ባንኮች በተለይም በኢንቨስትመንት ውሳኔዎች፣ በብድር ድልድል እና በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ይህም ታዲያ በተለይ ማህበራዊ እና አካባቢያዊ ኃላፊነታቸውን ጉልህ ያደርገዋል።
በእርግጥ የባንኮች ዋነኛ ተግባር ለተጠቃሚው ህብረተሰብ አገልግሎት መስጠትና በዚህም ሂደት የባለአክሲዮኖችን ድርሻ ማሳደግ ነው። ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ከፍ ማለት፣ የተቆጣጣሪው አካል ክትትል እና የህብረተሰቡ ፍላጎት የባንኮች ሚና ከፋይናንስ አገልግሎት በላይ አንዲሆን እና ኃላፊነት የሚሰማው የባንክ አሰራር ስራ ላይ እንዲውል አስገድዷል።
ሌላው ምንም እንኳን ባንኮች በአካባቢ ጥበቃ ላይ በቀጥታ ተጽዕኖ ባይኖራቸውም፣ የፋይናንስ ውሳኔያቸው ግን ከፍተኛ የአካባቢ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል። ለምሳሌ ኃላፊነት ባለው የብድር አሰጣጥ ማለትም አካባቢን ለሚጎዱ ፕሮጀክቶች ብድር ባለመስጠት፣ ለአካባቢ ጥበቃ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ።
በተጨማሪም ባንኮች ብዙውን ጊዜ እንደ ትምህርት፣ ጤና እና የድንገተኛ አደጋ ልገሳዎች በመሳሰሉ የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ይሳተፋሉ። እነዚህ ተግባራት ደግሞ ለህብረተሰቡ ደህንነት ትልቅ አስተዋፅኦ ከማድረጋቸውም በላይ በባንኮች እና በሚያገለግሉት ማህበረሰብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ይረዳሉ።
የብዙ ሃገራት ብሔራዊ ፖሊሲዎች ባንኮች ከትርፋቸው የተወሰነውን ለማህበራዊ ሃላፊነት ተግባራት እንዲመድቡ የሚያስገድዱ ሲሆን በባንክ ሥራ ውስጥ ማህበራዊ ሃላፊነት ወደ ስልታዊ እና የተቀናጀ አካሄድ ተሸጋግሯል። በበጎ አድራጎት መዋጮ ብቻ ከመወሰን ይልቅም ማህበራው ሃላፊነት በዋና ዋና የአደጋ አመራር እና የረጅም ጊዜ ዕሴት ፈጠራ ውስጥ ተካትተዋል።
በመሆኑም ዛሬ ላይ የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነት ከበጎ አድራጎት ተግባር ወደ የባንክ ስራዎች ስትራቴጂካዊ አካል ተለውጦ የዘመናዊ የባንክ አገልግሎት አንዱ አካል ሆኗል። በኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ስርዓቶች ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ከግምት በማስገባት፣ ባንኮች ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለአካባቢ ጥበቃ … በአጠቃላይ ለህብረተሰብ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ በማድረግ ትልቅ ስራ እየሰሩ ነው።
በባንካችን አቢሲንያ ውስጥ ማህበራዊ ሃላፊነትን መወጣት እንደ ግዴታ ሳይሆን በቢዝነስ ፍልስፍናችን ውስጥ ያለ ቁልፍ ተቋማዊ ዕሴት ነው። ባንካችን የማህበረሰብን ደህንነት የልማት ቁልፍ አካል በሚያደርጉና ስነምግባርን ጠብቀው የሚከናወኑ ተግባራትን በቁርጠኝነት ይሰራል። እንዲሁም ቅድሚያ በሚሰጣቸው ሃገራዊ ፕሮጀክቶችና ድጋፍ በሚሹ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ላይ በንቃት በመሳተፍ የማህበረሰባችንን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል ቀጣይነት ያለው ልማት እንዲረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
አቢሲንያ ባንክ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ያለው ቁርጠኝነት በየጊዜው በሚያደርጋቸው የፋይናንስ ድጋፎች፣ ስትራቴጂክ አጋርነቶች እና ዘላቂ ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ ማህበረሰብ-ተኮር ፕሮግራሞች ላይ በሚያደርገው ተሳትፎ የሚገለጽ ነው። ሌላው ባንካችን ደንበኞች ለበጎ አድራጎት ድርጅቶችም ሆነ ለአስቸኳይ ጊዜ ድጋፋቸውን በቀላሉና ግልጽነት በተሞላበት አኳኋን እንዲያከናውኑ የኦንላየን የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕላትፎርም አዘጋጅቷል ።
ለአብነት ባንካችን በ2024/25 (እ.ኤ.አ) ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችሉትን የተለያዩና ቀጣይነት ላለው የማህበረሰብ ድጋፍ ለሚያግዙ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ከ96.96 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ ነበር። ከዛ ቀደም ብሎ በነበረው ዓመት ማለትም በ2023/24 (እ.ኤ.አ) ደግሞ ወደ 93.91 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለተለያዩ ህብረተሰባችንን ለሚያግዙ ፕሮጀክቶች መድቦ ነበር።
ድጋፍ ከተደረገላቸው ዋና ዋና ሃገራዊ እና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ካላቸው ፕሮጀክቶች መካከል ለአበበች ጎበና የህጻናት መንደር፣ ለአዲስ አበባ መስተዳደር የቤቶች ግንባታና የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም፣ ለአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ ለዲቦራ ፋውንዴሽን፣ ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት፣ ለመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ሮተሪ ኢትዮጵያ፣ ሸገር ፓርክ ፕሮጀክት፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ፣ ለአሚን የተማሪዎች ሽልማት፣ ለባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ ለሙዳይ የበጎ አድራጎት ድርጅት … ወዘተ ይገኙበታል።
ከዚህም በተጨማሪ ባንካችን እንደ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፣ የኢትዮጵያ የቅርስ ባላደራ ማህበር፣ የፓርኪንሰን ህመምተኞች ድጋፍ ድርጅት፣ ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ፣ አዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት እና ሴክተራል ማህበር፣ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፌዴሬሽን እንዲሁም የሌሎች የተለያዩ የጤና፣ የልማትና የጸረ-ወባ ማህበራት ያሉ ታዋቂ የበጎ አድራጎትና የሙያ ማህበራት ጠንካራ አጋርና የላቀ ደረጃ አባል ነው።
ከአጋርነትም በተጨማሪ ባንካችን ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ወገኖችን ለመደገፍ ለሚያግዙ ብሄራዊና ሶሺዮ ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ያለማቋረጥ ልገሳውን አድርጓል። ከእነዚህ መካከል ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን፣ ለጤና ተቋማት ፣ ለተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች፣ ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ ለንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለድንገተኛና ሰብአዊ እርዳታ … ወዘተ ይገኙበታል።
ታዲያ ይህ የባንካችን በጎ ተግባር ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ዕውቅናን አስገኝቶለታል። ከዚህ ዕውቅና በተጨማሪ በዋናነት የማህበራዊ ሃላፊነት ለባንካችን በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት።
01. ጠንካራ ብራንድ/መልካም ገጽታ እና ስም
ማህበራዊ ሃላፊነት ማህበረሰባችን በባንካችን ላይ ጠንካራ ዕምነት እንዲኖረው ያደርጋል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ብዙውን ጊዜ ደንበኞች ለህብረተሰብ ደህንነት፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ስነምግባር የሚቆረቆሩ ተቋማት ምርጫቸው ስለሆኑ ነው።
02. የረጅም ጊዜ ደንበኞችን ለማፍራት
ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከራሳቸው ጋር የሚሄዱ ተመሳሳይ ዕሴቶች ያሏቸውን ተቋማት ይመርጣሉ። በተለይም ማህበራዊ ሃላፊነት ደንበኞችን ከተራ ሸማችንት ወደ ዘላቂ ወይም የረጅም ጊዜ ደንበኝነት የሚለውጥ ነው።
03.ተወዳዳሪነትን ይጨምራል
በርካታ ተወዳዳሪዎች ባሉበት የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሃላፊነት የሚሰማው አሰራር የሚከተሉ ተቋማት ከሌሎች የተሻለ የገበያ ዕድል ይኖራቸዋል። የማህበራዊ ሃላፊነት ስራ ደግሞ አንዱን ባንክ ከሌላው የሚለየው እና በፍጹም ሊቀዳ ወይም ኮፒ ሊደረግ የማይችል የራሱ ቀለም ነው።
04. የሰራተኞች ፍልሰትን ይቀንሳል
ብዙ ጊዜ ሠራተኞች ማህበራዊ ሓላፊነቱን በሚገባ በሚወጣ ባንክ ውስጥ ተቀጥሮ በመስራቸው ኩራት ይሰማቸዋል። ይሄ ደግሞ የሰራተኞችን የስራ ተነሳሽነት፣ ሞራል እና ምርታማነት ከፍ በማድረግ የሰራተኞች ፍልሰት እንዲቀንስ ያደርጋል።
ከላይ በመጠኑ እንዳየነው ማህበራዊ ሃላፊነት ለባንካችን ከሚኖረው ጠቀሜታም በላይ በዋናነት ለህብረተሰባችን በትምህርት፣ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ … በአጠቃላይ ለኢኮኖሚ ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ አለው። በመሆኑም ባንካችንም የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል።
