ወለድ አልባ የብድር ጥያቄ በባንኮች እንዴት ይስተናገዳል?

ወለድ አልባ የብድር ጥያቄ በባንኮች እንዴት ይስተናገዳል?

የሀገራችን ባንኮች ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በቅርቡም ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች እንዲቋቋሙ በመንግሥት የተሰጠውን የማበረታቻ ውሣኔ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ  መመሪያ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ የሆነ የባንክ አገልጋሎት ለመስጠት ያቀዱ አክሲዮን ማኅበራት በምሥረታ ላይ ይገኛሉ ፡፡  ይህም በሀገራችን ከወለድ ነጻ የባንክ  አገልግሎት ተደራሽነትን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚረዳ ይታመናል፡፡

የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ከመጠሪያው ባሻገር መለያዎቹን እና  ያካተታቸውን ልዩ ልዩ ጥቅሞች እንዲሁም ተያያዝ ጉዳዮች እንደመኖራቸው ሁሉ ይህንኑ አስመልክቶ በርካታ ጥያቄዎች ከደንበኞች ይነሣሉ፡፡ በመሆኑም ስለአገልግሎቱ ለደንበኞች በዝርዝር በማሳወቅ በተጠቃሚነት ረገድ ለውሣኔ ማገዝ ያስችላሉ ያልናቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች በወፍ በረር ለመዳሰስ እንሞክራለን ፡፡

ወለድ አልባ የብድር አገልግሎትን ለመጠቀም ደንበኞች ሊያውቁት የሚገባ መሠረታዊ ነጥቦች

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት አሠጣጥ ከብሔራዊ ባንክ መመሪያ በተጨማሪ የሸሪዓን መርህንና ህግጋትን በማክበር እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ Islamic Financial Services Board (IFSB) የሚያወጣቸውን መስፈርቶችን ጭምር ተከትሎ  የሚሠራ ሲሆን፣ ከባንክ ባለሙያዎች በተጨማሪ ባንኮች ትልቅ ደረጃ ላይ በደረሱ ዑለማዎች የተዋቀረ የሼሪያ አማካሪ ቦርድ አቋቁመው እያንዳንዱ አገልግሎት/Product ሲቀረጽ ጀምሮ አማካሪ ቦርድ አባላት፣ እያንዳንዱ ነገር ሼሪያን የጠበቀ መሆኑን በማረጋገጥ ሀሳብ ሠጥተዉበት እየተማከሩና እየተቆጣጠሩት በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚተገበር ነው፡፡

በወለድ አልባ የብድር ውል ስምምነት መሠረት በቅድሚያ በመሸጫ ዋጋ ላይ ከባንኮች ጋር አንድ ጊዜ ስምምነት ከተፈጸመና የመሸጫ/ብድር ውል ከተፈረመ በኋላ፣ የመሸጫ ዋጋ ላይ ለመጨመር ወይም ለመቀነስ ምንም ዓይነት ድርድር የማይካሄድ ሲሆን ይህም፣ ከመደበኛው የብድር ሥርዓት የተለየ ያደርገዋል። በመደበኛው ብድር አፈጻጸም ረገድ በብሔራዊ ባንክ መመሪያም ሆነ በባንኮቹ ውሣኔ በማንኛውም ሁኔታና ወቅት የብድር ተመን ለውጥ ሊደረግ ከመቻሉም ሌላ በውል በተሰጡ ብድሮችም ላይ ጭምር የብድር ተመን ለውጥ ተፈጻሚ ሊደረግ ይችላል፡፡

በወለድ አልባ የብድር አገልግሎት፣ ደንበኞች የግብይቱን/የብድሩን ዋጋ አስቀድመው አውቀው በእርግጠኝነት  ውል እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል፡፡ ባልተጠበቁና ወደፊት ሊከሰቱ በሚችሉ ሁኔታዎች የውል ይዘቶች አለመቀየር በሸሪያው የሚደገፍ እንደመሆኑ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎቶች በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት አንዳንድ ሰዎች ከወለድ ነጻ የብድር እንዲሁም ሌሎች ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎቶች ለእስልምና እምነት ተከታዮች ብቻ የቀረበ አገልግሎት አድርገው ይወስዱታል። ይሁን እንጂ ከወለድ ጋር ምንም ንክኪ እንዲኖረው የማይፈልግ ወይም አገልግሎቱን/አሠራሩን የመረጠ ማንኛውም ደንበኛ ወደ ባንኮቹ በመቅረብ አገልግሎቶቹን ከማግኘት ወይም ከመጠቀም የሚያግደው ነገር የለም፡፡ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚቋቋሙት አዳዲስ ባንኮችን ጨምሮ ሌሎች ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎትን የሚሠጡ ተቋሞች፣ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ እንዲሁም አገልግሎት ሲቀርጹ ሁሉንም ደንበኛ አካታች በሆነ መልኩ እንዲሆን በማሰብ ሲሆን፣ ይህ አሠራር በእኛ ሀገር ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በሌሎች ሀገራትም የተለመደ አሠራር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ለዚህም አቢሲንያ ባንክን ጨምሮ ሌሎች ባንኮች ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ራሱን የቻለ ከመደበኛው የሒሳብ አስተዳደር ሥርዓት የተለየ (Segregated) የሒሳብ አስተዳደር ሥርዓት (IFB Books of Account & Accounting System)  ሲኖራቸው፣ እያንዳንዱ የሒሳብ እንቅስቃሴ ወይም ግብይት ተለይቶ የሚካሔድና የሚመዘገብ ይሆናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተወሰኑ ባንኮች በመስኮት ይሰጡት የነበረውን መስተንግዶ በማሳደግ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሠጡ ቅርንጫፎችን በመክፈት ላይ ይገኛሉ፡፡ (አቢሲንያ ባንክ 42 ከሚደርሱት ከወለድ ነፃ  አገልግሎት ከሚሠጡት ቅርንጫፎቹ፣ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሠጡት (Dedicated) ቅርንጫፎች 21 ደርሰዋል፡፡)

ከወለድ ነጻ ብድር የወለድ ምጣኔ አይታሰብበትም ሲባል፣ ባንኮች በምን መንገድ ጥቅም ሊያገኙ እንደሚችሉ ብዙዎች ይጠይቃሉ፡፡ አገልግሎቶቹ ከወለድ ነጻ ይሁኑ እንጂ ባንኮች ወጪያቸውን ሸፍነው ትርፍ ማምጣት ስለሚጠበቅባቸውም  ለሚሠጧቸው አገልግሎቶች የተለያዩ  ክፍያዎችን (Fees & Charges) ይጠይቃሉ፡፡ ሆኖም ተያያዥ የብድር ክፍያዎችም በመደበኛው የባንኮች ብድር አሠጣጥ ላይ እንደሚታየው ከባንክ ባንክ፣ ከዘርፍ ዘርፍ የተለያዩ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ሌላው መነሣት የሚኖርበት ጉዳይ ቢኖር ከወለድ ነጻ ብድር የሚስተናገድበት እንዲሁም ከመደበኛው የብድር አሠጣጥ የሚለይበት መርህ ይሆናል።  ከወለድ ነጻ የብድር አሠጣጥ ንብረትን ማዕከል ያደረገ (Asset base lending) ሲሆን ከወለድ ነጻ ረገድ የሚቀርቡ የብድር ጥያቄዎች እንደ መደበኛው የብድር አሠራር (Cash base lending) ቀጥታ ጥሬ ገንዘብ ከመስጠት ይልቅ ብድሩ የተፈለገበትንና የተጠየቀበትን ዓላማ እንዲሳካ ማድርግ ላይ ያለመ ነው፡፡ ይህም የተፈለገውን ነገር (የማምረቻ ማሽን ወይም የፋብሪካ ጥሬ ዕቃ ሊሆን ይችላል) ቀጥታ ለአቅራቢው በመክፈልና በመግዛት እንዲሟላ ይደረጋል ፡፡ ይህ በአመዛኙ ያለው አፈጻጸም ይሁን እንጂ ቀጥታ በጥሬ ገንዘብ ተከፋይ የሚሆኑ እንደ ቃርድ/Qard ዓይነት የብድር አገልግሎቶች አሉ፡፡

ሌላው ከወለድ ነጻ ብድር ረገድ ሊሠመርበት የሚገባው የብድር ትንተናና ግምገማ ጥልቀትና ስፋቱ እንደ ብድሩ ዓይነትና መጠን እንዲሁም ድርጅቱ እንደሚገኝበት ዘርፍ የሚለያይ ቢሆንም ተበዳሪው ለተበደረው ገንዘብ ዋስትና ወይም ብድሩ ስለመከፈሉ መተማመኛ የሚያስይዘው የብድር መያዣ(Collateral) ማቅረብን ጨምሮ ሌሎች ለመደበኛው የብድር ጥያቄ መመዘኛ የተቀመጡ መሠረታዊ መስፈርቶችና ቅድመ ሁኔታዎች ተፈጻሚ  ይሆናሉ፡፡

ከወለድ ነጻ ብድር የሚሠጥባቸው ዘርፎች በሸሪዓው ሕግ ክልክላ ያልተደረገባቸው መሆናቸው ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ የአልኮል መጠጥ አምራች፣ የአሣማ ሥጋ ማቀነባበሪያ እና እርባታ፣ የቁማር ጨዋታ ሰጪ፣ የጦር መሣሪያ እና የመሳሰሉት ዘርፎች በባንኮቹ ከወለድ ነጻ አገልግሎት አማካኝ የማይስተናገዱና አገልግሎት የማያገኙ ናቸው ፡፡

ወለድ አልባ የብድር አገልግሎት ዓይነቶች

ሙራባሀ / Murabahah

በአሁኑ ወቅት በርካታ ባንኮች የሙራባሀ / Murabahah ብድር አገልግሎትን በስፋት ሥራ ላይ ያዋሉ ሲሆን በብድር ውል መሠረት በቀጥታ ከሻጭ ወይም ከአቅራቢ ላይ ንብረት/ሸቀጥ/ ለተበዳሪው በመግዛት ወዲያውኑ/በተራዘመ ክፍያ( Differed Payment) የግዥ ዋጋው ላይ ትርፍን (Mark-up) በመጨመር ለደንበኛው የሚሸጡበት ወይም የሚያስተላልፉበት የአፈጻጸም ስምምነት ያለው የብድር አገልግሎት ነው፡፡

ባንኩ 2 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው የማምረቻ ማሽን እንዲገዛለት ተፈላጊ ሠነዶችን በሟሟላት ደንበኛው የብድር ጥያቄ ቢያቀርብ ባንኩ  2 ሚሊዮን ብር የሚደርሰው የግዥ ዋጋ ላይ ያዋጣኛል ያለውንና ከደንበኛው ጋር ስምምነት የደረሰበትን ታሳቢ የትርፍ መጠን ብር 120ሺህ ቢሆን፣ የብድር ውሉ ስምምነት (Contract) የሚፈረመው በብር 2,120 ሺህ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ባንኩ ትርፉን በቅድሚያ ሊሰበስብ የሚችልበት አሠራር እንዳለ ሲታወቅ የሙራባሀ ብድር ውል የቃል ስምምነትን እንዲሁም ውክልናን ጨምሮ የተለያዩ ደረጃዎችን በማለፍ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

ባንኮች የሙራባሀ / Murabahah የብድር አገልግሎትን በመጠቀም ለተለያዩ ዘርፎች የብድር አማራጮችን ያቀርባሉ፡፡ በዚህ ረገድ ከባንክ ባንክ የብድር አገልግሎት ብዛትና ዓይነት በተወሰነ ደረጃ ሊለያይ ቢችልም አብዛኞቹ ከወለድ ነጻ የብድር አገልግሎት የሚሠጡ ባንኮች ለማምረቻ መሣሪያዎች፣ ለፋብሪካ ጥሬ ዕቃ ግዥ፣ለሕንጻና ለቤት ግንባታ፣ ለሌተር ኦፍ ክሬዲት ዋስትናና ለውጭ ንግድ፣ ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችና ለእርሻ ሥራዎች፣ እንዲሁም ለመኪና ግዥ እና ለዳያስፖራ የሚውል የብድር አቅርቦት አመቻችተዋል፡፡

በሙራባሀ / Murabahah የብድር አገልግሎት አፈጻጸም ረገድ ግዥው በሁለት መንገዶች ሊፈጸም የሚችልበት አሠራር ያለ ሲሆን አንደኛው ብድሩን በመጠቀም ግዥው ቀጥታ ለደንበኛው በስሙ ሲከናወን፣ ሌላኛው  ደግሞ ባንኮቹ የተፈለገውን ንብረት በራሳቸው ስም ከገዙና የንብረቱ ባለቤት ሆነው ደንበኛው በስምምነቱ መሠረት ብድሩን ከፍሎ ሲጨርስ፣ የንብረቱ የባሌቤትነት መብትን  በሒደት ለተበዳሪው የሚተላለፍበት መንገድ ነው፡፡

በይዕ ሰላም/ Bai’ salam

የበይዕ ሰላም ብድር አገልግሎት አንድን ዕቃ፣ ሸቀጥ(Commodity) በቅድሚያ ክፍያ አማካኝነት ለደንበኛው የሚገዛበትና የሚሸጥበት ሲሆን የዕቃው ዓይነት፣ ብዛት፣ ዕቃው የሚረከብበት ቀን እና ቦታ በቅድሚያ ተጠቅሶና ስምምነት ተደርጎ የሚከናወን ከወለድ ነጻ የብድር አገልግሎት አፈጻጸም ነው፡፡

ሙሻረካ እና ኢጃራ / Musharaka & Ijarah

ሙሻረካ እና ኢጃራ ከወለድ ነጻ የብድር አገልግሎት ባንኮች የተበዳሪው አጋር(Partner) በመሆንና ከተበዳሪው ጋር የትርፍ እና ኪሣራ የመጋራት ስምምነትን በማድረግ ገንዘብ የሚያበድሩበት እና ትርፍ/ኪሣራ የሚጋሩበት አሠራር ነው፡፡ የሙሻረካ እና ኢጃራ ከወለድ ነጻ የብድር አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በብዛት እየተሠራበት ባይሆንም ተጠያቂ የሆኑት የሕግ ክፍተቶች ላይ ተገቢ ማስተካከያዎች ከተደረጉ በቅርቡ በጥቅም ላይ እንደሚውል ይታመናል፡፡

አለማየሁ ስሜነህ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button