ባንካችን የ“እችላለሁ!” የሽልማት መርሐ-ግብር የቤት መኪና ዕድለኛን ይፋ አደረገ

ባንካችን የ“እችላለሁ!” የሽልማት መርሐ-ግብር የቤት መኪና ዕድለኛን ይፋ አደረገ
  • የ2025 ቢ.ዋይ.ዲ ሴጉል መኪና ጅማ ገብታለች

ባንካችን አቢሲንያ ማርች 8 ን በማስመልከት ለ5ኛ ጊዜ ያከናወነውን የ“እችላለሁ (I CAN)” መርሐ-ግብር በማጠናቀቅ የ2025 ቢ.ዋይ.ዲ ሴጉል ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መኪና ሽልማት ዕጣ የማውጣት ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ሚያዚያ  22 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሎተሪ  አዳራሽ አከናውኗል።

ይህን የባንካችን የሥራ ሐላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ታዛቢዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙበትን  የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት የባንካችን ቺፍ ኤንተርፕራይዝ ሰርቪስ ኦፊሰር የሆኑት ወ/ሮ መሠረት አስፋው በይፋ አስጀምረዋል።

በወጣው ዕጣ መሠረትም ለደንበኞች ከተላኩት ከ2.3 ሚሊዮን በላይ የዕጣ ኩፖኖች መካከል የቢ.ዋይ.ዲ ሴጉል መኪና ሽልማት የሚያስገኘው የዕጣ ቁጥር 0609300000113 ሆኖ በመውጣት የባንካችንን የጅማ ዲስትሪክት ሄርማታ ቅርንጫፍ ደንበኛ ዶ/ር ቤተልሄም ይትባረክን ዕድለኛ አድርጓል።

የዕጣ ማውጣቱን ሥነ-ሥርዓት ተከትሎ ወ/ሮ መሠረት በመርሐ-ግብሩ የተመዘገቡ በርካታ ስኬቶችን የዘረዘሩ ሲሆን፣ ለአብነትም በደም እጥረት ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ በተደረገ ሃገር አቀፍ የደም ልገሳ 3,012 ዩኒት ደም ተሰብስቧል ብለዋል።

ወ/ሮ መሠረት አክለውም በሐዋሳ፣ ጅማ፣ ደሴ እና ባሕር ዳር በተካሄዱ የንግድ ትርዒቶች ላይ ከ450 በላይ ሴት ነጋዴዎች እንደተሳተፉ፣ ለ150 ሴቶች በፋይናንስ ዕውቀትና በንግድ አመራር ዙሪያ ተግባራዊ ሥልጠና መሰጠቱን እና 1,234 የንግድ ሐሳቦች ቀርበው ለተመረጡ 50 ሴቶች እስከ 25 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ያለመያዣ ብድር ለመስጠት ዝግጅት እንደተጠናቀቀ በዝርዝር ገልጸዋል።

በተጨማሪም በፈጠራ ውድድር የተሳተፉና እስከ 200,000 ብር የሚሸለሙ እንስቶች  እንደተለዩ የገለጹት ወ/ሮ መሠረት 72 እንስቶች ባንካችን በተለይም ለሴቶች የሚሰጣቸውን አደይ እና ዘህራህ የቁጠባ ሒሳብ አገልግሎቶች የሚያስተዋውቅ የፈጠራ ሐሳብ በቲክ ቶክ አጭር ቪዲዮ ሠርተው የላኩ ሲሆን፣ በዚህ ከብር 100,000 – 500,000 የሚደርስ ሽልማት በሚያስገኝ ውድድር በሁለቱም ዘርፎች 6 እንስቶች ተለይተዋል ብለዋል፡፡

ወ/ሮ መሠረት በመጨረሻም ይህ መርሐ-ግብር የተሳካ እንዲሆን ላደረጉ የባንካችን ሠራተኞች፣ አጋሮች እና በንቃት ለተሳተፉ እንስቶች ልባዊ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ከላይ በተዘረዘሩት የውድድር ዘርፎች ያሸነፉ እንስቶችም በቀጣይ በሚከናወን የመዝጊያ መርሐ-ግብር ላይ እንደሚሸለሙ ገልጸዋል፡፡

ባንካችን በቅርቡ አካሂዶት በነበረው “ከአቢሲንያ ባንክ ጋር ይጀምሩ – ያድሱ እና ይደጉ” የሽልማት መርሃ-ግብር የፍልውሃ ቅርንጫፍ ደንበኛና በከተማችን በአንድ የግል የህክምና ክሊኒክ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ዮሴፍ ገ/መድህን የሃዩንዳይ አክሰንት ሴዳን ዘመናዊ መኪና አሸናፊ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button