bankofabyssinia.com

እራስዎን እንዴት ከአጭበርባሪዎች ይከላከላሉ?

እራስዎን እንዴት ከአጭበርባሪዎች ይከላከላሉ?

በዘመናችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እና የተጠቃሚዎቹን ቁጥር በእጅጉ በመጨመር ላይ የሚገኘው የዲጅታሉ አለም ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ለጠጠቃሚዎች የያዘ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ይህ የዲጅታል ፋይናንስ ስርዓት በአገልግሎት ሰጪዎች እና ተጠቃሚዎች በቂ እና በየጊዜው የሚተገበሩ የደህንነት ጥበቃ ቅድመ ስራዎች ካልተሰራበት እጅግ ጉልህ የሆነ ኪሳራን ሊያስከትል እንደሚችልም ብዙ ማስረጃዎች ስለመኖራቸው የሚያጠያይቅ ሀቅ አይደለም፡፡ ይህ አጭር ጽሁፍም በዲጅታሉ አለም እያደገ እና  መልኩንም ከአዳዲስ ከቴክኖሎጂ ለውጦች ጋር በመለዋወጥ የብዙዎችን  የፋይናንስ ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል ላይ ስለሚገኘው የበይነ መረብ ስርቆት (ዲጅታል ስካም) ምንነት፣ ቅድመ ጥንቃቄዎች እና የመፍትሔ ነጥቦች ላይ ዳሰሳ ያደርጋል፡፡

የበይነ መረብ ስርቆት በፋይናንስ ተቋማት

የበይነ-መረብ ማጭበርበር

ከላይ በመግቢያችን እንደተመለከትነው የተለያዩ የፋይናንስ አገልግሎቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ በበይነ-መረብ ዘዴዎች በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት መሰጠት መጀመራቸውን እና የተጠቃሚዎችም ቁጥር በእጅጉ በማሻቀብ ላይ መሆኑን ተከትሎ አጭበርባሪዎች ትኩረታቸውን በእነኚሁ የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ካደረጉ ሰንበትበት ብለዋል፡፡ በመሆኑም አጭበርባሪዎች በተጠና እንዲሁም ጊዜው የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የኢላማቸውን ግለሰባዊ ዝንባሌ ባገናዘበ አግባብ የተለያዩ የማጭበርበር ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ በአመት ብዙ ቢሊዮን ብሮችን በአለም አቀፍ ደረጃ ከተለያዩ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪዎች በዋነኛነት ደግሞ ከደንበኞቻቸው ያጭበረብራሉ፡፡ ይህን ተከትሎ እ.ኤ.አ 2022 ዓ.ም በአማሪካ ባንከርስ አሶሴሽን የተደረገው ጥናት እንደሚያመላክተው በአሜሪካ ብቻ ጥናቱ በተደረገበት ዓመት 2.2 ሚሊዮን የማጭበርበር ሪፖርቶች ሲመዘገቡ በሪፖርቶቹ ማጭበርበር ተደርጎበታል በመባል የተጠቀሰው ገንዘብ  በጥቅሉ  8.8 ቢልዮን የሜሪካን ዶላር መሆኑን ጥናቱ ያመላክታል፡፡

በአብዛኛው እንደሚስተዋለው የፋይናንስ ማጭበርበር ሰለባ ሲሆኑ የሚስተዋሉት አረጋዊያን እና ዝቅተኛ የዲጅታል ፋይናንስ ግንዛቤ ባላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ሲሆን ብጥቅሉ ሲታይ የማጭበርበር አደጋን በቅድሚያ ለመገንዘብ በሚያደግታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖን ሲያሳድር ይስተዋላል ይህንን ቅድመ ዳሰሳ በቁጥሮች በማስደገፍ ፋይናንሺያል ትራንስፓረንሲ ኮሚቴ እ.ኤ.አ በ2021 ይፋ ባደረገው ጥናት በአለም ዙሪያ በ2021 ብቻ ከ1 ቢልየን የአሜሪካን ዶላር ከነኚሁ የህብረተሰብ ክፍሎች በአጭበርባሪዎች መመዝበሩን ያትታል፡፡

ከላይ የተመለከቱት ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የፋይናንስ ማጭበርበር በአለም ዙሪያ እየተበራከተ እና መጠኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሻቀብ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በፋይናንሱ ዓለም በፍጥነት ተቀባይነትን እያገኙ የመጡት የክሪፕቶ ከረንሲ እና  የቶክን መገበያያዎች አጭበርባሪዎች ያለአግባብ ያገኙትን ገንዘብ ለማሸሽ እና ከተጠያቂነት ለመዳን የሚችሉበትን ውስብስብ የአሰራር ዘዴዎች ይዞ በመቅረቡ አሁን ላይ አጭበርባሪዎችን ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ፈታኝ አድርጎታል፡፡    

የተለመዱ የማጭበርበሪያ ዘዴዎች

በዚህ ርዕስ ስር በአጭበርባሪወዎች በተለያዩ ጊዜአት በአብዛኛው ጥቅም ላይ የሚውሉ የማጭበርበር ዘዴዎችን እንመለከታለን ይህም አንባቢያን ለሚያደርጉት የቅድመ መከላከል ስራ በወሳኝነት ሊያግዝ የሚችሉ ነጥብ ለመዳሰስ ያለመ ነው፡፡

1-  ፊሺንግ፡ ይህ በአጭበርባሪዎች በአብዛኛው እና ለረዥም ጊዜ በጥቅም በመዋል ላይ የሚገኝ ሲሆን ለስርቆት ኢላማ ለሆነው ተቀቋም ወይም ግለሰብ የተለያዩ ኢሜይል ወይም የጽሁፍ መልዕክትን ልክ ከትክክለኛ አገልግሎት ሰጪ እንደተላከ በማስመሰል የማጭበርበር ኢላማው ፍቃድ ለሌላቸው ሶስተኛ ወገኖች ሊያስተላልፍ ያልተገባውን እንደ የባንክ ሂሳብ ዝርዝር መረጃ፣የሚስጥር ቁጥር እና የመሳሰሉ ግለሰባዊ ይዘት ያላቸውን መረጃዎች እንዲያጋራ እና በማስከተልም የፋይናንስ ደህንነቱን አደጋ ላይ በመጣል ከደንበኛው ጋር በመደራደር ክፍያን መቀበል አልያም በሂሳቡ የሚገኘውን ተቀማጭ ያለ ፍቃዱ ወጪ ለማድረግ ብሎም የማንነት ስርቆት ለመፈጸም በሰፊው በአጭበርባሪዎች ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ከዚሀም ጋር ተያይዞ የስማርት ስልኮችን ሰፊ ተደራሽነት ተከትሎ የጽሁፍ መልዕክቶች በአብዛኛው የስማርት ስልክ ተጠቃሚ የሆኑ ተገልጋዮችን ማዕከል በማድረግ መልእት ከባንክ የተላከ እንደሆነ በማጭበርበር የተላከውን የጽሁፍ መልዕክት በመክፈት ኢላማው በውስጡ ያለውን ማስፈንጠሪያ (link) በሚጫንበት ወቅት ወሳኝ የተባሉ ግለሰባዊ መረጃዎቹ ለአጭበርባሪዎች ጠለፋ  የሚጋለጡበትን መንገድ የሚያመቻች የማጭበርበር ዘዴ በስፋት በስራ ላይ እየዋለ  ይገኛል፡፡

2-  የድምጽ ማጭበርበር(voice phishing): ይህ በሰፊው በሀገራችን የተለያዩ የባንክ ደንበኞችን የፋይናንስ ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን ይህ የማጭበርበር ዘዴ ከስሙ ለመረዳት እንደሚቻለው አጭበርባሪዎች የባንክ ወይም የሌላ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪን ሰራተኛ አልያም ተወካይ በመምሰል ለማጭበርበር ኢላማው ስልክ በመደወል በደንበኛው የሚተዳደረው የባንክ ሂሳብ ላይ የገጠመ የቴክኒክ ብልሽት አልያም የአሰራር ለውጥ እንዳለ በመንገር ይህ ችግር ይፈታ ዘንድ ደንበኛው በአገልግሎት ሰጪው ዘንድ ያለውን ሚስጥራዊ መረጃዎች እንዲያጋራ የሚጠይቁበት የማጭበርበር ዘዴ ነው፡፡

3-  ሀሰተኛ መጠይቆች: በሰፊው በአጭበርባሪዎች ጥቅም ላይ በማዋል ላይ የሚገኝ ዘዴ ሲሆን ለጥቃቱ ኢላማ የሆነውን ግለሰብ በመምረጥ እውነታኛ ያልሆነ ጥናት ደንበኛ በሆነበት ባንክ እየተሰራ እንደሆነ ይህም በመሰረታዊነት በኢላማው ሊመለሱ የሚገቡ መጠይቆችን እንደሚያካትት በመግለጽ የጥቃቱ ኢላማ ፍጹም ተገቢ ያልሆኑ እና በመደበኛ ጥናት መጠይቅ መዘርዝሮች ውስጥ ሊካተቱ የማይገባቸው ግለሰባዊ የፋይናንስ መረጃወች እንዲሰጥ የማታለያ መንገድ በመሆን በጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን በአብዛኛው በአጭበርባሪዎች በጥቅም ላይ በመዋል ላይ የሚገኙትን ጨምሮ ሌሎች በዚህ ርዕስ ላይ ያልተካተቱ የማጭበርበር ተግባራት የደንበኛውን የባንክ ሂሳብ ከመዝረፍ ባለፈ ዘላቂ የሆኑ እንደ የማንነተት ስርቆት፣ ዝቅተኛ የብድር አመላለስ ታሪክ፣ እና ስነ-ልቦናዊ ቀውስን በማጭበርበር ድርጊት ተጠቂው ላይ ጥለው ስለማለፋቸው ቀላል የማይባሉ ማሳያዎች ስለመኖራቸው የማይታበል ሀቅ በመሆኑ የባንካችን ደንበኞች በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚከተሉትን የጥንቃቄ እርምጃዎች በመከተል እራሳቸውን ከአጭበርባሪዎች ለመከላከል ይችላሉ፡-

እንዴት እራስዎን ይከላከሉ?

1-  ቀይ መስመሮትን ይለዩ፡ በየትኛውም ሁኔታ የመጀመሪያው እራስዎን ከአጭበርባሪዎች የሚከላከሉበት መፍትሔ የማጭበርበር ኢላማ ስለመሆኖ ጠቋሚ ነጥቦችን መለየት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የትኞቹ ጉዳዩች እንደ ቀይ መስመር ሊወሰዱ ይችላሉ የሚለውን ከዚህ እንደሚከተለው እንመልከት፡፡

ችኮላ፡ አጭበርባሪዎች አብዛኛውን ጊዜ የጥቃት ኢላማቸው በተረጋጋ መንፈስ ከእነርሱ ጋር ስለሚያደርገው የመረጃ ልውውጥ እንዳያስብ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ ይህንንም ሲያደርጉ ተጠቂውን በማዋከብ እና ችኮላ በተሞላበት ሁናቴ ነው፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት አንድ የባንክ ቤት የደነንበኞች አገልግሎት ሹም መሆኑን መግለጽ ለኢላማው የስልክ ጥሪ አልያም ኢሜይል የሚያደርግ አጭበርባሪ በአፋጣኝ ለሚጠይቀው ጥያቄ መልስ እንዲሰጠው ያለበለዚያ የደንበኛው ሂሳብ ሊታገድበት ወይም ሊዘጋ እንደሚችል ሊናገር ይችላል፡፡›

ያልተጠየቀ ግንኙነት (unsolicited contact) ፡ ባንኮች የደንበኞቻቸውን የአገልግሎት ጥራት ለማረጋገጥ በየጊዜው ሊያደርጉ የሚችሉት ግንኙነት እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ አይነቱን ግንኙነት የአጭበርባሪዎች ድርጊት የሚለየው በግንኙነቱ ጊዜ በተለምዶው ሊጠየቁ የማይገባቸውን ሚስጥራዊ የሆኑ ግላዊ ይዘት ያላቸውን መረጃዎች ኢላማው እንዲሰጥ ይጠየቃል፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት አንድ የባንክ ደንበኛ ስለ አገልግሎት ጥራት ማሻሻል በሚያትት የኢሜይል ልውውጥ ላይ ግላዊ የሆነን እንደ የሞባይል ባንኪንግ ይለፍ ቃል ያለ መረጃ ቢጠየቅ ይህንን መረጃ ቆም ብሎ ሳያስብ ከመስጠት ሊቆጠብ ይገባዋል፡፡

የወል መጠሪያዎችን መጠቀም፡ ተቋማት ከደንበኞቻቸው ለመገናኘት በሚጠቀሟቸው በተለያዩ  የግንኑነት ዘዴዎች ደንበኛውን በስሙ እና ልዩ መለያው በመጥቀስ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን በአብዛኛው ጊዜ አጭበርባሪዎች ካላቸው የመረጃ ውስንነት አንጻር ለጥቃት ኢላማ ያደረጉትን ግለሰብ በወል መጠሪያው በመጠቀም ለምሳሌ እንደ የተከበሩ ደንበኛችን በማለት ግንኙነት ሲያደርጉ ይስተዋላል ይህም ሌላኛው ቀይ መስመር ተብሎ ሊወሰድ የሚገባው ነው፡፡

2-  ወደ ባንካችን የጥሪ ማዕከል ይደውሉ፡ አቢሲንያ ባንክ የደንበኞቹን የፋይናንስ ደህነት ለማረጋገጥ ባስተዋወቃቸው የዲጅታል ፋይናንስ መተግበሪያዎች ላይ ካካተታቸው አስተማማኝ የደህንነት መጠበቂያ አሰራሮች ጎን ለጎን ደንበኛው በየትኛውም ጊዜ ጥሰት ሲፈጸምበት ወይም  ጥርጣሬ ካለው በነጻ ስልክ መስመር 8397 በመደወል ሂሳቡ ስላለበት ሁኔታ ብሎም የመጭበርበር ጥርጣሬን ለማረጋገጥ ይችላል፡፡ እንዴት? እንደሚከተለው:-

ጥርጣሬ ባደረቦት ግንኙነት የተሰጦትን ስልክ ቁጥር ወይም ሌላ የግንኙነት መስመር ከመጠቀሞ በፊት በቅድሚያ ባንካችን ባዘጋጀው የነጻ የስልክ መስመር በመደወል አልያም በባንኩ ኦፊሴሊያዊ ድህረ-ገጽ ላይ በተመለከቱ ሌሎች የግንኑነት መስመሮች በመጠቀም መረጋገጫዎችን ይጠቀሙ፡፡

ግልጽ ጥያቄዎችን ይጠይቁ፡ በባንኩ በቀረበው የነጻ ስልክ መስመር በመጠቀም ስላሎት የመጭበርበር ጥርጣሬ ግለጽ እና ፈጣን የሆነን መልስ ከተገቢው/ከሚመለከተው የባንኩ ተወካይ ስለ ሂሳቦት አሁናዊ ሁኔታ በቂ ማብራሪያ እና ምላሽን ለማግኘት ይችላሉ፡፡

አጠራጣሪ ተግባራትን ሪፖርት ያድርጉ፡ በማንኛውም አይነት የግንኙነት ዘዴ የመጭበርበር ኢላማ እንደሆኑ ከተጠራጠሩ  ባንኩ ባዘጋጀው የነጻ ስልክ መስመር በመደወል ጥቆማዎትን ይስጡ፡፡ ይህም ሊወስዱ የሚገባዎትን የደህንነት ጥንቃቄ እርምጃዎች ብሎም በሂሳቦት ላይ ስላሉ ያልተለመዱ እንቅስቃሴዎች በባንኩ ቁጥጥር እንዲደረግ ትልቅ እገዛን ያደርጋል፡፡

ተጨማሪ የቅድመ መከላከል እርምጃዎች፡ ከላይ በዋነኛነት ከተዳሰሰው ማጭበርበርን የመከላከያ መንገድ ጎን ለጎን ደንበኞች ከዚህ የሚከተሉትን ሌሎች አማራጮች ሊከተሉ ይችላሉ፡-

ጠንካራ የይለፍ ቃል ይጠቀሙ፡ ደንበኛው በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ እና ተገማች የሆኑ እንደ ልደት ቀን የስልክ ቁጥር እና ሙሉ ስም የመሳሰሉ ይለፍ ቃሎችን ከመጠቀም ይልቅ የፊደላት፣ ምልክቶች እና የቁጥሮች ድብልቅ የሆኑ ጠንካራ እና በቀላሉ በአጭበርባሪዎች ሊገመቱ የማይችሉ የይለፍ ቃሎችን በመጠቀም ራሱን ከአጭበርባሪዎች ለመታደግ ይችላል፡፡

ተደራራቢ የደህንነት ማንቂያን ይጠቀሙ፡ ይህም ሲባል ደንበኛው በሚጠቀመው አገልግሎት ላይ ቀድሞ ከሚጠቀመው የደህንነት ማንቂያ ለምሳሌ የይለፍ ቃል ይጠቀሙ ከነበር በዚሁ የደህንነት ማንቂያ ላይ ተደራቢ ለመሆን የሚችል ሌላ የደህነንነት መቆጣጠሪያን ይጠቀሙ፡፡ ይህም የዲጅታል እንቅስቃሴዎን ከአጭበርባሪዎች ለመከላከል ተጨማሪ ዘዴን ለመቀየስ ያስችሎታል፡፡

በየጊዜው ሂሳቦት ስላለበት ሁኔታ ይከታተሉ፡ ከባንካችን የሚደርሶትን የሂሳብ መግለጫ እና የዲጅታል ባንኪንግ መተግበሪያዎች ላይ ያሎትን እንቅስቃሴ በቋሚነት ይከታተሉ ይህን ማድረጎ በሂሳቦት ላይ የሚስተዋሉ ያልተለመዱ የሂሳብ ልውውጦችን በቀላሉ ለመገንዘብ እና የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያስችሎታል፡፡

የግል መመረጃዎን በጥንቃቄ ያጋሩ፡ በኢሜይል ወይም በሌላ ማነንኛውም  የግንኙነት ዘዴ ካልታወቁ ግለሰቦች አልያም ተቋማት የሚቀርቡሎትን ግለሰባዊ ጥያቄዎች ከመመለስ ይቆጠቡ፤ የተለያዩ ካልተረጋገጡ መነሻዎች የሚላኩ መስፈንጠሪያዎችንም ከመጫን ራሶን ይገድቡ፡፡ በዚህ አግባብ ምንግዜም ከማን ጋር የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ላይ እንዳሉ በትኩረት በማሰብ ያልተገቡ ግለሰባዊ ይዘት ያላቸውን መረጃዎች ለሶስተኛ ወገኖች ከማጋራት ወይም እንዲጋሩ በር ከመክፈት ራስዎንይቆጥቡ

ደህነታቸው በተጠበቁ ኔትዎርኮች ይጠቀሙ፡ የሞባይል አልያም ኢንተርኔት ባንኪንግ በሚጠቀሙበት ጊዜ ለአጭበርባሪዎች  ኢላማነት በቀላሉ ከሚጋለጡ የጋራ ኔትዎርኮች እና ቪፒ.ኤን ከመጠቀም ይልቅ የግል ኔትዎርኮችን ይጠቀሙ።

የጸረ ቫይረስ መተግበሪያዎች መታደሳቸውን ያረጋግጡ ይህም በአጭበርባሪዎች በጥቅም ላይ ሊውሉ ከሚችሉ የደህንነት ጥሰት ተጋላጭነትን ሊጨምሩ ከሚችሉ እንደ ማልዌር እና ቫይረሶች ራስዎንለመመከላከል ሁነኛ መፍትሔ ነው፡፡

በየጊዜው ራስዎንበእውቀት ያበልጽጉ፡ በየጊዜው የሚወጡ መረጃወችን እና የአገልግሎት አሰጣጥን የተመለከቱ ጉዳዩችን በተመለከተ ያሉ ጉዳዮን በንቃት ይከታተሉ፡፡

የመፍትሔ ነጥቦች

በአጭበርባሪዎች ስለመታላለዎ እርግጠኛ ከሆኑ እና በባንካችን ስላሎት ሂሳብ ደህንነት አደጋ ላይ ከወደቀ የሚከተሉትን የመፍትሄ እርምጃዎች በመከተል በመጭበርበር የሚደርስቦትን አሉታዊ ጫና ለማስቀረት ወይም በእጅጉ ለመቀነስ  ይችላሉ፡፡

ወዲያውኑ ከባንካችን ጋር ግንነኙነት ይፍጠሩ በሂሳቦት ላይ ያስተዋሉት እንግዳ ነገር አልያም ለማጭበርበር መጋለጦትን ካረጋገጡ ወዲያውኑ ለባንካችን በማሳወቅ በሂሳቦ ላይ የሚከወኑ ከእርሶ ፍቃድ ውጭ ያሉ ክንውኖች እንዲቋረጡ ማድረግ  ይችላሉ፡፡

እንደ ይለፍ ቃል እና የመሳሰሉትን ከባንክ ሂሳቦት ጋር በቀጥታ ግብኙነት ባላቸው መገልገያዎች ላይ የሚጠቀሙባቸውን የደህንነት መጠበቂያዎችን የጥቃት ኢላማ መሆንዎን ከተገነዘቡበት ወይም በቂ ጥርጣሬ ካደረቦት ወዲያውኑ ይቀይሩ ፡፡

የመጭበርበር ማንቂያ (fraud alerts) የመጠቀም ባህሎን ያዳብሩ ይህም ከእርሶ ሂሳብ ጋር በተገናኘ ቅርብ ቁርኝት ያላቸው አገልግሎት ሰጪዎች ከየትኛውም ግንኙነት ጅማሬ በፊት ተገቢውን የማንነት ፍተሻ በማድረግ ከተገቢው ግለሰብ ጋር ግንኙነት ውስጥ እንዳሉ በማረጋገጥ ደንበኛው ከማንነት ስርቆት እና የዚሁ ድርጊት ተከታይ ከሆኑ የተለያዩ አሉታዊ ተጽእኖዎች እራሱን ለመከላከል ይችላል ፡፡

በህግ ስልጣን ለተሰጣቸው አካላት ያሳውቁ፡ የማጭበርበር ሰለባ ከሆኑ የኮምፒውተር ወንጀጀልን ለመደንገግ በ2008 ዓ.ም በወጣው አዋጅ መሰረት መሰል የማጭበርበር ጉዳዮችን ለመከታተል እና ለፍትሕ ለማቅረብ ስልጣን ለተሰጣቸው የኢንፎርሜሽን  መረብ ደህንነት መስሪያ ቤት እና ሌሎች የፍትህ ተቋማት ስለ ጉዳዩ በፍጥነት ያሳውቁ፡፡

ማጠቃለያ፡

አጭበርባሪዎች በየጊዜው ቴክኖሎጂው የደረሰበትን ደረጃ በመከተል የተለያዩ የማጭበርበሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም  የተራቀቁ እና ለእውነትነት የቀረቡ በሚመስሉ መደለያዎች የብዙዎችን የፋይናንስ ደህንነት አደጋ ላይ መጣላቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሆኖም ደንበኞች እራሳቸውን በየጊዜው መልኩን ከሚቀያይረው የአጭርባሪዎች ወጥመድ ራሳቸውን ለመከላከል ይችሉ ዘንድ እራሳቸውን በተገቢው መረጃ በማዘመን ተገቢውን ጥረት ስለማድረጋቸው ዘወትር ማሰብ ይገባቸዋል፡፡

በተጨማሪም በየትኛውም ጊዜ የሚያጋጥሟቸውን አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ለባንካችን የነጻ የስልክ መስመር ብሎም ሌሎች ኦፊሲያላዊ የግንኙነት መስመሮችን በመጠቀም ማሳወቅ ለነገ የማይባል ሌላው መሰረታዊ ነጥብ ነው፡፡ በጥቅሉ ከላይ የተመለከቱትን የደህንነት ቅድመ ጥንቃቄዎች እና የእርማት እርምጃዎችን በመከተል ወሳኝ የሆነውን የፋይናንስ ደህንነቶን ይጠብቁ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button