ባንካችን አቢሲንያ ዛሬ የካቲት 25 ቀን 2018 ዓ.ም ለጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ እና ማገገሚያ ማዕከል የህንጻ ግንባታ ዕገዛ ይውል ዘንድ የ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
ባንካችንን በመወከል በስፍራው የተገኙት የባንካችን ዴፒዩቲ ቺፍ ከስተመር ሪሌሽንሺፕና አክዊዜሽን ኦፊሰር የሆኑት አቶ ወሰንየለህ አበራ ድጋፉን ካስረከቡ በኋላ “እናንተ አብዛኞቻችንን በግልና በቡድን የማንችለውን ሸክም ተሸክማችኋል“ ያሉ ሲሆን አክለውም “መጥተን ስለጎበኘናችሁ እጅግ በጣም ተደስተናል፡ የዛሬው ድጋፋችንም የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው አይሆንም” ብለዋል።
የጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ እና ማገገሚያ ማዕከል መሥራችና ሥ/አስኪያጅ የሆኑት ሊቀህሩያን መለሰ አየለ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው “አቢሲንያ ባንክ ዛሬ ያደረገልን የገንዘብ ድጋፍ በባንክ ደረጃ ከተደረጉልን ድጋፎች ሁሉ ከፍተኛው ነው“ሲሉ ተናግረዋል። “የባንኩ ሠራተኞች በተለይ በበዓል ወቅት በግልም ሆነ በጋራ መጥተው የሚጎበኙን ሲሆን የዛሬው ግን የተለየ ነው“በማለት አድናቆታቸውንም ገልጸዋል።
በዚህ የድጋፍ ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ የባንካችን የበላይ የሥራ አመራሮች እና ሠራተኞች የተገኙ ሲሆን 720 ለሚሆኑና በማዕከሉ ተጠልለው ለሚገኙ የአዕምሮ ሕሙማንም የምሳ ግብዣ ተደርጓል ።
በመጨረሻም የማዕከሉ መስራችና ሥ/አስኪያጅ የሆኑት ሊቀህሩያን መለሰ አየለ ለባንካችን የምስጋና የምስክር ወረቀትና ዋንጫ ያበረከቱ ሲሆን እንደ አቢሲንያ ሁሉ ሌሎች ባንኮችም የድጋፍ እጆቻቸውን እንዲዘረጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል።








Leave a Reply