ባንካችን አቢሲንያ በአዲስ አበባ ሰሚት አካባቢ የሚገኘውን ቅርንጫፉን በታዋቂው የእግር ኳስ ተጫዋችና ኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ ስም ቅዳሜ ህዳር 6 ቀን 2018 ዓ.ም በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ሰየመ።
ባንካችንን በመወከል በዝግጅቱላይ የተገኙት የከስተመር አካውንትስ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ አየለ ገብሬ እንደተናገሩት ባንካችን አቢሲንያ በተለያዩ መስኮች አሻራቸውን ያሳረፉ ባለውለታዎችን ለማስታወስና ስማቸው ዛሬም ዳግም ከፍ ብሎ እንዲነሳ ቅርንጫፎቹን በባለውለታዎቻችን ስም በመሰየም የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል።
የመንግስቱ ወርቁ ዳግም የታሪክ ትንሳዔ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሰለሞን በቀለ ዱባለ በበኩላቸው ባንካችን ኢንስትራክተርመንግስቱ ወርቁ ለሃገር የከፈለውን ዋጋ ከግምት አስገብቶ ስሙ ዳግም ከፍ እንዲል በማድረጉ የተሰማቸውን ልባዊ ደስታና አድናቆት ገልጸዋል። ታዋቂው የእግር ኳስ አሰልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻውም ባንኩ ለስፖርቱ ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት በማድነቅ ባንኩን አመስግነዋል።
ኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ ሃገራት ባደረጋቸው ግጥሚያዎች ለአኩሪ ድል ያበቃ ከመሆኑም በላይ ብሔራዊ ቡድኑን በማሰልጠንም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ ይታወቃል።
ሁሌም ቅርንጫፎቹን ለሃገር ውለታ በዋሉ ታላላቅ ሰዎች በመሰየም የሚታወቀው ባንካችን ዛሬም በታላቁ የስፖርት ሰው መንግስቱ ወርቁ ስም ቅርንጫፉን በመሰየሙ ታላቅ ክብርና ደስታ ይሰማዋል።
በምርቃቱ ሥነ-ሥርዓት ላይም የባንካችን የስራ ሃላፊዎች፣ ታዋቂው የእግር ኳስ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋችና አሰልጣኝ ንጉሴ ገብሬ፣ ታዋቂ የስፖርት ጋዜጠኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።










Leave a Reply