ዲጂታል ኢኮኖሚ በኢትዮጵያ

ዲጂታል ኢኮኖሚ በኢትዮጵያ

የሰው ልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ ለኑሮ ማቅለያ አያሌ ጉዳዮችን እየከሠተ ሲገለገልባቸው ቆይቷል፡፡ በዘመናት ሒደት ውስጥ የሰው ልጅ ከፈጠራቸው ትላልቅ ጉዳዮች መካከል የቴክኖሌጂ ውጤቶች ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ ከቴክኖሌጂ ውጤቶች ጋር ተያይዞ የሚጠቀሰው በይነ መረብ (Internet) ነው፡፡ በይነ መረብ በአሁኑ ሰዓት እንደ አንድ የሰውነት አካል እስኪቆጠር ድረስ ዓለምን አንድ በማድረግ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች የሚከወኑበት ምርጥ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው፡፡ በበይነ መረብ የሚፈጸሙ ተግባራት ከመዘርዘር ይልቅ የማይፈጸሙትን መግለጽ እስኪቀል ድረስ የሰዎች ግንኙነት በጠቅላላ ከዚህ ጋር ተዋሕዷል፡፡

ሁሉንም ቅርብ ያደረገው በይነ መረብ በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በመምራትና በመቆጣጠር ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫመተም ነው፡፡ በይነ መረብን በመጠቀም የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች የምንፈፅምበትን  የዲጂታል ኢኮኖሚን ሥርዐት አስገኝቶልናል፡፡ ዲጂታል ኢኮኖሚ በበይነ መረብ አማካይነት የተለያዩ ግብይቶችን የምንፈጽምበት አሠራር ነው፡፡ የግብርና፣ የታክስ፣ የኢንዱስትሪ፣ የባንኪንግ፣ ፋይናንስ፣ የቱሪዝም፣ ቴሌኮም፣ የጤና ሊሆን ይችላል በዲጂታል ቴክኖሎጂ በታገዘ መሥራት ያስችላል፡፡

ይኽ ዲጂታል ኢኮኖሚ ከበይነ መረብ መምጣት ጋር ተያይዞ ከ1995 እ.አ.አ በስፋት ሲተገበር የነበረ ሥርዐት ነው፡፡ በአሁን ሰዓት በርካታ የአውሮፓ፣ የኤዢያ አገራት የንግድ እንቅስቃሴያቸውን ዲጂታል ኢኮኖሚ በማድረግ እየተገለገሉበት ነው፡፡ አፍሪካ ከአገር አገር ልዩነት ቢኖረውም በቴክኖሎጂ ዘርፍ እያደጉ የመጡ የአገራት ተግባራዊ እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያስ?

መሠረታዊ ልማቶችዋን (Infrastructures) በአሁኑ ጊዜ እያዘመነች የመጣችው ኢትዮጵያ፣ ዓለም በደረሰበት ቴክኖሎጂ ራሷን በማላመድ እየጣረች ነው፤ ፍጥነቱ ዝቅተኛ ቢኾንም ቅሉ፡፡ ሆኖም ታዳጊ አገራት ፊታቸውን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ባዞሩበት ሰዓት አገራችንም ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ጀምራለች፡፡ ምንም እንኳን ዓለም በዲጂታል ኢኮኖሚ በሚያደርገው ግብይት ፈጣን እድገት እያሳየ ቢመጣም በኢትዮጵያ ያለው ሒደት እጅግ አዝጋሚ ነው፡፡

ከዘመኑ ጋር መራመረድ ለድርድር የማይቀርብ  ነው፡፡ አሁን ላይ ይኽን በመረዳት ዲጂታል ኢኮኖሚን በኢትዮጵያ ለማስለመድ ከፍተኛ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ በብሔራዊ ደረጃ NATIONAL DIGITAL EKONOMIC POLICY በመቅረጽ ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመተግበር እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሴክተሮች በአሁኑ ጊዜ እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡

በአገራችን አገልግሎት ከሚሰጡ መሥሪያ ቤቶች መካከል የገቢዎች ሚኒስቴር በአሁኑ ጊዜ አሠራሩን ማቀላጠፍ የሚያስችል ኢ-ታክስ የተሰኘ ዲጂታል የታክስ አከፋፈል ሥርዐት ዘርግቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ የፋይናንስ ሚኒስቴር ዲጂታል ፋይናስ ለማድረግ እየሠራ ነው፡፡ እንዲኹም በዋናነት በዓለም ላይ የተለያዩ ግብይቶች ክፍያ የሚጸምበት ሥርዐት ኢ-ኮሜርስ (E-Commerce) የዲጂታል ክፍያ የመፈጸሚያ ሥርዐት እየተከናወነ ነው፡፡ ኢ-ኮሜርስ ማንኛውንም ግዢና ሽያጭ በበይነ መረብ (Internet) አማካይነት ማከናወን የሚያስችል የንግድ ሥርዐት ነው። (አቢሲንያ ባንክ በዲጂታል ክፍያ ረገድ የዲጂታል ንግድን (E-Commerce) ለማቀላጠፍ የሚያስችለውን የቪዛ ሳይበር ሶርስ Visa SyberSource Payment Gateway Technology የኦንላይን ክፍያ አማራጭ በማቅረብ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንደስትሪ ቀዳሚ በመሆን አገልግሎት እየሰጠ እንደኾነ ይታወቃል፡፡

አገራችን በተለያዩ ሴክተሮች የምትሰጣቸውን አገልግሎቶች ዲጂታል በማድረግ ወደ ዘመናዊ አሠራር እየሔደች እንደኾነ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ግን የንግድ፣ የኢኮኖሚ፣ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎችን፣ የተለያዩ ክፍያዎችን ዲጂታል ማድረግ ምንድን ነው ጥቅሙ?

  • የተቀላጠፈ አገልግሎት ማግኘት ያስችላል፡- አገልግሎት የሚሰጡ የመንግሥትና የግል ተቋማት ደንበኞቻቸው ባሉበት ቦታ ሆነው የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙና እንግልትን በመቀነስ በወረፋ፣ ፋይል በመፈለግ ወዘተ የሚፈጀው ምልልስ በመቀነስ አገልግሎቱ ቀልጣፋ እንዲኾ ያደርጋል፡፡
  • ምርታማነትን በማፋጠን ከፍተኛ የኾ የሥራ ዕድልን ይፈጥራል፡- በተለያዩ ምክንያች የሚጠፋው ጊዜያች በመቀነስ በሥራ ላይ የሚኖረንን ትኩረት ከፍ በማድረግ አምራችነታችን ይጨምራል፡፡
  • የሥራ እድል ይፈጥራል፣
  • በአንድ ቦታ ይሰጥ የነበረው አገልገሎት በማስፋት ተደራሽነትን ከፍ ያደርጋል፡፡
  • ንግድን በማቀላጠፍ ግብይቶች እንዲፋጠኑ ያደርጋል፡- ንግድ በተፋጠነ መጠን ምርታማነትና የሥራ ዕድል ይጨምራል፤ ንግድን ወደ ዐዲስ ዘርፍ እንዲሔድ ያነሣሣል፡፡
  • ኋላ ቀር አሠራርን በማስቀረት ለዐዳዲስ አሠራር ያዘጋጃል፡፡

ዓለም በፍጥነት እየተለወጠ ነው፡፡ በየጊዜው የሚመጡት ዐዳዲስ አሠራሮች የማናውቃቸው እስኪመስለን  ለውጡ ፈጣን ነው፡፡ ዲጂታል ኢኮኖሚው በዚኽ ተለዋዋጭ ዓለም እያደገ የመጣ፣ የንግድ ሥርዐት በማዘመን በሁሉም ቦታ ዘልቆ በመግባት አስተማማኝ የኢኮኖሚ ዘርፍ በመፍጠር ኑሮን እያቀለለ ይገኛል። በዚኽ ሒደት ራስን በፍጥነት በማላመድ እና የቴክኖሎጂውን ትሩፋት በመጠቀም እንደሠለጠኑት አገሮችና ድርጅቶች ዓለም ከደረሰበት የሥልጣኔ ጠርዝ ድረስ መጓዝ ይጠይቃል፡፡

የኢትዮጵያ ከፍታ ከዘመኑ መድረስ ብቻ ሳይኾን ከዘመኑ መቅደም ነው!

አሰናኝ ምኒልክ ብርሃኑ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button