ዕድር ለተሻለ ለውጥ!

ዕድር ለተሻለ ለውጥ!

በአካባቢያችንን የሚገኘው ዕድር ቤት አዳራሽ አናት ላይ የተሰቀለው ድምፅ ማጉያ ከመኖሩ በፊት፣ ጋሽ ፉናና የሚባሉ ጥሩንባ ነፊ ነበሩ፡፡ ጋሽ ፉናና ካልተኙ በስተቀር ጡሩምባዋ ከእጃቸው አትለይም፡፡ እኛም በልጅታችን፣ እንዲያስነፉን እንለምናቸው ነበር፤ እርሳቸውም ልጅ ስለሚወዱ አይጨክኑብንም፡፡ ነገር ግን እንደርሳቸው በጣም ማስጮኽ ስለማንችል ባገኘናቸው ቁጥር እንዲያስደግሙን ደጋግመን እንጠይቃቸዋለን፡፡
የጋሽ ፉናና ጥሩንባ በጣም ስለምትጮኽ የሰፈር ሰዎች “የሞተን ይቀሰቅሳል” ይላሉ፡፡ ነገር ግን ጡሩምባዋን ከነፉ በኋላ “እከሌ ዕድር አባል የሆናችሁ፣ እገሌ የሚባል ሰው አርፏልና ነገ ቀብር በዚህ ሰዓት ነው” እያሉ ቢናገሩም ድምፃቸው አይሰማም ነበር፤ ስለዚህ ያለን አማራጭ ማን እንደሞተ ለማጣራት እርሳቸው ዘንድ መቅረብ፤ አልያም ጎረቤት መጠይቅ ይኖርብናል፡፡
በዚህ ጊዜ የዕድሩ አባላት፣ ወንዶቹ ድንኳን ለመትከል ከዕድሩ ሊቀ መንበር ወይም ጸሐፊ ጋር ተጠራርተው ወደ ዕድር ቤቱ ይሔዳሉ፤ ሴቶቹ ነፍስ ይማርን ለማሰናዳት ሰሐን፣ ድስት፣ ኩባያ፣ ስንዴ፣ ምስር ፍለጋ ወደ ሴት ዕድር ያመራሉ፡፡ ይኽ ማኅበራዊ ሕይወት ከኢትዮጵያ ውጪ በሌላው ዓለም የተለመደ አይመስልም፡፡
በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ ስያሜዎች አሉት፡፡ ለአብነት ያህል ቅሬ፣ ጓኝ፣ አፎቻ፣ ዋለልቻ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ (ባህልና ክርስቲያናዊ ትዊፊት በኢትዮጵያ፣ ካህሳይ ገ/እግዚአብሔር፣ ገጽ 281) በቃል እንደሚነገረው ማስረጃ ከሆነ ዕድር ተጀመረ የሚባለው ከጣልያን ወረራ በኋላ በዐዲስ አበባ እና መሰል ከተሞች ነው፡፡
‹‹ሕይወትና ሞት›› በሰው ልጅ ገጽ ላይ የተጻፉ የተፈጥሮ ቃላት በመሆናቸው፣ ሰዎች እንደማይቀሩ አውቀው ለመተሳሰብ፣ ለመረዳዳትና ዐብሮነት ለማዳበር የሚፈጽሟቸው ተግባራት መካከል ዕድር ቀዳሚው ነው፡፡ ዕድር ሃይማኖት፣ ዘር፣ የፖለቲካና የኑሮ ደረጃ የሚፈጥረውን ልዩነት በመበጣጠስ፤ በአባላቱ ልቡና ውስጥ የሞተን ሰው ከሕያው ጉራ በመንፈስ የሚያስተሳስር ተቋም ነው። ሞት ለነጠቀው ቤተሰብ ደግሞ አለኝታነትን እና ጭንቀትን የሚያጋራ ጠንካራ መሠረት ነው፡፡
ዕድር ለቀብር ጊዜ የሚያገለግል ውል በመሆኑ፤ የቀብሩን ሥርዐት በሚመለክት ገንዘብ የሚዋጣበት አገልግሎት ነው። ይህም ማለት አንድ ሰው ኀዘን ሳይደርስበት አስቀድሞ ገንዘብ ያዋጣል፤ አብዛኛው የአገራችን ዕድሮች ያልተጻፈ እና የተጻፈ መተዳደሪያ ሕጎችና ደንቦች አላቸው፡፡ እነዚህን መተዳደሪያዎች የማይፈጽም ከሆነ ከገንዘብ ጀምሮ የተለያዩ ቅጣቶች የሚጠብቁት ይሆናሉ፡፡
ለዛም ነው! እኛ ኢትዮጵያውያን መሪር ኀዘን ቢገጥመንም ብቸኝነት ወይም ጭንቀት ከሚያመጣው ቀውስ ውስጥ የማንገባው፡፡ ይህንንም ቀድመን በመረዳት ባህላዊ ትውፊታችን ለሕመሙ መድኃኒት ከመፈልሰፍ ይልቅ በሽታው ቀድሞ እንዳይከሠት ዕድርን የመሠረትነው፡፡ ከዚህ አንጻር ዕድር ሥነ ልቡናዊ ጉዳትን በመቀነስ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሞተን ለመቅበር በሚል እሳቤ የተቋቋሙት ዕድሮች ወደ መረዳጃ ዕድር በማደግ እና ከተለመደው አሠራር ወጣ በማለት በልማት እና በተለያዩ በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ይህንን በጎ ጅማሬ በማስቀጠል የመመሥረቻ፣ የአባልነት ምዝገባ እና በየወሩ የሚከፈለውን የገንዘብ መጠን በመጨመር ዐቅማቸውን በማሳደግም ላይ ናቸው፡፡
ሰዎች ከመሞት ይልቅ መኖርን እንደሚጓጉ የተረዱ በርካታ ዕድሮች፣ በሕይወት መበልጸግን መርጠው ወደ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እየተጓዙ ነው፡፡ የአባሎቻቸውን ችግር በመረዳት ለአነስተኛ ንግዶች ማስጀመሪያ ገንዘብ በማበደር፤ በቤቶች ግንባታ ላይ በመሠማራት፣ የአክስዮን ግዢ በማከናወን እና የተለያዩ ተቋማትን በመገንባት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ ዕድሮች ከማኅበራዊ እና ከሥነ ልቡናዊ ፋይዳ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ያመለክታል፡፡
በዚህ የለውጥ ጉዞ የሚራመዱት ዕድሮች በአገር ግንባታ ላይ የሚኖራቸው ድርሻ የሚናቅ አይደለም፡፡ ግን ዘርፉን የበለጠ ለማዘመን የሚያግዛቸው እና የሚደግፋቸው የቢዝነስ ተቋም ያስፈልጋቸዋል፡፡
ኢትዮጵያዊ ማንነትን እና ዕሴትን በማስቀጠል ማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ የሚሳተፉ ተቋማትን በማገዝ እና አሠራራቸው በማቀላጠፍ የሚታወቀው ባንካችን አቢሲንያ፤ በዐዳዲስ አማራጮች ከጥሩ ወለድ ጋር ከዕድር ተቋማት በጋር ለመሥራት ደጁን ክፍት አድርጎ እነሆ ብሎናል፡፡ ድር ቢያብር የሚያስረው ብዙ ነው፡፡ ዐብሮነት ለዘላቂ ለውጥ መሠረት ነው፡፡
አቢሲንያ የሁሉም ምርጫ!
ምኒልክ ብርሃኑ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button