አቢሲንያ ባንክ ‘‘ለአቢሲንያ አሚን’’ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎቱ ብራንድ አምባሳደር በመሰየም በባንክ ኢንደስትሪው ቀዳሚ ሆነ፡፡
ባንካችን በጥቅምት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በስቴይ ኢዚ ፕላስ ሆቴል የባንኩ ተቀዳሚ ደንበኞች፣ የባንኩ የሥራ አመራር አባላት እና የተለያዩ የሚዲያ አካላት በተገኙበት ‘ለአቢሲንያ አሚን’’ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት በብራንድ አምባሳደርነት ከተሾመው ከአቶ ሙሐመድ ፈረጅ ጋር የፊርማ ስነ-ስርዓት አካሂዷል፡፡
በስነ-ስርዓቱም ላይ የወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚደንት፣ አቢሲንያ ባንክ የወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎቱን እ.ኤ.አ በታህሳስ 2017፤ ከ6 ዓመታት በፊት፤ መጀመሩን እና አገልግሎቱን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ‘‘አቢሲንያ አሚን’’ በሚል ሥያሜ የሸሪዓ መርሆችን መሠረት በማድረግ የተቀማጭ የብድር እና ሌሎች አገልግሎቶችን በማቅረብ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን መልመሉን፤በዚህም ከ21 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰቡን፡፡ይህም አፈፃፀም ባንኩን አገልግሎቱን ከሚሰጡ የግል የንግድ ባንኮች በአንደኝነት ደረጃ እንዳስቀመጠው ገልጸዋል፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትን ስኬቶችና በኢንዱስትሪው መሪነቱን ለማስቀጠል፣ አገልግሎቱን በሰፊው በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ተብሎ እምነት የተጣለበትን ወጣት ጋዜጠኛ እና የማስታወቂያ ባለሞያ አቶ ሙሐመድ ፈረጅን ለአቢሲንያ አሚን ለወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎቱ ብራንድ አምባሳደር አድርጎ መሾሙን በፊርማ ስነስርአቱ ላይ አብስረዋል፡፡
አምባሳደሩም የ ‘‘አቢሲንያ አሚን’’ የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶችን በሚገባ በመረዳት፤ የባንኩን ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት በብቸኝነት፤ በተለያዩ የሚዲያ ዘርፎች፤የማኅበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ፤ በድምፅ በምስልና በፅሑፍ፤ የተለያዩ የማስተዋወቂያ ዘዴዎችን በመጠቀም እንደሚያስተዋውቅ የሚጠበቅ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በተያያዘም አቶ መሐመድ ፈረጅ ከ15 ዓመታት በላይ በእስላማዊ ኪነጥበብ ማለትም በዜማና ግጥም ደራሲነት፤ በፊልምና ቲያትር፣በድራማ፣በማስታወቂያና በርካታ ህዝብ በሚታደሙበት መድረኮች አጋፋሪነት፣እንዲሁም በጋዜጣና መጽሔት ውጤቶች አዘጋጅነት በቂ ልምድ ያካበተ የማስታወቂያ ባለሞያ እንደሆነ በተጨማሪም ባለሙያው ከተለያዩ የማስታወቂያ ድርጅቶች ጋር በማስታወቂያ ሀሳብ አመንጪነት፣በተራኪነት እና ሌሎች ግብዓቶችን በመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበረከት እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ለዚህም አበርክቶው ከፍተኛ አድናቆትና ክብር በማሕበረሰባችን ዘንድ የተቸረው በመሆኑ፣በህዝብ ዘንድ በተለይም በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቀባይነቱ እየጨመረ፤ዝነኛ ከሚባሉ ጥቂት ግለሰቦች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ እንደሆነ አሳውቀዋል፡፡
በመጨረሻም አቶ መሐመድ ፈረጅ ይኸንን ሙያዊ ልምድ እና ማኅበረሰባዊ ተቀባይነቱን በመጠቀም፤ የባንካችንን ሥምና ገፅታ ከዚህ በላቀ ደረጃ እንደሚያገዝፈው እንደሚተማመኑ በመግለጽ መልክታቸውን አጠናቀዋል፡፡
Leave a Reply