አቢሲንያ ባንክ የተጠናቀቀውን የ2024/25 በጀት ዓመት የሥራ አመራር ጉባዔውን ሐምሌ 17 እና 18 ቀን 2017 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ሲያካሂድ ቆይቶ ሊበረታቱና ሊሻሻሉ የሚገባቸውን የሥራ አፈፃፀሞች በመለየትና የባንኩን ቀጣይ ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች በማስቀመጥ በስኬት ተጠናቅቋል።
በስብሰባው ላይ በዋና ዋና ቁልፍ መለኪያዎች አፈፃፀም ከዕቅድ አንፃር የተሠሩ ሥራዎች በዲስትሪክቶች በሰፊው የተነሱ ሲሆን አፈጻፀማቸው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንፃር የበለጠ የተሳካበት ዓመት እንደነበረ ተገልጿል።
የዲጂታል ዘርፉን ለማሳደግ በባንካችን እየተተገበረ በሚገኘውና ባንካችንም የሚታወቅበትንና የኢንዱስትሪው መሪነቱን ባረጋገጠበት የዲጂታል ዘርፍም አዳዲስ የቴክኖሎጂ አሰራሮችን በመተግበር ከዚህ ቀደም ከተመዘገበው የላቀ አፈፃፀም ማምጣት ይቻል ዘንድ ሁሉም ዲስትሪክቶች እንዲሁም በዋናው መ/ቤት የሚገኙ የሥራ ክፍሎች ሥራቸው የተገመገመበት ጉባዔ ነበር፡፡
በጉባዔው በአፈፃፀማቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ዲስትሪክቶች የምስጋና እና ማበረታቻ የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ሲሆን ሽልማታቸውንም ከባንካችን የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መኮንን ማንያዘዋል እና ከባንካችን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ በቃሉ ዘለቀ ተረክበዋል፡፡
በዚህም መሠረት የሃዋሳ ዲስትሪክት የአንደኝነትን ደረጃን ሲቀዳጅ በሁለተኝነት የምስራቅ አዲስ አበባ ዲስትሪክት እንዲሁም የመካከለኛው አዲስ አበባ ዲስትሪክት በ3ተኛነት ደረጃ አጠናቀዋል፡፡
በተጨማሪም በዓመቱ አፈፃፀም ልዩ ተሸላሚና ዕውቅና የተሰጠው በተለይም የዓመቱን ተጨማሪ የተቀማጭ ሂሳብ ዕድገት አፈፃፅም ከተከታታይ ሩብ ዓመታት አንፃር በመጨረሻዎቹ ሩብ ዓመታት በከፍተኛ መሻሻል /Great Come Back/ አበረታች ዉጤት ላስመዘገበው የጂማ ዲስትሪክት የዕውቅና ስርተፍኬት ተሰጥቶታል።
ለሁለት ቀናት በተካሄደው በዚሁ ዓመታዊ የሥራ አመራር ጉባዔ ላይ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ አመራር አባላት፣ የባንኩ ሥራ አመራር አባላት፣ የዋናው መ/ቤት እና የዲስትሪክት ዳይሬክተሮች እንዲሁም የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡








Leave a Reply