የአቢሲንያ ባንክ የ25 ዓመት ከፍታ ጉዞ!

የአቢሲንያ ባንክ የ25 ዓመት ከፍታ ጉዞ!

በወርኃ የካቲት 1906 ዓ.ም.፣ በጥንታዊ ኢትዮጵያ ስም “አቢሲንያ” ተሰይሞ በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የባንክ አገልግሎት አሐዱ አለ። ይኽ ታሪካዊ ባንክ እስከ 1931 ዓ.ም. ለ25 ዓመታት አቢሲንያ ባንክ እየተባለ ሲጠራ ቆይቷል፡፡  

ዛሬና ነን አሻግረው በተመለከቱ ልበ ብርሃኖች፣ በአገር ልማት ውስጥ ትልቅ አሻራን ሊያሳርፉና ለበርካቶች ዋርካ የሚኾን ተቋምን ሊመሠርቱ ብሩኅ ሕልም ዓለሙ። ይኽ ዕውን ይኾን ዘንድ፣ መውጣት መውረድ፤ መነሣት መውደቅን ያዙ። እንደ አራቱ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት፤ አራቱ ባለሕልሞች፡- አቶ ደበበ ሀ/ዮሐንስ፣ አቶ ነገዎ ደጀኔ፣ አቶ አዲስ አንተነህና አቶ በትሩ አድማሴ ባንክ የመፍጠርን አሳብ ፀነሱ።

ከግዙፉ የዕውን ጫፍ የመውጣት ጉዞን ሊያሠምሩ፣ በሕዝብ ልብ ውስጥ ሰተት ብሎ መግባትንና የመወደድ ዙፋን ላይ ለመቀመጥ እንዲያስችል አገርኛ ስያሜን በደበበ ሀብተ ዮሐንስ ፊታውራሪነት አፀደቁ። እነኾ ታሪክ ራሱን ሊደግም፣ በወርኃ የካቲት 1988 ዓ.ም. በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የተመሠረተውን የባንክ ስም ወርሶ፤ በ13 የመሥራች አባላት፣ በ17.8 ሚሊዮን ካፒታል፣ በአንድ ቅርንጫፍና በ32 ሠራተኞች “አቢሲንያ ባንክ” ዳግም ተወለደ።

በዚኽ 25 ዓመታት ውስጥ የተፈራረቁ የቦርዱ አመራሮች፣ ፕሬዝዳንቶችና ሥራ አስፈጻሚዎች በየዘመናቱ ያስቀመጡት የማዕዘን ድንጋይ አቢሲንያ ባንክ አኹን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።  በዚኽ ሒደት የባንኩ ፕሬዝዳንቶችና ሥራ አስፈጻሚዎች ከንግሥና ዘመናቸው በቅደም ተከተል እንዲኽ እንቃኘዋለን፤  

አቶ ተካልኝ ገዳሙ (ዋና ሥራ አስፈጻሚ) 1996-2002፣ አቶ ተክሌ ዓለምነህ (ፕሬዝዳንት) 2002-2003፣ አቶ ከበደ ተመስገን (ፕሬዝዳንት) 2003-2007፣ ወ/ሮ አሰለፈች ሙልጌታ (ፕሬዝዳንት) 2007-2008፣ አቶ ጫንያለው ይልማ (ፕሬዝዳንት) 2009፣ አቶ አዲሱ ሃባ (ፕሬዝዳንት) 2010-20014፣ አቶ ሙሉጌታ አስማረ (ዋና ሥራ አስፈጻሚ) 2014-2018 ፣ አቶ በቃሉ ዘለቀ (ዋና ሥራ አስፈጻሚ)  2019-አኹን ናቸው።

በባንካችን የሥራ አስፈጻሚነትና የቦርድ ሊቀ መንበርነት ሥራ ደርበው በመሥራት፣ ለረጅም ጊዜ በማገልገል ብቸኛ በመኾን አቶ ተካልኝ ገዳሙ በጉል ይታወሳሉ።

የሩብ ክፍለ ዘመን ጉዞ በቁጥር ስሌት ሲቃኝ፤

 • አጠቃላይ የሀብት መጠን 104,684,141,766.04
 • አጠቃላይ ብድር 77,357,565,538.30
 • አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 88,768,343,932.90
 • አጠቃላይ ካፒታል 9,154,165,325.57
 • ዓመታዊ አጠቃላይ ገቢ 9,867,002,029.12

ከትጉኃን መናኸርያ ወደ የ ሁሉም ምርጫ

አቢሲንያ ያሳለፍናቸው 25 ዓመታት አጠቃላይ ዕድገቱ ሽቅብ የወጣበት ይኹን እንጂ መንገዱ የአልጋ ላያ ጉዞ አልነበረም። ኾኖም ባንኩ የትጉኃን መናኸርያ በመኾኑ ነገን የመድረስ ግብ አንግቦ በጋሬጣዎች መሐል እያለፈ የኹሉም ምርጫ ለመኾን በቅቷል። ይኽም ከውስጥና ውጭ የገጠሙትን በርካታ ተግዳሮቶች በጠንካራ አመራርና በብርቱ ሠራተኞች ጥንካሬ ሰብሮ በኹሉም ረደግ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ዛሬ ላይ ወደ ደረሰበት አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

አገልግሎት በመስጠት ብር ማባዛት፤

አቢሲንያ የመጀመሪያው ቅርንጫፉን በቦሌ አካባቢ በመክፈት ወደ ሥራ አመራ። በየአምስት ዓመታት የቅርንጫፎቹን አድማስ እያሰፋ አኹን ከ600 በላይ በማድረግ ለሕብረተሰቡ በቅርበት መድረስ ችሏል። በ31 ሠራተኞች የተጀመረው የትጉኋን ጉዞ ወደ 10 ሺሕ ተጠግቷል። በመኾኑም የሥራ ታሪካቸው ከባንኩ ጋር የጀመረና በውጣ ውረዱ አብረው ያለፉ በርካታ ሠራተኞች ለባንኩ ሕልውና ጡባቸውን አኑረዋል።

ማኅበራዊ ሓላፊነት አገራዊ ግዴታችን

አቢሲንያ አገር ስትከፋ አብሮ ተከፍቷል፤ ስትደሰት ተደስቷል። ከልማቷ ጎን ተሰልፎ በሥራ ዕድል ፈጠራዎች ለብዙ ሺዎች ዋርካ ኾኗል። ያገኘውን የመወደድ ግርማ ሳያባክን በተለያዩ ማኅበራዊና አገራዊ ሓላፊነቶች በስፋት በመሳተፍና ከ145 ሚሊዮን በላይ ድጋፍ በማድረግ የወጣበትን ሕዝብ ክሷል።

በብዙ መሰናክሎች ሳይወድቁ የአገራችንን ኢትዮጵያ ስም ከፍ ላደረጉ ባለውለታዎች ቅርንጫፎቹን በስማቸው በመሰየም አበርክቷቸውን ለትውልድ እየዘከረ ማኅበራዊ ሓላፊነቱን ሲወጣ ከርሟል። በዚኽም ከ70 በላይ ቅርንጫፎቹን በአገር ባለውለታዎች ስም በመሰየም በባንክ ኢንደስትሪው ላይ በጎ ገጽታን ገንብቷል። የብድር አገልግሎት ከ120 ቢሊየን ብር በላይ ወደ ኢኮኖሚው አስገብቷል። በዚህም የውጭ ምንዛሬ ከፍ ባማድረግ፣ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ለአገራችን ትልቅ አስተዋጽዖን አድርጓል።

ከሌሎች ባንኮች የሚለየው

 • የትኩረት አቅጣጫውን ዲጂታላይዜሽን በማድረግ በአገራችን ካሉ ባንኮች በቀዳሚት የዲጂታል ንግድን በEcommerce የክፍያ አማራጭ አገልግሎትን መስጠቱ፤
 • ከቪዛ (Visa Inc.) ጋር የኤሌክትሮኒክ ንግድን (E-Commerce) ለማቀላጠፍ የቪዛ ሳይበር ሶርስ (Visa SyberSource Payment Gateway Technology) የኦንላይን ክፍያ አማራጭ ቴክኖሎጂን ማቅረቡ፤
 • ቅርንጫፎቹን ለአገር ትልቅ አበርክትዎ ባላቸው ባለውለታዎች ስም መሰየሙ፤
 • የ Virtual Banking Center በማዋቀር ቀዳሚ ባንክ በመኾኑ፤
 • አነስተኛ የንግድ ዘርፍ (Cultural Business Center) ላይ የተሠማሩ ተቋማት አቅርቦታቸውን በአገር ውስጥና በውጪ ገበያ ተወደዳሪ እንዲኾኑና አቅማቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ድጋፍ ማድረጉ
 • የአገልግሎት አሰጣጥ አድማሱን በማስፋት የብድር፣ የቁጠባ፣ የክፍያ አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ በተለያዩ አማራጮች ማቅረቡ ልዩ ያደርገዋለ።

የትጉኋን ልጆች ኹሌም ለአዳዲስ ተግባራት የተፋጠኑ ናቸው፤ አቢሲንያ ከዘመኑ ጋር በሚያደርገው ጉዞ፣ ሃምሳ ሎሚዎቻችን ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ።

ባለአክሲዮኖች፣ ክቡራን ደንበኞችና ሠራተኞቻችን እናመሰግናለን።

አቢሲንያ የኔ፣ ያንተ፣ የእናንተ የሁላችንም ምርጫ!

ምኒልክ ብርሃኑ (አርታዒ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button