ባንካችን አቢሲንያ ትናንት ሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም የደንበኞች የዕውቅና እና የምስጋና ቀንን ምክንያት በማድረግ ረጅም ጊዜ አብረውት የሰሩ ደንበኞቹን እና አጋሮቹን በመሸለም እና ዕውቅና በመስጠት በሸራተን አዲስ በደማቅ ዝግጅት አከበረ።
በፕሮግራሙ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባንካችን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በቃሉ ዘለቀ “የዝግጅቱ ዓላማ ባንካችን ከደንበኞቹ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማጠናከር፣ ለአስተዋፅኦዋቸው ምስጋና ማቅረብና ለስኬታችን የላቀ ድርሻ ላበረከቱ ደንበኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ደግሞ ተገቢውን ተቋማዊ ዕውቅና መስጠት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለውም “እኛን ምርጫችሁ አድርጋችሁ ስለታመናችሁን፣ ይበልጥ እንድንሻሻልና እንድንዘምን ስላበረታታችሁን እና ሁልጊዜም ከጎናችን ስለቆማችሁ ለእናንተ ደንበኞቻችን ያለኝን የላቀ ምስጋና አቀርባለሁ” ብለዋል።
በመድረኩ ላይ ከ400 በላይ የሚሆኑ ተቋማት በፕላቲኒየም፣ በጎልድ፣ በሲልቨር እና በፓርትነርሺፕ ደረጃ ተሸላሚ በመሆን ከባንካችን ስራ አስፈጻሚ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች እጅ የዕውቅና የምስክር ወረቀት እና የባንካችንን አርማ የያዘ ሽልማት ተቀብለዋል።
አንጋፋዎቹ የልማት ተቋማት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮም፣ እንደ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ያሉ የሚዲያ ተቋማት፣ የክልል ተቋማት፣መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ እንደ አፍሪካ ህብረት ያሉ አህጉራዊ ተቋማት፣ ኤምባሲዎች፣ የተለያዩ የንግድ ድርጅቶች … ወዘተ ከተሸላሚዎቹ መካከል ይገኙበታል።
ከባንካችን ጋር የሚሰሩ የተለያዩ ተቋማት ምስክርነት፣ በአንጋፋው ከያኒ ጌትነት እንየው የቀረበ ግጥም እና በመሳሪያ የተቀነባበረ ሙዚቃ ከዝግጅቱ ሁነቶች መካከል ጥቂቶቹ ነበሩ።
በዚህ ደማቅ ሥነ-ሥርዓት ላይ የባንካችን የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የበላይ ሥራ አመራር አባላት፣ ለባንካችን ስኬት ልዩ አስተዋፅኦ ያደረጉ ደንበኞችና አጋር አካላት እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።












