ባንካችን በሁለተኛው ዙር 2026 ፊፋ ዓለም ዋንጫን አስመልክቶ ባዘጋጀው የሽልማት መርሀ ግብር የላፕቶፕ ዕድለኛ ለሆኑት ደንበኛ ዛሬ ሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም. ሽልማታቸውን አስረክቧል።
ባንካችን አቢሲንያ ዓለም አቀፍ የዲጂታል መክፈያ ሲስተም ከሆነው ቪዛ ጋር በመተባበር ደንበኞች የአቢሲንያ ቪዛ ካርድን ተጠቅመው ግብይት ሲፈጽሙ የ2026 ፊፋ ዓለም ዋንጫን በቀጥታ የመመልከት ዕድል የሚያስገኝ ታልቅ የሽልማት ፕሮግራም አዘጋጅቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ደማቅ የሽኝት ፕሮግራም ተደርጎላቸው ዕድለኛ ደንበኞቹም ጨዋታውን እየታደሙ ይገኛሉ፡፡
ሽልማቱ በሁለተኛ ምዕራፍ የቀጠለ ሲሆን ደንበኞች የአቢሲንያ ቪዛ ካርዳቸውን ተጠቅመው ሲገበያዩ የተቀላጠፈ ክፍያን ከመፈጸማቸው በተጨማሪ ከባንካችን በእጅ ስልካቸው የሚላክላቸውን ሊንክ ተጭነው ‘spin the wheel’ ጨዋታውን ሲጫወቱ ተጨማሪ ሽልማት በሚያስገኝላቸው መርሀ ግብር ከዚህ በፊት ሁለት ደንበኞችን ዘመናዊ ስልክ እና የ10,000 ብር ፕሪፔይድ ካርድ መሸለሙ ይታወሳል። በዋናው መሥሪያ ቤት የስብሰባ አዳራሽ በተደረገው የሽልማት ሥነ ስርዓት የመካከለኛው አዲስ ዲስትሪክት ሳር ቤት ቅርንጫፍ ደንበኛ የሆኑት አቶ ተምኪን አሊ የላፕቶፕ ተሸላሚ ሆነዋል። በፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የካርድ ባንኪንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንሙት ደሳለው መርሀ ግብሩ እስከ ሐምሌ 24 ቀን 2018 ዓ.ም. እንደሚቀጥል ገልጸው ደንበኞች ግብይት ሲፈጽሙ የአቢሲንያ ቪዛ ካርድን እንዲጠቀሙና ከባንካችን የሚላክላቸውን ሊንክ ተጭነው ዕድላቸውን በመሞከር እንደ ግብይታቸው መጠን ፍሪጅ፣ ላፕቶፕ፣ ዘመናዊ ስልክ እና እስከ 10,000 ብር የሚደርስ የፕሪፔይድ ካርድ ሽልማት ተካፋይ እንዲሆኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።



