ለኢትዮጵያውያን፣ አደይ አበባ ዐዲስ ዓመት እና ዐዲስ የስኬት መንገድ!

ለኢትዮጵያውያን፣ አደይ አበባ ዐዲስ ዓመት እና ዐዲስ  የስኬት መንገድ!

ዘመን ዘመንን ሊተካ፣ ዓመት ዓመትን ሊወርስ በሰዓታት ምጥ፣ በቀናት መወለድና በወራት ዕድገት ንጹሕ መንፈስና ተስፋ፣ ዐዲስ ማንነትና ዐቅም ልንላበስ ጥቂት ጊዜያት ቀሩን፡፡ የዘመን ብሥራት ባለፉት ጊዜያት የቁጭት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ያለመቻል ስሜቶችን አራግፎ እንደ ንሥር ዐዲስ ገላን እያላበሰ ትኩስ ኃይልን ሊሰጠን ዐዲስ ዓመት ደረሰ፡፡ እንኳን አደረሳችኹ!

በብቸኝነት ዐሥራ ሦስት ውብ የፀሐይ ወራትን የታደለች ኢትዮጵያ፣ በሦስት ወራት ክረምት መልክአ ምድሯን አረስርሳ በእንቡጥ የልጃገረዶች መረዋ ድምፅ “አበባ አየሽ ወይ” እያስባለች የዘመን መለወጥን ታበስረናለች፡፡ የዐዲስ ዓመት መባቻ የሚታወሰው ምድር ስትለመልም፣ ተራሮችና ኮረብቶች፤ ሸለቆና ሜዳዎች በአደይ አበባ ሲደምቁ፣ ሲፈኩ ነው፡፡ አደይ አበባ ዐዲስ ዓመት አንድ ብሎ ሲጀምር በቢጫ ቀለማት፣ በአረንጓዴ ቅጠሏ ደምቃ በመታየት ለኢትዮጵያውያን የተስፋ፣ የልምላሜ፣ የሰላም ምኞትን ታላብሳለች፡፡

አደይ አበባ እና አቢሲንያ ባንክ

ባንካችን ከቀደምት የኢትዮጵያ መጠሪያ “አቢሲንያ”፣ ስያሜውን ብቻ ሳይኾን ግብሩን በመውረስ ያኔ ኢትዮጵያ በተጓዘችባቸው የሥልጣኔ መንገድ ሐዲዱን በመዘርጋት በባንክ ቴክኖሎጂ ከዘመኑ ጋር እየተጓዘ አኹን ድረስ ዘለቀ፡፡ በበርካታ ቅርንጫፎቹ፣ በተለያዩ የአገልግሎት አማራጮች፣ በዐዳዲስ አሠራር ከዘመኑ ጋር እየታደሰ በመምጣቱ በየዓመቱ ለስኬቱ የሚበረከቱለት ሽልማቶች ለድሉ ያቆማቸው ሐውልቶች ሕያው ምስክሮቹ ኾኑ፡፡ እንደጥንቱ አቢሲንያውያን ጠንካራቱና ጀግንነቱ መለያው ባሕርያት በማድረግ ከባንኩ ረድፍ ተወዳዳሩ ብቻ ሳይኾን ተመራጭ ለመኾን በቁ፡፡ ታዲያ ይኽን የልበ ሙሉነት መንፈስ በመጋራት ዓመት ዓመት ከተስፋው ጋር ዐብራው የምትጓዝ አደይ አበባ መለያው (Logo) ናት፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ብቻ የምትበቅለውን፣ ዐዲስ ተስፋን የምትሰጠውን፣ በባለ ስድስት መልከ አበቦች ያላትን አደይ አባባ ባሕርይዋን በመጋራት፣ አቢሲያን ውድ ደንበኞቹን ዐዳዲስ የተስፋ ጅማሮን በማብሰር በተሠማሩበት ዘርፍ ከጎናቸው በመቆም ከስኬት ጫፍ ዐብሯቸው ይዘልቃል፡፡ ቆራጥነትና ጠንክሮ መሥራት ዋናው ምልክቱ በማድረግ ባንካችን በተላበሰው አደይ አበባዊ ማንነት ዘላቂ ስኬት ያመጣል፡፡ በዐዲስ ዘመን ልምላሜን ያላብስ ዘንድ፣ እንደ አደይ አበባ በፈኩት ቅርንጫፎቹ፣ ከምንም ጊዜ በላይ ከደንበኞቹ ጎን በመድረስ ስኬትን በባዶ ተስፋ ሳይኾን በተጨባጭ ዐብረው ለሚሠሩት ያጎናጽፋል፡፡

ዐዲስ ዓመትን ከእኛ ጋር!

አብዛኞቻችን ከዘመን መለወጥ ጋር ራሳችንን በማላመድ ለዐዳዲስ ተግባር እንዘጋጃለን፡፡ ከዐዲስ ዓመት ጋር በዐዲስ ተስፋ ለመጋራት ያለፈውን ዓመት በኹለት መልኩ አሳልፈን ይኾናል፡፡ አንዳንዶቻችን ያለፈውን ዓመት በስኬት፣ በድል፣ ያሰብነውንና ያቀድነውን ያሳካንበት፣ ንግዳችን የሰመረበት፣ የመትረፍተፍ ዓመት በመኾን፤ ሌሎቻችን ደግሞ ስንፍና የነገሠበት፣ ከትርፍ ይልቅ ብዙ ኪሳራ ውስጥ የወደቅንት፣ አሳባችን፣ ውጥናችን እንዳይኾን የኾነበት፣ ንግዳችን የቁልቁት ጉዞውን ያፋጠነበትና በከንቱ ያሳለፍንበት ዓመት ይኾናል፡፡ እኛ አቢሲንያዎች ግን ዓመቱን በድል የተወጣንበት፣ ዘመኑን በትርፋማናትና በውጤታማነት ያጠናቀቅንበት፣ ከትጉኃኖች ጋር በመጓዝ 25ኛውን የስኬት ዓመታችንን የጨበጥንበት፣ ከአንድ የአገልግሎት መስጫ እስከ 600 በላይ ቅርንጫፎች፤ ከ31 እስከ 10 ሺሕ ሠራተኞች፤ ከ17 ሚሊዮን እስከ 9 ቢሊዮን በላይ ካፒታል የደረስንበት የመትረፍረፍ ጊዜ ነበር፡፡

ታዲያ! መጪውን ዓመት እንዴት ለማሳለፍ አስበዋል! ወደ ስኬት የሚያመጣዎትን መንገድ ለመቀየስ፣ ከአደይ አበባ ጋር መፍካት እንችል ዘንድ ከሁሉም ምርጫ ጋር ዐብሮ መሥራትን ውስኔዎ ያድርጉ! አቢሲንያ ዘመኑ ከደረሰባቸው ዐዳዲስ ዐሠራሮች ጋር ይጠብቆታል፡፡

ዐዲሱን ዓመት ግባ በለው!!!

ዘመኑ የስኬት፣ የሥራ፣ የሰላም ይኹን!

ምኒልክ ብርሃኑ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button