bankofabyssinia.com

‘‘ትውልድን በሥነ-ምግባር፣ተቋምን በአሰራር!’’ በሚል መሪ ቃል ለባንካችን ሠራተኞች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ

‘‘ትውልድን በሥነ-ምግባር፣ተቋምን በአሰራር!’’ በሚል መሪ ቃል ለባንካችን ሠራተኞች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ

ባንካችን አቢሲንያ ለሠራተኞቹ ሲሰጥ የቆየው ‘‘ትውልድን በሥነ-ምግባር፣ተቋምን በአሰራር!’’ በሚል መሪ ቃል ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የሚወሰዱ የመከላከያ ስልቶች ላይ ያተኮረ ስልጠና ተጠናቀቀ።

የባንካችን የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መምሪያ በራሱ ከሚሰጣቸው ስልጠናዎች በተጨማሪ ከፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በጋራ በመተባበር ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን በያዝነው የ2018 የበጀት ዓመትም በሰባት ዙር ለ700 ሰራተኞች ስልጠና ለመስጠት የያዘውን ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ ለማከናወን ችሏል።

በዚህ ለሁለት ቀናት በኢንተር ለግዠሪ ሆቴል በተሰጠው ስልጠና ላይ የተነሱ ዋና ዋና ጉዳዮችም የሙስና ምንነት፣ የሙስና አይነቶች ፣የሙስና ወንጀሎች እና ልዩ ባህሪያት፣በባንክ ዘርፍ የሚስተዋሉ የሙስና ተጋላጭነት እና ብልሹ አሰራሮች እንዲሁም የሚያስከትሉት ጉዳት፣ የሙስና መከላከያ ስልቶች …ወዘተ የሚሉ ነበሩ።

ስልጠናውንም የሰጡት የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የሆኑት ዶ/ር ዮሐንስ ጴጥሮስ፣ዶ/ር ተስፋዬ ሂርጰሳ እና ዶ/ር አወቀ አሸናፊ ነበሩ።ስልጠናው በተግባር እና በውይይት ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ በመጨረሻም ሰልጣኞቹ በሁለት ቀናት ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት የሚፈትሽ ምዘና እና የስልጠናው ውጤታማነትና ተገቢነት ላይ ግብረ-መልስ ተካሂዷል።

በስልጠናው ማጠቃለያም የባንካችን የስልጠና ክፍል ስራ አስኪያጅ የሆኑት ወ/ሮ ማርታ ዘውዴ ሙስና በየትኛውም ተቋም እንዲሁም በየትኛው የስልጣን እርከን የሚከሰት በመሆኑ፣ በሁለት ቀናት ያገኛችሁትን ዕውቀት፣ ክህሎት እንዲሁም የአመለካከት ለውጥ በመጠቀም እራሳችሁን እንዲሁም ባንካችንን ከሙስናና ብልሹ አሰራር መጠበቅ አለባችሁ ሲሉ አሳስበዋል።

በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ የኢንተር ለግዠሪ ሆቴል ለሰባተኛው ዙር ሰልጣኞች ልዩ ባህላዊ የቡና መስተንግዶ በማዘጋጀት የሥልጠናውን የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ከሰልጣኞች ጋር በኅብረት አክብረዋል።

ይህ ስልጠና ባለፈው ዓመት ለባንካችን ከፍተኛ አመራሮች፣ዳይሬክተሮች፣ዲቪዥን ስራ አስኪያጆች፣ቡድን መሪዎች እና ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች መሰጠቱ አይዘነጋም።

ምንጭ ፡ ሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና መምሪያ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button