bankofabyssinia.com

የደንበኞች የዲጂታል ፋይናንስ ግላዊ መረጃዎች እንዴት ይጠበቃሉ?

የደንበኞች የዲጂታል ፋይናንስ ግላዊ መረጃዎች እንዴት ይጠበቃሉ?

ለተለያዩ አገልግሎቶች ረጃጅምና አሰልቺ የይለፍ ቃላትን ለማስታወስ መሞከር ባስ ሲልም ረስቶ መንገላታት የብዙዎቻችን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ግን እየዘመነ በመጣው የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት አዳዲስ፣ ለአጠቃቀም ምቹ የሆኑ የፋይናንስ ደህንነት ስርዓቶችን በማካተት እነዚህን ችግሮች መቅረፍ ተችሏል፡፡
ይህም ፋይናንስንና ቴክኖሎጂን አጣምረው በመስራት ላይ ያሉ እንደ ባንክ፣ ፊንቴክ ኩባንያዎችና ሌሎች መሰል ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት ጎን ለጎን በየጊዜው መልካቸውን በመቀያየር የብዙዎችን የፋይናንስ ደህንነት አደጋ ላይ እየጣሉ የሚገኙትን የተለያዩ የበይነ-መረብ አደጋዎችን ለመቆጣጠር ብሎም የሚያደርሱትን አደጋ መጠን ለመቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባር ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡
ይህ አጭር ጽሁፍም ከቀደሙት ጊዜያት አንስቶ በፋይናንስ ዘርፍ ባሉ የዲጂታል አገልግሎቶች ላይ ምን ምን ዓይነት የደህንነት መቆጣጠሪያ መንገዶች በመተግበር ላይ እንዳሉና በዚሁ ዘርፍ በአቢሲንያ ባንክ የተዋወቀው አዲሱ የአፖሎ መተግበሪያ ምን አይነት ገጽታ እንዳለው ይዳስሳል፡፡

የፋይናንስ ደህንነት ድሮና ዘንድሮ 
የፋይናንስ ዓለም ራሱን ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር ማዛመድ የጀመረው በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ሲሆን ይህም በአብዛኛው በፋይናንስ ዘርፉ ያሉ ተቋማት የበይነ-መረብ የባንክ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ የተጀመረ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የመጀመሪያዎቹ የበይነ-መረብ የባንክ አገልግሎቶች በስራ ላይ ያዋሏቸው የደህንነት መከላከያ ዘይቤዎች መሰረታዊ የሆኑትን እንደ የይለፍ ቃል (Password) እና በአብዛኛው ጥቅም ላይ የሚውለው ማመስጠር (Encription) የነበረ ሲሆን በጊዜው እንደ ጥሩ ቴክኖሎጂያዊ እመርታ የታዩ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ለብዙ የበይነ መረብ አደጋ ተጋላጭነታቸው ግልጽ እየሆነ የሄደና እ.ኤ.አ በ2000ዎቹ የመጀመሪያ አመታት ቀላል የማይባል የደህንነት አደጋን በምዕራቡ አለም ባሉ ሀገራት አስከትሎ አልፏል ፡፡ ይህም በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት፣ ህግ አውጪዎች እንዲሁም ተጠቃሚዎች አዲስና ደህንነነቱ የተረጋገጠ ስርዓት እንዲፈልጉ ትልቁን አስተዋጽኦ እንዳበረከተ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
ዲጂታል ባንኪንግ ለብዙሃኑ በተዋወቀባቸው የመጀመሪያዎቹ አመታት በተጠቃሚዎች ዘንድ የነበረው ትልቁ ጥያቄ የዲጂታል ባንኪንግ ለደንበኞቹ ቀልጣፋና ምቹ አሰራርን ቢያስተዋውቅም፣ በሌላ በኩል ደንበኞች  ደህነንታቸው በበቂ ሁኔታ ባለመጠበቁ  ብዙዎች አዲሱን የፋይናንስ አሰራር በመቀላቀል ረገድ ትልቅ ክፍተት ነበር፡፡ ሆኖም ባለፉት 10 አመታት በአለም ዙሪያ የተመዘገበው ፈጣን የበይነ-መረብ ግብይት  ዕድገት ብዙዎችን ወደ አዲሱ የዲጂታል ባንኪንግ አለም ከመቀላቀሉም በላይ አስተማማኝ የደህንነት መጠበቂያ ስርዓት አስፈላጊነትና ትግበራን ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ አድርጎታል፡፡

መሰረታዊ የደህንነት መጠበቂያ ስርዓቶች
በዚህ ርዕስ ስር  በአለም አቀፍ ደረጃ ባሉ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪዎች ዘንድ መሰረታዊ የሚባሉትና በአዲሱ የአፖሎ መተግበሪያ ላይ የተካከቱትን እንደ የፊት ገጽታን ማረጋገጫ ያለውንና በሃገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ አቢሲንያ ባንክ በስራ ላይ ያዋለውን የባዮሜትሪክ የደህንነት መጠበቂያ ስርዓት ጨምሮ ሌሎች የደህንነት መጠበቂያ ገጽታዎች በአጭሩ የሚዳሰሱ ይሆናል፡፡
 

1. ማመስጠር (Encription)
በጊዜ ሂደት የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ሰጪዎች በሚሰጧቸው አገልግሎቶች ላይ በደንበኞቻቸው የግል መረጃዎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመከላከል በማሰብ መረጃን የማመስጠር ወይንም የኢንክሪፕሽን ስራዎችን እንደ ቀዳሚ የደንበኞች መረጃ ደህንነት መጠበቂያ መንገድ ተግባር ላይ ሲያውሉ ይስተዋላል፡፡ በመሆኑም አዲሱ የአፖሎ መተግበሪያ ላይ የመረጃ ማመስጠር ስራ የሚሰራው ደንበኞች በመተግበሪያው ላይ ያላቸውን ዝርዝርና የፋይናንስ ደህንነታቸውን አደጋ ላይ የሚጥሉ መረጃዎችን ለመጠቀም ወይንም ለመፍታት ፍቃድ ለሌላቸው ሶስተኛ ወገኖች  በቀላሉ በማይፈታ መንገድ ማቀናበርን የሚመለከት ተግባር  ሲሆን አፖሎ በዚህ ረገድ አለም የደረሰበትን የማመስጠር/ኢንክሪፕሽን ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ያዋለ በመሆኑ ደንበኞች ግላዊ መረጃዎቻቸው በተገቢው መንገድ ይጠበቃሉ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

2. ተደራራቢ/ተከታታይ ማረጋገጫዎች (Multifactor Authentication)
የፋይናንስ ተቋማት በሚሰጧቸው የበይነ መረብ አገልግሎቶች ላይ የሚስተዋሉ የደህንነት ጥያቄዎችና ተደጋጋሚ ጥሰቶችን ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን በአግባቡ መፍትሄ ለማበጀት በማሰብ አዲሱ የአፖሎ መተግበሪያ ተደራራቢ/ተከታታይ ማረጋጫዎች የደህንነት መጠበቂያ መንገዶችን ተግባር ላይ አውሏል፡፡ ተደራራቢ/ተከታታይ ማረጋገጫዎች (Multifactor Authentication) ከስማቸው ለመረዳት እንደሚቻለው የአገልግሎት ተጠቃሚው የተለያዩ የደህነነት መጠበቂያ እርከኖችን በማለፍ ወደሚፈልገው አገልግሎት እንዲያመራ የሚያደርግ ስርዓት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የአፖሎ ሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ለመጠቀም በምዝገባ ላይ የሚገኝ ግለሰብ ይህንን በሚያደርግበት ወቅት እንደ የይለፍ ቃልና የማረጋገጫ የጽሁፍ መልዕክት ጉዳዩን በሚከውንበት የተለያዩ ደረጃዎች ቢጠየቅ፣ ይህን እንደ ተደራራቢ/ተከታታይ ማረጋገጫ ልንወስደው እንችላለን፡፡

3.    ሰው ሰራሽ አስተውሎት
ይህ ዓይነቱ የደህንነት መጠበቂያ አሰራር በዘርፉ ባሉ ተቋማት በጥቅም ላይ  መዋል  የጀመረው በጣም በቅርቡ ሲሆን ይህም ለረጅም ጊዜ ሲሰራባቸው የቆዩትን የማመስጠርና ተደራራቢ/ተከታታይ ማረጋገጫዎችን የመጠቀም አሰራር በእጅጉ በማሻሻል በዘርፉ በአብዛኛው ሲነሱ የነበሩ የደንበኞች የደህንነት ጥያቄዎችን በሚገባ የሚፈታ አሰራርን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ በዚህም ረገድ አዲሱ የአፖሎ መተግበሪያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ በመተግበሪያው ላይ የሚሰበሰበውን ጥልቅ የመረጃ ማህደር ፈጣን በሆነ አግባብ የሚታዩበትን አጠራጣሪና ህገ ወጥ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን በመለየት መፍትሄ ለመስጠትና የደንበኞቹን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ ያስቻለ አሰራርን ተግባራዊ አድረጓል፡፡ ለምሳሌ አንድ  በበይነ-መረብ በመታገዝ አዲስ አበባ ውስጥ ግብይት የፈጸመ ተጠቃሚ በፍጥነት ሞያሌ ከሚገኝ ተቋም ገንዘቡን ለማውጣት ቢሞክር፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚታገዘው የደህንነት መጠበቂያ ስርዓት እንደ አጠራጣሪ ድርጊት በመለየት ተጨማሪ ማጣራት እንዲከናወን የማድረግ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡
 

4.  የባዮሜትሪክ መለኪያዎች
አዳዲስ የሳይንስ ግኝቶችን ተከትሎ በፋይናንስ ደህነት ጥበቃ ስራዎች ላይ በአሁኑ ወቅት ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር በአንድነት በተግባር ላይ በመዋል ላይ የሚገኙት ቀዳሚ መሳሪያዎች የባዮሜትሪክ መለኪያዎች ሲሆኑ እነርሱም በዋነኛነት ከሰው ሰው  ልዩ የሆኑትን የተፈጥሮ ገጽታዎች ለምሳሌ የጣት አሻራ፣ የፊት ገጽታና የድምጽ  ማንነትን ለማረጋገጥ በጥቅም ላይ ያዋሉ ናቸው፡፡ እራሱን ከአዳዲስ አሰራሮች ጋር እያዘመነ የደንበኞቹ ተቀዳሚ ምርጫ የሆነው አፖሎም ይህን የደህንነት መጠበቂያ በስራ ላይ ያዋለ ሲሆን ደንበኞች ከመመዝገባቸው በፊት ልዩ የሆኑትን ግላዊ መረጃዎቻቸውን ማለትም የፊት ገጽታቸውን በሚጠቀሙት የእጅ ስልክ በኩል ያለ ምንም እንግልት ገቢ በማድረግ ፈጣንና አስተማማኝ የሆነውን አፖሎ እንዲቀላቀሉ ይጋብዛል፡፡ በአሁን ሰዓት በፋይናንስ ዘርፍ በዋነኛነት በጥቅም ላይ እየዋሉ ከሚገኙ የባዮሜትሪክ መለኪያዎች ከዚህ እንደሚከተለው በጥቂቱ ተብራርተዋል፡፡

–   የጣት አሻራ ማረጋገጫ
አሁን ላይ በአብዛኛው በስራ ላይ የዋለ የባዮሜትሪክ መለኪያ ዓይነት ሲሆን ቴክኖሎጂው ለተጠቃሚዎች ምቹ ከመሆንም ባለፈ የእያንዳንዱ ሰው አሻራ ከሌላው ተገልጋይ ልዩ በመሆኑ ግለሰቡ/ደንበኛው የሰጠው ግላዊ  የደህንነት መጠበቂያን በሌሎች ለመጭበርበር ከባድ  በማድረግ ደንበኛው ደህንነቱ በበቂ ሁኔታ የሚጠበቅበትን አማራጭ ይሰጣል፡፡
–    የፊት ገጽታ ማረጋገጫ
በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ  የአገልግሎት ተጠቃሚውን የፊት ገጽታ ጨምሮ በፊቱ ላይ ያሉ ልዩ ምልክቶችን በመመርመር በፍጥነትና ለፍጹምነት በቀረበ አግባብ የተጠቃሚውን ማንነት መለየት የሚያስችል ነው፡፡ አፖሎ በኢንደስትሪው ካሉ ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች በቀዳሚነት አሰራሩን ያስተዋወቀ ሲሆን ይህም ባለፉት ጊዜያት በይለፍ ቃል ስርቆትና መጥፋት ሲደርሱ የነበሩ የፋይናንስ ደህንነት ጥሰቶችን  የሚከላከል ፍቱን መፍትሄ በመባል ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡
–     የድምጽ ማረጋገጫ
ድምጼ የሞባይል ባንኪንግ ግብይት ወይንም ገንዘብ ለማስተላለፍ ይረዳኛል ብለው አስበው ያውቃሉ? እያደገ በመጣው የባዮሜትሪክ ደህንነት መጠበቂያ ስርዓት ማዕቀፍ ውስጥ የደንበኛውን ድምጽ በመለየት ወደ ሚፈልገው አገልግሎት መሄድ የሚችልበትን ስርዓት ከማመቻቸቱም በላይ ደንበኛው ጣቶቹን ሳይጠቀም ገንዘብ ለመላክ ወይንም ሌሎች ተግባራትን ጨምሮ ለመከወን የሚችልበትን አዲስ አሰራር የሚያመቻች ነው፡፡

ከደንበኞች በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች
አዳዲስ የቴክኖሎጂ እመርታዎች የዲጅታል ፋይናንስ ዘርፍን ማዘመናቸው የማይካድ ሀቅ ቢሆንም ደንበኞች በተደጋጋሚ የሚያነሷቸው በርካታ ከግለሰብ የፋይናንስ ደህንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች አሉ.፡፡ በዚህ ርዕስ ስር የትኞቹ ጥያቄዎች በደንበኞች እንደሚነሱና በምን አይነት የደህንነት ጥበቃዎች እንደሚመለሱ እንመለከታለን፡፡

1. የግል መረጃዎቼ እንዴት ባለ መንገድ ይጠበቃሉ?
በየትኛውም በበይነ መረብ የሚሰጥ የፋይናንስ አገልግሎት ለማግኘት በሚደረግ ምዝገባ ወቅት የሚሰጡ ግላዊ መረጃዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ግላዊ መረጃዎች ለባለቤቶቻቸው ያላቸውን ከፍተኛ አስፈላጊነትና በግላዊ መረጀዎቹ ላይ ሊደርስ የሚችል ምዝበራ ወይም ስርቆት በግለሰቦች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ከፍተኛ ጉዳት ከግምት በማስገባት የዲጂታል ባንኪንግና መሰል የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎት ሰጪዎች ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ማመስጠሪያ መተግበሪያዎችን ብሎም ጠንካራና ቀጣይነት ያላቸውን የደህንነት ቁጥጥሮች ያደርጋሉ፡፡ በመሆኑም የደንበኞች ግላዊ መረጃዎች ለፍጹምነት በቀረበ አግባብ ይጠበቃሉ፡፡

2.  የባዮሜትሪክ መረጃዎቼ በአጋጣሚ ቢቀየሩስ?
ከላይ የደንበኞች የባዮሜትሪክ ዳታ ልዩ የሆነ ባህሪና በሌሎች ለመጭበርበርና ለመቀየር አስቸጋሪ መሆኑ የተጠቃሚዎችን ደህንነት ከማስጠበቅ አንጻር ቀዳሚውና በብዙ አገልግሎት ሰጪዎች ዘንድ ተግባራዊ እንደሚደረግ አይተናል፡፡ ሆኖም ደንበኛው የባዮሜትሪክ መረጃውን ከሰጠ በኃላ በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት፣ መሰረታዊ ለውጥ ወይንም ሌላ ተፈጥሮአዊ ገጽታን ሊቀይሩ የሚችሉ ነገሮች ቢገጥሙትስ? ይህን በተመለከተ በተቋማት ዘንድ እንደ መፍትሄ የሚቀርበው ተደራራቢ/ተከታታይ ማረጋገጫዎችን (Multifactor Authentication) ጥቅም ላይ ማዋል ሲሆን ይህም ደንበኛው በአካላዊ ገጽታው ላይ ለውጥ ወይንም አደጋ ቢፈጠር ሊጠቀምባቸው የሚችሉ እንደ የይለፍ ቃል ያሉ አማራጭ የደህንነት መጠበበቂያ መንገዶችን ለመከተል ይቻላል፡፡

3.   እንዴት ባለ መንገድ ጠንካራ የይለፍ ቃል ማዘጋጀት እችላለሁ?
የይለፍ ቃል ማዘጋጀትን በተመለከተ በአብዛኛው በተጠቀሚዎች ዘንድ የሚስተዋለው ክፍተት ለማስታወስ ቀላል የሆኑና ለደህንነት ጥቃት አድራሾች ግምት ቅርብ የሆኑ እንደ ስልክ ቁጥርና የልደት ቀን የመሳሰሉ የይለፍ ቃላትን መጠቀም ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በቀላሉ ሊገመቱ የማይችሉ የይለፍ ቃላትን ማዘጋጀት መፍትሄ ነው፡፡ ግን እንዴት? በሚጠቀሙት የእጅ ስልክ ወይም በኮምፒዩተርዎ ላይ የሚገኙትን ልዩ ልዩ ስርዓተ ነጥቦች ፣ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ኪቦርድ የሚጠቀሙ ከሆነ የካፒታልና ስሞል ፊደላትን ቀላቅሎ መጠቀሙ የይለፍ ቃልዎን ጠንካራ ያደርገዋል፡፡

4. በምጠቀመው የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎት ላይ የደህንነት ጥሰት መኖሩን ከጠረጠርኩ ምን ላድርግ?
በሚጠቀሙት የዲጅታል  አገልግሎት ላይ የፋይናንስ አገልግሎት ደህንነትዎ ላይ ጥርጣሬ ካደረብዎ፣ ያለ ማመንታት ወደ ደንበኞች አገልግሎት ማዕከል ይደውሉ፡፡ ይህን በማድረግዎ ማንኛውም አይነት ጥሰት ካለ የሚስተካከልበት ወይንም ተጨማሪ ምርመራ የሚደረግበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ፡፡

5.  አፖሎ እንዴት ባለመንገድ የፋይናንስ ደህንነቴን ይጠብቅልኛል?
የደንበኞችን ደህንነት መጠበቅና ይህም በአግባቡ መፈጸሙን ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባሩ የሆነው አፖሎ  ለዚህ ዓላማው መሳካትም የተለያዩ አሰራሮችን ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ከእነዚህም መካከል በዋነኛነት በመተግበሪያው የሚገለገሉ ደንበኞቹን ከመጭበርበር ለከላከል እንዲሁም አደጋ ከመድረሱ በፊት ያልተለመዱ ብሎም አጠራጣሪ ሁኔታዎች መኖራቸውን የሚጠቁም በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ ጠንካራ የቁጥጥር ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል፡፡ ይህ በመሆኑም የደንበኞች ደህንነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አስተማማኝ በሆነ መሰረት ላይ እንዲቀመጥ ያደርገዋል፡፡

6.  የአፖሎ የይለፍ ቃሌ ቢጠፋብኝ እንዴት አድርጌ ሌላ የይለፍ ቃል ማግኘት እችላለሁ?
የይለፍ ቃልዎን በተለያየ አጋጣሚ ሊረሱት፣ ስልክዎ ወይም ኮምፒዩተርዎ ሊጠፋብዎ ይችላል፡፡ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም፣ በቅድሚያ በመተግበሪያው ላይ ወደ መጀመሪያው ገጽ በመሄድ የይለፍ ቃል መርሳት የሚለውን ቁልፍ በመጫን የሚቀርቡልዎትን የማጣሪያ ጥያቄዎች መመለስ ይኖርብዎታል፡፡ በመቀጠልም በምዝገባ ወቅት በሰጡት ስልክ ቁጥር ወይንም ኢሜይል በኩል የተላከልዎትን የማረጋገጫ ኮድ/ማስፈንጠሪያ በመጠቀም አዲሱን የይለፍ ቃልዎን ማዘጋጀት ይችላሉ፡፡

የእርስዎ ደህንነት በአፖሎ
ዲጂታል ባንኪንግ ቅንጦት ሳይሆን በዕለት ተዕለት ስራችን ላይ ትልቅ የቴክኖሎጂ አቅም ሲሆን አቢሲንያ ባንክም በዘርፉ ፈር ቀዳጅ የሆነውን የአፖሎ መተግበሪያ ከአስተማማኝ የደህንነት መጠበቅያ ስርዓቱ ጋር  ለተጠቃሚዎች ይፋ ካደረገ ሰንበትበት ብሏል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግልጽ እንደሚስተዋለው ብዙዎች ወደ አዲሱ የዲጂታል ዓለም በፍጥነት እየተቀላቀሉ መሆኑን ተከትሎ አስተማማኝ የደህንነት መጠበቂያ ስርዓት መዘርጋት ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አፖሎ የደንበኞቹን የአገልግሎት እርካታ ከማረጋገጥ እኩል የደንበኞቹን ደህንነት መጠበቅ ተቀዳሚ ዓላማው አድርጎ በትኩረት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button