በመመሪያ ቁጥር 1047/2017 ለህዝብ የሚሸጡ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን ግዑዝ-አልባ ማድረግ፣ ክፍል 3 ግዑዝ አልባ የማድረግ ሂደት፣ አንቀጽ 6 ግዑዝ አልባ በማድረግ ሂደት ውስጥ ስለሚደረግ የመረጃ ልውውጥ መሠረት ሰነደ ሙዓለ ንዋይ አውጪዎች ለሁሉም የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ያዦች በዚህ መመሪያ ውስጥ ስለተቀመጡ መስፈርቶች፣ ግዑዝ አልባ የማድረግ ሂደትን፣ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮቻቸውን ግዑዝ አልባ የማድረግ ሂደትን እንዲጀምሩ እና በተጠየቁ ጊዜ ግዑዝ አልባ የማድረግ ሂደቱ ያለበትን ሁኔታ ማሳወቅ አለባቸው፡፡ ስለሆነም፡-
- ለህዝብ ሽያጭ የሚቀርቡ እና በአውጪዎቻቸው ፈቃድ ለሰነደ ሙዓለ ንዋዮች አስቀማጭ እና ክፍያ አጣሪና ፈጻሚ አገልግሎት ሰጪ የማስተላለፍ ውክልና የተሰጡ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግዑዝ አልባ መደረግ እና በማዕከላዊ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግምጃ ቤት መመዝገብ አለባቸው፡፡
- ከላይ እንደተገለጸው የተመዘገቡት ለህዝብ ሽያጭ የሚቀርቡ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች በባለስልጣኑ እስኪመዘገቡ ድረስ በማዕከላዊ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግምጃ ቤት መመዝገቡም ሆነ ለግብይት መቅረብ የለባቸውም፡፡
- ግዑዝ አልባ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ሕጋዊ ተቀባይነት ያላቸው ትክክለኛ እና ተፈፃሚ የገንዘብ ሰነዶች ናቸው፡፡
- የግዑዝ አልባ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ባለቤትነት በማዕከላዊ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግምጃ ቤት በተያዘ የኤሌክትሮኒክ መዝገብ መረጋገጥ አለበት፡፡
- የግዑዝ አልባ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች የባለቤትነት ዝውውር የሚደረገው በማዕከላዊ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግምጃ ቤት ውስጥ በሚደረግ የኤሌክትሮኒክ የምዝገባ ደብተር አማካኝነት ነው፡፡
- በማዕከላዊ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግምጃ ቤት የተያዘው የኤሌክትሮኒክ መዝገብ የባለአክሲዮኖችን መለያ ዝርዝሮችን፣ በየሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ያዥ የወጡ እና የተያዙ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን መጠን እና በሰነደ ሙዓለ ንዋይ አስቀማጭ እና ክፍያ አጣሪ አገልግሎት ሰጪ ህግ የሚጠየቁ ሌሎች መረጃዎችን በመመዝገብ ህጋዊ የባለቤትነት መረጃ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡
- በአንድ መደብ፣ አይነት እና መብት ይዘው በአንድ አውጪ የወጡ ግዑዝ አልባ የተደረጉ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ዋጋቸው ሳይነካ አንዱ በሌላው ሊተካ የሚችል “ተቀያያሪ/ተለዋዋጭ” ናቸው፡፡
- ከማስታረቅ ሂደቱ አስቀድሞ እያንዳንዱ አውጪ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ያዦችን በሙሉ የመገኛ አድራሻቸውን እንዲያሻሽሉ ማስታወቅ አለበት፡፡ አውጪው ለሰነደ ሙዓለ ንዋይ አስቀማጭ ግዑዝ አልባ እንዲደረግ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ መዝገቡን ከማቅረቡ አስቀድሞ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ያዦች በሙሉ የመገኛ አድራሻቸውን/በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን ግዑዝ አልባ ለማድረግ የተጠየቀውን መረጃ መስጠት/ማሻሻል አለባቸው፡፡
- ማንኛውም ሰው በቅድሚያ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ሂሣብ ሳይኖረው ተቀማጭ በተደረጉ ወይም ግዑዝ አልባ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን ለመግዛት ወይም ለመሸጥ ትዕዛዝ መስጠት አይችልም፡፡ የተፈቀደላቸው ሰነደ ሙዓለ ንዋይ አስቀማጭ አባሎች ለራሳቸውም ሆነ ለደንበኞቻቸው በማዕከላዊ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግምጃ ቤት ውስጥ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ሂሣብ መክፈት እና መያዝ አለባቸው፡፡
- የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ያዥ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ አስቀማጭ በውስጠ ደንቡ በሚገልጸው መሰረት ተቀባይነት ያለው የማንነት መግለጫን እና የደንበኛህን እወቅ መስፈርትን አካቶ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ሂሳብ መክፈቻ ቅጽ ከሞላ በኋላ በሰነደ ሙዓለ ንዋይ አስቀማጭ አባል በኩል የማዕከላዊ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ግምጃ ቤት ላይ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ሂሣብ መክፈት አለበት፡፡
- የማዕከላዊ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግምጃ ቤት ሂሳብ ከተከፈተ በኋላ እያንዳንዱ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ያዥ ግዑዛዊ የሆነውን የምስክር ወረቀት ወይም የሰነደ ሙዓለ ንዋይ የባለቤትነት ማረጋገጫውን በሰነደ ሙዓለ ንዋይ አስቀማጭ አባሉ የማስቀመጫ ቅጽ መሙላት እና የሰነደ ሙዓለ ንዋይ አስቀማጭ በውስጠ ደንቡ በሚገለጸው መሰረት ተቀባይነት ያለው የማንነት መግለጫን እና የደንበኛህን እወቅ መስፈርትን አሟልቶ ማቅረብ አለበት፡፡
- በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ያዡ በመያዣነት የተሰጡ የምስክር ወረቀቶች በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ያዡ ሂሳብ ውስጥ ገቢ ከመደረጋቸው በፊት የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ያዡ በመያዣነት የያዘውን አካል ጋር መመካከር አለበት፡፡
- ያልተከፈሉ እና በከፊል የተከፈሉ አክሲዮኖች ግዑዝ አልባ ሊደረጉ እና ወደ ማዕከላዊ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግምጃ ቤት ሂሣብ ገቢ ሊደረጉ የሚችሉት ሙሉ ለሙሉ ክፍያ ሲፈጸምባቸው ብቻ ነው፡፡
- ስህተቶችና ቅሬታዎች በተመለከተ አውጪው የቅሬታውን ወይም የስህተቱን የመጨረሻ ውሳኔ በ5 የስራ ቀናት ውስጥ ለባለስልጣኑ ማሳወቅ አለበት፡፡ ቅሬታው በ10 የስራ ቀናት ውስጥ ያልተፈታ እንደሆነ ወይም ቅሬታ አቅራቢው በአውጪው በተሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘ እንደሆነ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ያዡ አውጪው በሰጠው ውሳኔ ላይ ለባለስልጣኑ ይግባኝ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ለባለስልጣኑ የሚቀርበው ይግባኝ በቅሬታው የነበረውን ጠቅለል ያለ ሒደት እና አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች ቅጂን መያዝ ይኖርበታል፡፡
- ባለሥልጣኑ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች የግዑዝ-አልባነት ቀን ይፋ ካደረገ ከ10 ዓመት በኋላ፣ ግዑዝነት ባላቸው የምስክር ወረቀቶች የተወከሉ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች የይገባኛል ወይም መልሶ ይገባኛል ጥያቄ ያልቀረበባቸው እንደሆነ በባለሥልጣኑ በሚተዳደረው ልዩ ሒሳብ ገቢ ይደረጋሉ፡፡ በዚህ የተጠቀሱትን ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች በተመለከተ የይገባኛል ጥያቄ ለማቅረብ የሚፈልጉ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ያዦች የባለቤትነት ወይም የተጠቃሚነት ማስረጃቸውን ለባለሥልጣኑ በማቅረብ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮቹን ተመላሽ ማድረግ ይችላሉ፡፡
- የሰነደ ሙዓለ ንዋይ የምስክር ወረቀቶችን ግዑዝ አልባ ለማድረግ እምቢተኛ መሆን የተከለከለ ነው፡፡
አቢሲንያ ባንክ አ.ማ

Leave a Reply