አቢሲንያ ባንክ ዛሬ ነሐሴ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ከፋስትፔይ (Fastpay LLC) ጋር ዓለም ዓቀፍ ዲጂታል የሐዋላ አገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ የሚረዳውን የሳይበር ሶርስ (Cybersource) የክፍያ አማራጭ ቴክኖሎጂ የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ተፈራርሟል፡፡
ባንካችንን በመወከል የደንበኞች ማኔጅመነት ዋና አፊሰር አቶ ደሳለኝ ይዘንጋውና በፋስትፔይ በኩል ደግሞ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም መርዳሳ የመግባቢያ ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡
ይህ ስምምነት በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወይም ማንኛውም ቪዛ ወይም ማስተር ካርድ ያላቸው ግለሰቦች በኢትዮጵያ ለሚገኙ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ገንዘብ በዲጂታል የሐዋላ አገልግሎት መላክ የሚያስችላቸው የክፍያ አማራጭ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ፋስትፔይ (Fastpay LLC) ባበለጸገው “ፋስትፔይ” መተግበሪያ አማካኝት የቪዛ ወይም ማስተር ካርዳቸውን ተጠቅመው ወደሀገር ቤት በሐዋላ ገንዘብ ለሚልኩ ሰዎች ወዳጅ ዘመዶች ባንካችን ክፍያቸውን በማቀላጠፍ ድርሻውን ይወጣል፡፡
ይህ ቴክኖሎጂ በዋነኛነት የውጭ ምንዛሪ አቅምን ያሳድጋል፣በውጪ ለሚኖሩ ሰዎች ከሌሎች የሐዋላ መላኪያ ዘዴዎች በተሻለ በቀላሉና ከአገልግሎት ክፍያ ነጻ በሆነ መልኩ ገንዘብ መላክ ያስችላል፣ የዲጂታል ግብይቶችን በማሳደግ የደንበኞችን ልምድና እርካታን ያሻሽላል፤ ከዚህም በላይ መንግስት በኢ-መደበኛ መንገድ የሚደረገውን የሐዋላ ዝውውር ለመቀነስ የሚያደርገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ ያግዛል፡፡
እጅግ ዘመናዊ በሆኑ ቴክኖሎጂዎች የተደገፉ የባንክ አገልግሎቶችን በመጀመር ረገድ ግንባር ቀደም የሆነው ባንካችን በቅርቡም ተግባር ላይ ያዋለው አዲስ ስትራቴጂም ለዲጂታል ስርዓት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ ሲሆን ዛሬም አስፈላጊውን የአደረጃጀትና የቴክኖሎጂ ስርዓት በማቀናጀት ለደንበኞቹ ከመቼውም ጊዜ በላይ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል፡፡










Leave a Reply