bankofabyssinia.com

ባንካችን አቢሲንያ የባለአክሲዮኖች 29ኛ መደበኛ እና 16ኛ አስቸኳይ ጉባዔውን አካሄደ

ባንካችን አቢሲንያ የባለአክሲዮኖች 29ኛ መደበኛ እና 16ኛ አስቸኳይ ጉባዔውን አካሄደ

ባንካችን አቢሲንያ የባለአክሲዮኖች 29ኛ መደበኛ እና 16ኛ አስቸኳይ ጉባዔውን ትናንት መስከረም 20 ቀን 2018 ዓ.ም በአድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሽ አካሄደ፡፡

ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መኮንን ማንያዘዋል የባንኩን እ.ኤ.አ የ2024/25 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በበጀት ዓመቱም በአብዛኛው የአፈፃፀም መለኪያዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ለተሰብሳቢዎቹ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው ገለጻ ባሳለፍነው የበጀት ዓመት የባንካችን ጠቅላላ ገቢ ብር 39.07 ቢሊዮን ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የብር 11.32 ቢሊዮን ዕድገት አሳይቷል፡፡

ባንካችን እ.ኤ.አ በ2024/25 በጀት ዓመት ካለፈው ዓመት የ91.38 በመቶ ከፍተኛ ጭማሪን በማስመዝገብ ብር 10.10 ቢሊዮን ያልተጣራ ትርፍ እንዳገኘም በጉባዔው ላይ ተገልጿል፡፡

አቶ መኮንን አክለውም እ.ኤ.አ በ2024/25 በጀት ዓመት ባንካችን እንደ ቀደሙት ዓመታት ሁሉ የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገቱን አስጠብቆ የዘለቀ ሲሆን አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑንም ከብር 192.51 ቢሊዮን ወደ ብር 243.18 ቢሊዮን ማድረስ ችሏል፡፡

እንደ ቦርድ ሰብሳቢው ገለጻ የባንካችን እ.ኤ.አ የ2024/25 በጀት ዓመት አጠቃላይ ሃብት ብር 286.23 ቢሊዮን ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት አጠቃላይ ሃብት ጋር ሲነጻጸር የብር 63.92 ቢሊዮን ወይም የ28.76 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በተመለከተም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 663.02 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተገኘ ሲሆን ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር የ56.37 በመቶ ብልጫ እንዳለው አቶ መኮንን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ባንካችን በመላ ሃገራችን በሚገኙ 928 በሚደርሱ ቅርንጫፎቹ፣ 11,065 በሚጠጉ ታታሪ ሰራተኞቹና እንዲሁም በከፍተኛ ቁጥር ባደጉት የዲጂታል ባንክ ቴክኖሎጂ አማራጮቹ በመታገዝ ለደንበኞቹ ደረጃውን የጠበቀ የባንክ አገልግሎት እንደሰጠ በጉባዔው ላይ ተብራርቷል ፡፡

በመጨረሻም የቦርድ ሰብሳቢው ባንኩ ዘመኑን የዋጀ የዲጂታል ቴክኖሎጂን ስራ ላይ በማዋሉ አገልግሎቱን ከማዘመኑም በተጨማሪ የሰራተኛውን የምርታማነት ምጣኔ ማሳደጉን አጽንኦት ሰጥተው በመግለጽ ንግግራቸውን አጠቃልለዋል፡፡

በጉባዔው ማጠቃለያም ባንኩ አጠቃላይ ካፒታሉን ማሳደግ እንዲችል በሙሉ ድምጽ የተወሰነ ሲሆን በተጨማሪም የዲጂታላይዜሽን ስራዎችን በማጠናከርና አዳዲስ አገልግሎቶችን በመጨመር ለደንበኞቹ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁነቱን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button