠቡ
- የሚስጥር ቁጥር(PIN) ሲያስገቡ ሌላ ሰው እየተመለከተዎት እንዳልሆነ ያረጋግጡ
- በኤቲኤም ላይ የሚስጥር ቁጥር(PIN) ሲያስገቡ የኪፓዱን ክፍል በእጅዎ ይሸፍኑ
- የሚስጥር ቁጥርዎን(PIN) ሌላ ሰው እንዳየብዎት ከጠረጠሩ፣ ወዲያውኑ ይቀይሩት ወይም ወደ ባንኩ ቅርንጫፍ ይሂዱ
- ኤቲኤም በቂ ብርሃን ባለበት ቦታ ይጠቀሙ!
- የኤቲኤም ማሽኑ በትክክል እንደሚሠራ ያረጋግጡ!
- በጣም የሚያጠራጥር ሁኔታ ካጋጠመዎት ሌላ ኤቲኤም ይጠቀሙ
- በኤ.ቲ.ኤም ላይ ያልተለመደ መሳሪያ ምናልባትም ካሜራ ሊሆን የሚችል አጠራጣሪ ነገር ካስተዋሉ ይራቁ
- የሚስጥር ቁጥር(PIN) በድምፅ አይናገሩ
- ካርድዎን ለማንም አይስጡ
- “እኔ ልርዳዎት” የሚል እገዛን በጥንቃቄ ይመልከቱ
1.1 የኤ.ቲ.ኤም ካርድዎ ቢጠፋ
ካርድዎ ከጠፋ ወይም ከተሰረቀ፣ በፍጥነት ለባንኩ ያሳውቁ። ይህም ያልተፈቀደ ግብይትን በመከላከል ገንዘብዎን በአጭበርባሪዎች ከመዘረፍ ያድናል።
1.2. የሚስጥር ቁጥር (PIN) ቢረሳ
የሚስጥር ቁጥር (PIN) ቢረሱ፣ በራስዎ ብዙ ጊዜ መሞከር አይመከርም። የሞባይል ባንኪንግ የሚስጥር ቁጥር (PIN) ከተረሳ ወይም ከታገደ፣ ወደ ቅርብ ቅርንጫፍ በመሄድ PIN እንዲታደስ/እንዲቀየር (reset) መጠየቅ ይችላሉ።
1.3. ኤ.ቲ.ኤም ገንዘብ ሳይሰጠን ነገር ግን ሂሳባችን ቢቀነስ
ይህ ሲከሰት፦
- ደረሰኝ ካለ ይያዙ
- የግብይት መልዕክቱን (transaction notification) ይመልከቱ
- ግብይቱ በራሱ ከተመለሰ (reversed) ትንሽ ጊዜ ይጠብቁ
- ካልተመለሰ ግን ለባንኩ ያሳውቁ
2. የሞባይል እና ኢንተርኔት ባንኪንግ
የሞባይል ባንኪንግ ሂሳብን ለማየት፣ ለመክፈል፣ ለማስተላለፍ እና ሌሎች ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ነው። ታዲያ ደንበኞች የሞባይል ባንኪንግ ሲጠቀሙ ከታች የተዘረዘሩትን የደህንነት ጥንቃቄዎች ሊያደርጉ ይገባል።
ዘርፈ–ብዙ የደህንነት ማስጠበቂያ የይለፍ–ቃል ይጠቀሙ፦ ሞባይል ስልክዎን በአሻራ፣ በፊት ገጽታ፣ ፓተርን፣ ፓስወርድ እና ፓስ ኮድ … ወዘተ በመጠቀም ስልክዎን ይቆልፉ።
ባለ ሁለት ደረጃ ማረጋገጫ ((Two-Step Verification)) ይጠቀሙ፦ የሞባይል ባንኪንግ ደህንነትን በባለ ሁለት ደረጃ ማጠናከር ይቻላል።
የሚመጣውን SMS በጥንቃቄ ያንብቡ፦ “ሂሳብዎ ታግዷል”፣ “ሽልማት አሸንፈዋል”፣ “ካርድዎ ተዘግቷል” …ወዘተ የሚሉ መልዕክቶችን በጥንቃቄ ይመልከቱ።
የተረጋገጡና ትክክለኛ የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያዎችን (application) ከአስተማማኝ ምንጮች አውርደው ይጠቀሙ፦ የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያዎች ትክክለኛ በባንኩ ዕውቅና ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ ተገቢ ነዉ፡፡
መተግበሪያዎችን ማዘመን፡– በስልክዎ ላይ የሚገኙ መተግበሪያዎችን የደህንነት ክፍተቶችን ለመድፈንና የባንክ ሂሳብዎን ደህንነት ለማስጠበቅ በየጊዜው ያዘምኗቸው፡፡
ከህዝብ መገልገያ ዋይፋይ ይልቅ የሞባይል ዳታ ይጠቀሙ፡– የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶችን ለመጠቀም ለህዝብ መገልገያ ከቀረቡ ነፃ ዋይፋዮች ይልቅ የሞባይል ዳታዎችን ይጠቀሙ፡፡ በተለይ የኢንተርኔት ባንኪንግ ሲጠቀሙ፣ በህዝብ ዋይፋይ በኩል የባንክ ሂሳብ ከማስገባት ይቆጠቡ።
የባንክ ሂሳብዎን ዘወትር ይከታተሉ፡– የአካውንትዎን ሁኔታ (Status) በየጊዜው ይከታተሉ፣ የማያውቁት የሂሳብ ለውጥ ካለም፣ በአፋጣኝ አቅራቢያዎ ወደሚገኝ ቅርንጫፍ በመሄድ ያሳውቁ፡፡
3.ከሞባይ እና ኢንተርኔት ባንኪንግ ጋር የተያያዙ የማጭበርበር ስልቶች
1.1 “ከባንክ ነኝ” የሚል ስልክ
አንድ ሰው ደውሎ “የባንክ ሰራተኛ ነኝ፤ ሂሳብዎ ችግር ገጥሞታል፤ የሚስጥር ቁጥር (PIN) /OTP ይንገሩኝ” ካለ የማጭበርበሪያ ስልት ስለሚሆን፣ መረጃውን አይስጡ።
3.2 “ሽልማት አሸንፈዋል” የሚል ሃሰተኛ ጥሪ
“እንኳን ደስ አለዎት 100,000 ብር አሸንፈዋል! OTP ይላኩልን” የሚል መልዕክትም ሊመጣ ይችላል። ይህም ማጭበርበሪያ ሊሆን ስለሚችል በፍጹም አይመኑ።
3.3 ሐሰተኛ የማጭበርበሪያ ድረ–ገጽ
አጭበርባሪዎች ከባንክ ድረ-ገጽ ጋር የሚመሳሰል ድረ-ገጽ በማዘጋጀት የሚስጥር ቁጥር (PIN) ፣ የይለፍ ቃል (Password) ወይም የአንድ ጊዜ የይለፍ ቃል (OTP) በመጠየቅ ሊያጭበረብሩ ይችላሉ።
ስለዚህ፦
- በማያውቁት ማስፈንጠሪያ (Link) አይግቡ
- የባንኩን ኦፊሴላዊ መተግበሪያ/ድረ-ገጽ በራስዎ ይክፈቱ
- የሚስጥር ቁጥር(PIN) /OTP በስልክ ለሚጠይቅ ሰው አይስጡ
- አጠራጣሪ መልዕክት ሲመጣልዎት አይመልሱ
- ተጨማሪ የደህንነት መመሪያዎች
ደንበኞች የሞባይል ወይም ኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት ሲጠቀሙ በግላቸው የሚችሉትን ያክል ጥንቃቄ ማድረግ ያለባቸው ሲሆን፣ ከታች የተዘረዘሩትን የጥንቃቄ መልዕክቶችም ልብ ሊሉ ይገባል፡-
● የባንክ ገንዘብ ዝዉዉር ማረጋገጫን አስመስለዉ የተሰሩ ሃሰተኛ የዝዉዉር ማረጋገጫ የጽሁፍ መልዕክቶች፣ ስክሪንሾት… ወዘተ በጥንቃቄ እናንብ
● ሞባይላችንን መቆለፍ፡- በተለይም ግብይቶች በምንፈፅምበት ግዜም ይሁን በማንኛውም ወቅት ስልካችንን በጠንካራ የይለፍ ቃል ወይም በባዮሜትሪክ አማራጮች መቆለፍ
● ግብይቶችን /ክፍያዎች/ ስንጨርስ የክፍያ መተግበርያዎች ዘግተን በመውጣት የይለፍ ቃላችን እነሱ ላይ ሴቭ አለመሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል
● የባንክ ሒሳቦቻችን ሁኔታ (Statements) በየግዜው መፈትሽ/መመልከት
● በባንካችን ድረ-ገፆች ላይ የተቀመጡ የደህንነት መመሪያዎችን መከተልና መተግበር
● ሞባይላችንን ላለመጠቀም ወይም ለሌላ ሰው ለመስጠት ስንወስን፣ የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያውን እና ታሪኩን ማስወገድ እና ሚስጥራዊ መረጃዎች ማጥፋት
● ስልካችንን እና የባንክ መተግበሪያዎችን ለመክፈት የተለያዩ የሚስጥር ቁጥሮችን PIN/OTP) መጠቀም
● ሀሰተኛ የክፍያ ማረጋገጫ የጽሑፍ መልዕክቶችን መጠንቀቅ፡-የሽያጭ ክፍያ በሚፈፀምበት ግዜ ገንዘቡ ወደ ባንክ ሒሳባችን በትክክል መግባቱን ወይም አለመግባቱን ወደ ባንክ ሂሳባችን በመግባት ማረጋገጥ
● ደንበኞች ግብይት/ክፍያዎች በሚፈፅሙበት ግዜ ወዲያውኑ ክፍያ/ግብይት እንደፈፀሙ የሚያሳውቅ መልዕክት ወደ ስልካቸው እንደደረሳቸው ማረጋገጥ። እነዚህ መልዕክቶች በተለያየ ምክንያት ከዘገዩ ወይም ከቀሩ፣ ወደ ባንክ አካውንታቸው በመግባት ሒሳባቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።
