የባንኮች ብድር አሰጣጥና ለመበደር የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች

የባንኮች ብድር አሰጣጥና ለመበደር የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች

የብድር አሰጣጥ ሂደቶች ከባንክ ባንክ የተለያዩ እንደመሆናቸው የብድር  መመሪያዎችና ፖለሲዎችም እንዲሁ ከተቋም ተቋም በተወሰነ ደረጃ የተለያዩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ባንኮች የብድር ማመልከቻ ከመቀበል ጀምሮ ደንበኛ ወይም ተበዳሪ የሚፈልገውን የብድር መጠን ለመፍቀድ እንዲሟላ የሚፈልጉት፣ የጋራ መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሁም መስፈርቶች አሉ፡፡ አነዚህን መስፈርቶችና ጉዳዮች በሚገባ መገንዘብና አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ በሂደት ማሟላት የብድር ጥያቄ ውድቅ እንዳይሆን ከማገዝ ባለፈ፣ የሚፈለገውን የብድር መጠን ሳይቀናነስ ከባንኮች የማግኘት ዕድልን ያሰፋል፡፡ በተጨማሪም የብድር ጥያቄ ከቀረበ በኋላ አስፈላጊ ሰነዶች እንዲሁም ቅድመ ሁኔታዎች ባለመሟላታቸው ምክንያት በመመላለስ የሚባክነውን የአበዳሪ ተቋሙንም ሆነ የደንበኛውን ጊዜና ጉልበት ያድናል፡፡

ከሌሎች የብድር ተቋማት በተለየ ሁኔታ፣ ባንኮች ከተለያየ አቅጣጫ ሊመጣ የሚችል አደጋን (Risk) ለመለየትና ብድሩ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ (Credit Risk) ቀድሞ ለመከላከል፣ በርካታ ገንዘብ-ነክ እና ገንዘብ-ነክ ያልሆኑ የትንተና መሣሪያዎችንና ዘዴዎችን (Trend Analysis, Ratio Analysis, Fund Flow & Cash Flow Analysis, SWOT Analysis, Business Plan Analysis, PESTEL, 5C’s, Market Analysis etc) ይጠቀማሉ፡፡  እንዲሁም የብድር ትንተናና ግምገማ ጥልቀትና ስፋቱ እንደ ብድሩ ዓይነትና መጠን እንዲሁም ድርጅቱ እንደሚገኝበት ዘርፍ የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የብድር ጥያቄው ለአዲስ ፕሮጀክት ወይም ለነባር ፕሮጀክት ማስፋፊያ በሚሆንበት ወቅት፣ ተበዳሪው ከሚያቀርበው የአዋጭነት ዝርዝር ጥናት በመነሳት ለሌሎች ብድሮች ከሚደረገው የመመዘኛ ትንተና በተለየ ወይም በተጨማሪ ስለ ገበያ ሁኔታ፣ በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ስላለው ክፍተት፣ ስለ ዘርፉ የገበያ ፉክክር፣ ስለ ድርጅታዊ መዋቅሩና አስተዳደሩ፣ ስለ ቴክኒካል ጉዳዮች፣ ስለ ጥሬ ዕቃ አቅርቦት መኖር፣ ስለ ምርቱ ወጪና ዋጋ፣ ስለ ህጋዊነቱና ትርፋማነቱ፣ በአጠቃላይ ስለ ንግዱ አዋጭነትና ቀጣይነት ሠፊና ጥልቅ ጥናት ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ይካሄዳል፡፡ ስለሆነም እንዲቀርቡ የሚፈለጉት ሰነዶች እንዲሁም እንዲሟሉ የሚጠበቁት መስፈርቶች ለባንኮች የብድር ትንተና  ግብዓትነት የሚያገለግሉ  ወይም የሚወሉ ናቸው፡፡

ሌላው አበዳሪ ተቋማት በብድር አሠጣጥ ሂደት ያላቸው የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ አነስተኛ የብድር ተቋማት በአብዛኛው፣ የሚሠጡአቸው ብድሮች ሙሉ በሙሉ በመያዣ (Collateral) እንዲሸፈኑ በማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ሂደት የሚከተሉ ሲሆን፣ ባንኮች በበኩላቸው የሚሠጡት ብድር ንብረትን በመያዝ ስጋቱ (Risk) እንዲሸፈን ቢፈልጉም፣  ዋና ትኩረታቸው ግን አስተማማኝ የገንዘብ ፍሰት (Cash Flow) መኖሩ ላይ ነው፡፡ ስለሆነም የተበዳሪውን የገንዘብ ፍሰት ትንበያን በመተንተን ተበዳሪው በየወቅቱ የሚኖረውን የመክፈል አቅም ይመዝናሉ፡፡ በአጠቃላይ ለባንኮች የብድር መያዣ፣ ከደንበኛው የመክፈል አቅምና ፍላጎት እንዲሁም የንግዱ አዋጭነት ቀጥሎ የሚመጣ ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እንዲሁም በርካታ የብድር አገልግሎቶች የመኖራቸውን ያህል እያንዳንዱ የብድር አገልግሎት የራሱ የሆነ (Specific) ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታዎችን፣ መስፈርቶችንና ሰነዶችን ይጠይቃል፡፡  በመሆኑም፣ ለዛሬ እንደ መነሻ ንግድ ባንኮች በብድር አሠጣጥ ሂደት በመሠረታዊ ደረጃ ትኩረት የሚየደርጉበትን ጉዳዮች፣ ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሁም የሚከተሉትን የብድር አሠጣጥ ሂደትን ብቻ በጥቂቱ ለመጠቃቀስ እንሞክራለን፡፡

1。 የተበዳሪው ፀባይ (Character)

ከብድር ክፍያው ጋር በተገናኘ ባንኮች መረዳት ከሚፈልጉት ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው የተበዳሪው የብድር ታሪክ (Credit history) ሲሆን፣ በዚህም ከዚህ በፊት ምን ዓይነት የብድር ልምድ እንዳለው፣ ከየትኞቹ ተቋማት እንደተበደረ፣ ምን ዓይነት ብድር እንደወሰደ፣ የብድር ክፍያውን በወቅቱ ይፈፅም እንደነበረ፣ ከዚህ በፊት ተበድሮ ሙሉ በሙሉ የዘጋቸው ብድሮች መኖራቸውን ጭምር የሚዳሰስበት ሲሆን ይህንንም አሁን ላይ የእንዳንዱ ተበዳሪ ዝርዝር መረጃ (Credit Information)፣ ከጋብቻ ሁኔታ ጀምሮ፣ ምን ዓይነት ብድር መያዣ እንዳቀረበ፣ የት ባንክ ላይ ምን ዓይነት ብድር እንደጠየቀና አሁን ላይ ምን ያህል ያልተከፈለ ቀሪ የብድር መጠን እንዳለበት፣ የብድሮቹ ጤነኝነት ጭምር በብሔራዊ ባንክ የብድር መረጃ ቋት ውስጥ ስለሚገኝ፣ ከብድሩ ጋር የሚነካኩትን ግለሶቦች (ያገባ ከሆነ የባለቤቱን እንዲሁም የብድር መያዣ ንብረቱን ዋቢ አድርጎ የሚያቀርብለትን ግለሰብ) የታክስ መለያ ቁጥር በመጠቀም መረጃዎችን ለማግኘት የሚችሉበት አሰራር በመኖሩ፣ ባንኮች ተበዳሪው ለብድር ብቁ መሆኑን (Creditworthiness) ለማረጋገጥ፣ መረጃዎቹን ለብድር ትንተና ግብዓት ይጠቀሙበታል፡፡ ስለዚህም እያንዳንዱ ከብድር ጋር የተገናኘ እንቅስቃሴ፣ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ማካሄድ እና ተበዳሪው ቃል በገባውና ብድር ውል ላይ በሰፈረው መሠረት ክፍያዎችንና ግዴታዎችን በአግባቡ መፈጸም፣ ከማንኛውም አበዳሪ ተቋም ጋር በቀጣይ ለሚኖር የብድር ግንኑነት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በርግጥ ከፀባይ ጋር በተገናኘ በዚህ ብቻ አይወሰንም፡፡ ሌሎች የተበዳሪው ግልጽነት፣ መረጃ የመስጠት ፍላጎት፣ የትብብር መንፈስ፣ ክህሎት፣ የግል ታሪክ እና ዝና  ግምት ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡

2。የብድር መያዣ (Collateral)

ምንም እንኳን ባንኮች የሚከተሉት ገንዘብ ፍሰት ላይ ትኩረት ያደረገ (Cash-flow based lending) አካሄድ ነው ተብሎ ቢታሰብም፣ እስከተቻለ ድረስ የብድር መያዣን እንደ ሁለተኛና የመጨረሻ አማራጭ ሲገለገሉበት ይታያል፡፡ የብድር መያዣ፣ አንድ ተበዳሪ ለተበደረው ገንዘብ ዋስትና ወይም ብድሩ ስለመከፈሉ መተማመኛ ይሆን ዘንድ የሚያቀርበው ወይም የሚያስይዘው ንብረት ሲሆን ይህም በዋናነት ቤት፣ ህንፃ፣ ማሽን፣ መጋዘን፣  የማምረቻ ቦታ እንዲሁም መኪና ሊሆን ይችላል፡፡  በዚህም ተበዳሪው በራሱ ስም የተመዘገበ ንብረትን በመያዣነት ሊያቀርብ የሚችል ሲሆን በተጨማሪም ለሚበደረው ብድር ሌላ በሶስተኛ ወገን ተመዝግቦ የሚገኝ ንብረትን ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ባንኮች፣ የብድር መያዣው በማንና በምን ይዞታ ላይ እንደሚገኝ እንዲሁም አሁን ላይ በገንዘብ ምን ያህል ይገመታል የሚለውን ጥያቄ የተለያዩ ባለሙያዎችን በመጠቀም የሚያስጠኑ ሲሆን፡፡ ለዚህም ባንኮች ለእያንዳንዱ የብድር መያዣ ንብረት የራሳቸው የሆነ የሚመሩበት የግምት መመሪያ (Valuation Manual)  አላቸው፡፡ መመሪያውም፣ ለምሳሌ ንብረቱ ማሽን ከሆነ ለተለያዩ ዓላማዎች የሚውሉ በመኖራቸው ምክንያት የትኛው ማሽን ተቀባይነት ይኖረዋል (ከተመረተ ምን ያህል ጊዜ) ከሚለው ጀምሮ በርካታ ዝርዝር ነገሮች የተቀመጡበት ነው፡፡  ከብድር መያዣ ጋር በተገናኘ ከባንኮቹ የግምት መመሪያ በተጨማሪ በብሔራዊ ባንክ በኩል የተቀመጠ ሁሉም ባንኮች የሚተዳደሩበት የበላይ የሆነ መመሪያም ይገኛል፡፡ ነገር ግን ንግዱ ከሚገባው በላይ አዋጪ ሆኖ በተገኘ ጊዜና ሁኔታ እንዲሁም ከላይ የተጠቀሱት መስፈርቶች በበቂ ሁኔታ የተሟሉ ሆኖ ሲገኝ የባንኮችን ያለ መያዣ እስከማበደር ሊደርስ የሚችል የማበደር ፍላጎት (Appetite) ይከፍታል፡፡   

3。ካፒታል (Capital)

 ካፒታል አንድ የሚጠቁመው ነገር የድርጅቱ ባለቤት ለንግዱ ወይም ለሥራው ያለውን ቁርጠኝነት  እና በሥራው ያለውን መተማመን ሲሆን፣ ስለዚህም የድርጅት ካፒታል አስተማማኝና ሥራውን የሚመጥን ሆኖ እንዲገኝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

4. የሥራ ዕቅድ (Business Plan)

የብሄራዊ ቁጠባችን ትንሽ መሆን ላይ ከፍተኛ የብድር ፍላጎት ተጨምሮበት በባንኮች እጅ የሚገኘው ገንዘብ ውስን ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን ውስን የህዝብ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀምም ጭምር ባንኮች አንድ ሌላ ማረጋገጥ የሚፈልጉት ጉዳይ ቢኖር ብድሩ የሥራ ዕቅድ ላይ በተቀመጠው መሠረትና ባንኮቹ ለተስማሙበት ትክክለኛ ዓላማ መዋሉን ነው፡፡ ለዚህም ተበዳሪው በብድር የሚያገኘውን ገንዘብ ለምን ዓላማ እንደሚያውለው፣ የጠየቀው ብድር በምን መልኩ ጥቅም ላይ እንደሚውል፣ ብድሩን ቢያገኝ የድርጅቱ የገንዘብ ፍሰት ምን እንደሚመስል፣ ዘርፉ ውስጥ የሚኖረውን የገበያ ድርሻ፣ በምን ስልት ዕቅዱን እንደሚያሳካ፣ የቢዝነሱ ዋና አቅራቢዎችና ደንበኞች ማን እንደሆኑ እንዲሁም ሌሎች የሥራ ዕቅዱ ማካተት የሚኖርበትን ነገሮች ሁሉ ባንኩን በሚያሳምን መልኩ በሚገባ በጽሑፍ አዘጋጅቶ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ይህ የሥራ ዕቅድ ለብድርም ሲባል ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ድርጅት የግድ ሊኖረው የሚገባ እንደ የጉዞ ካርታ የሚያገለግለውና በየጊዜው ሊዘጋጅ የሚገባ በመሆኑ፣ የሥራ ዕቅድ መጻፍና ማዘጋጀትን ልማድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ የሥራ ዕቅድ ለባንኮች ዋናና ጠቃሚ የብድር ትንተና ሂደት ግባዓት ሆኖ ይገኛል፡፡

5。የገንዘብ ዓቅም (Capacity)

 ብድርን ለመክፈል የሚያስችል የገንዘብ ፍሰት ወይም ሃብት መኖሩን ማረጋገጥ ሲሆን ይህንንም የዕዳ ክፍያን ከገቢ ጋር በማነፃፀር የሚታይ ነው፡፡ ለዚህም የገንዘብ አስተዳደር ስርዓትን በየጊዜው ማሻሻልና ማጠናከር ተገቢ ነው፡፡

6。የብድር ስጋት ደረጃ (Credit Risk Grading/Rating)

ባንኮች የደንበኞችን የብድር ስጋት ደረጃ ለመለየት የሚጠቀሙበት ስርዓት ሲሆን፣ በዋናነት ተበዳሪው ወይም ደንበኛው በብድር ውሉ መሠረት ቃል የገባውን ግዴታ ሳይወጣ ቢቀር ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት (loss) የሚመዝኑበት ነው፡፡  በውስጡም የተበዳሪ ድርጅቱ አስተዳደር ስጋት (Management Risk) ጨምሮ፣ ከዚህ ጋር በተገናኘም በድርጅቱ ውስጥ ተተኪ ወይም የመተካካት ዕቅድ (Succession Plan) መኖሩን፣ ተተኪው አሁን ላይ በድርጅቱ ውስጥ የሚገኝበት ቦታ፣ በአስተዳደሩ ላይ የሚገኙ ግለሰቦች ከሥራው ጋር የተገናኘ ልምድና የትምህርት ዝግጅት፣ ለድርጅቱ ስልት (Strategy) ስኬት አስፈላጊ የሆነው የሠራተኛውና የአስተዳደሩ ግንኙነት፣ የደንበኛው የገንዘብ አስተዳደር ስርዓት ጥንካሬ፣ የሒሳብ መግለጫ (Financial Statement) ጥራት፣ የደንበኛው ታማኝነትና የትብብር መንፈስ፣ እስከ አሁን ድረስ ያለው የብድር ሒሳብ አጠቃቀም፣ ድርጅቱ የሚገኝበት ዘርፍ በምን ሁኔታ እንደሚገኝ፣ የገበያ ፉክክሩ እንዲሁም የገበያ ድርሻው እና የድርጅቱ አጠቃላይ የሥራ አከናወን (Business Performance) ተገምግሞ ደረጃ ወይም ነጥብ የሚሠጥበት ሂደት ሲሆን ተበዳሪው ወይም ደንበኛው እዚህ ጋር የሚያገኘው ደረጃ ወይም ነጥብ (Score) የተለያዩ መብቶችና ጥቅሞች የሚያሰጠው ወይም የሚያሳጣው ነው፡፡ ሆኖም የዚህ ውጤት ምንም ይሁን ምን ባንኮች ለሀገር ለወገን እጅግ ይጠቅማል ብለው የሚያምኑበትን ብድር ወይም ተበዳሪ (Case) በመመሪያቸው ወይም በፖሊሲያቸው ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው በልዩ ሁኔታ (Exceptions) የሚያዩበት አሠራር አላቸው፡፡

7。ሌሎች አስፈላጊ ሠነዶችና ቅድመ ሁኔታዎች

  • ሕጋዊ እና አዋጭ የንግድ ሥራ ያለው 
  • ሕገወጥ የንግድ ተግባር ያልፈፀመ
  • ጤናማ የባንክ ሒሳብ አጠቃቀም ያለው 
  • ተበዳሪዎች፣  ዋና ዋና የአክስዮን ባለቤቶች እና ከደንበኛው ጋር የባለቤትነት ዝምድና ያላቸው ድርጅቶች የተበላሸ ብድር በማንኛውም ባንክ ከሌላቸው
  • የብድር ማመልከቻ
  • የታደሰ የንግድ ወይም የኢንቨስትመንት ፈቃድ ያለው
  • ዋና የምዝገባ የምስክር ወረቀት
  • የግብር ከፋይ የምዝገባ ምሰክር ወረቀት
  • ኦዲት የተደረገ ወይም ኘሮቪዝናል  የሒሳብ መግለጫ
  • የእህት ድርጅቶቹ ዝርዝርና የሒሳብ መግለጫ
  • የሥራ ዕቅድ እና የገንዘብ ፍሰት ትንበያ መግለጫ
  • የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር እና ቦርድ የትምህርት ደረጃ ኃላፊነትና  የሥራ ልምድ
  • የድርጅቱ መተዳደሪ ደንብ እና መመስረቻ ጽሁፍ
  • የተመዘገበ ቃለ ጉባኤ
  • ድርጅቱ የተቋቋመበት የጋዜጣ ማስታወቂያ አዋጅ   
  • የጋብቻ ሁኔታን የሚገልጽ ሰነድ
  • የሽርክና ሰነድ
  • የቦርድ የድጋፍ ደብዳቤ  /በቦርድ ለሚተዳደሩ እና የቦርድ ፈቃድ ለሚያስፈልጋቸው /
  • ዋስትና
  • ለውጭ ዜጐች የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ
  • የመድን ዋስትና/ብድሩ ከተፈቀደ በኋላ/

ከላይ የተጠቀሱት ቅድመ ሁኔታዎችና ሠነዶች እንደ ብድሩ ዓይነትና አሰፈላጊነት ዝርዘሩ ሊጨምርና ሊያንስ ይችላል፡፡ እንዲሁም አብዛኞቹ ባንኮች ለእያንዳንዱ የብድር አገልግሎት አስፈላጊ ሠነዶችና ቅድመ ሁኔታዎችን በዝርዝር የያዘ ቼክ ሊስት (Check List) አዘጋጅተው የሚሠጡ ሲሆን፣ ከዚህ ጋር በተገናኘ የተወሰኑ ባንኮች ለደንበኞች ወይም ለተበዳሪዎች ልዩ አማካሪ (Financial Advisor and Relationship Manager) አላቸው::

አለማየሁ ስሜነህ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button