፲ የፋይናንስ አቅማችንን የምናሳድግባቸው አማራጮች

፲ የፋይናንስ አቅማችንን የምናሳድግባቸው አማራጮች

ለአንድ የንግድ ድርጅት ጠንካራ ሥርዐትና (System) የሰው ኃይል የጀርባ አጥንት  ሊሆን ይችላል። ግን የፋይናንስ ዐቅሙ የተዳከመ ከሆነ ከባድ የሕልውና ሥጋት ውስጥ ይወድቃል። በዚህ የውድድር ዓለም ውስጥ ለመዝለቅ፤ ተመራጭና ተፈላጊ ሆኖ ለመቆየት ግዴታ የገንዘብ ዐቅምን ማሳደግ ይገባል። የፋይናንስ ዐቅማችንን ከምናሳድግባቸው መንገዶች ብዙዎች የሚስማሙባቸውን እነሆ።

፩. የፋይናንስ እቅድ ያዘጋጁ፤

ፋይናንስን ለመቆጣጠርና ግቦችን ለማሳካት የፋይናንስ እቅድ አስፈላጊ ነው። ይህ ከበጀት በተለየ መልኩ ረዘም ያለ ጊዜን ይሸፍናል። (በጀት የፋይናንስ እቅድ አካል ነው) የፋይናንስ እቅዶች በአንድ ወይም በሁለት የፋይናንስ ግቦች ላይ በማተኮር የበለጠ ውጤታማ እንድንሆን ያግዙናል። ኢንቨስት ማድረግ፣ አክስዮን መግዛት፣ ተጨማሪ ድርጅት መክፈት፣ የመሳሰሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ።

፪. ኢንቨስት ያድርጉ፤

ገንዘብ ለማግኘት ሁለት መንገዶች አሉ፤ ሥራ በመሥራትና ገንዘባችን በአክሲዮን፣ ቦንዶችን በመግዛት ወይም ኢንቨስት በማድረግ። ኢንቨስት ማድረግ አደጋዎች አብሮ የሚያመጣ ቢሆንም፣ ትርፍን በማሳደግ ኪሳራን ለመገደብ ይረዳል።

፫. አዳዲስ የግብይት ዘዴዎችን ተጠቀሙ፤

በንግድ ላይ ተጨማሪ ጥረት ለማድረግ የግድ ተጨማሪ ገንዘብ ማውጣት አይጠይቅም። ግን በትንሽ ወጪ ብዙ ማትረፍ የሚያስችሉ ስልቶችን መንደፍ ይጠይቃል። ከተለመደው አሠራር በመላቀቅ አዳዲስ የግብይት ዘዴዎችን በመጠቀም ገቢያችንን ማሳደግ እንችላለን፤ በይነ መረብን፣ ማኅበራዊ ሚዲያን ወዘተ.መጠቀም ከነዚህ ዘዴዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

፬. ወጪና ገቢን ይቆጣጠሩ፤

ከሚያገኙት በላይ ወጪ የሚያወጡ ከሆነ ወደፊት መራመድ አይችሉም፤ የፋይናንስ ሒደቱም ወደ ችግር ሊያመራ ይችላል። ስለዚህ ፋይናንስን ለመቆጣጠር ወጪን ለአንድ ወይም ለሁለት ወር መከታተል የሚያስችል በጀት መፍጠር ይችላሉ። በተለምዶ በሚያገኙትና በሚያወጡት የገንዘብ መጠን ላይ በመመሥረት የወደፊት የፋይናንስ ሁኔታን ለመለወጥ ይረዳል።

፭. ወጪዎን ለአንድ ወር ይከታተሉ፤

ወጪን መከታተል የፋይናንስ መሠረታዊ ተግባር ነው። እንዴትና ለምን ገንዘብዎን እንደሚያወጡ ለማወቅ፤ ትርጉም ባለው መንገድ ወጪዎትን እንዲያውሉ (ለክፍያ፣ ምግብ፣ መጓጓዣ፣ መዝናኛ፣ ወዘተ) ይረዳዎታል። በወሩ መገባደጃ ጠቅላላ ወጪዎትን ያስሉ፤ ይህን በማድረግ አላስፈላጊ ወጪን እንደሚቀንሱና ተጨማሪ ገንዘብ ምን ላይ እንደሚያወጡ ያውቃሉ።

፮. ቀደም ብለው መቆጠብ ይጀምሩ፤

ቁጠባ በተወሰነ የጊዜ ገደብ የማያወጡትና ጥቅም ላይ የሚውል የገቢ መጠን ነው። የዓመት ገቢዎን አስሉ፤ ከገቢዎ ለቁጠባ ይክፈሉ፤ የቁጠባ መጠንዎን በየዓመቱ ለመጨመር ይሞክሩ። ለቁጠባ ግቦችን ያዘጋጁ። መቆጠብ ካልቻሉና በቁጠባ ላይ በቋሚነት ካልሰሩ አስቸጋሪ ጊዜያቶች በብድር ሊያሳልፉ ይችላሉ። የቁጠባ ገንዘብ ያልተጠበቀ ጊዜ ለሚከሠት የፋይናንስ ችግር ጥሩ መተማመኛ ነው።

፯. እዳን በመክፈል እዳን ማደስ

በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ትልቁ ስሕተት ከፍተኛ ወለድ ባለው ዕዳ መያዝ ነው። የፋይናንስ አቅምን ለማሳደግ ሊደረጉ ከሚችሉ ነገሮች አንዱ እዳን መክፈል ነው። እዳዎትን መክፈል ከቻሉ ተጨማሪ የፋይናንስ እድሎችን ማግኘት ይችላሉ። ስለዚህ እዳዎትን ይዘርዝሩ፤ የእዳ ክፍያ ዕቅድ ያዘጋጁ፤ ከፍተኛ ወለድ ያላቸው ብድሮች በቅድሚያ ይክፈሉ። ዝቅተኛ ወለድ ያላቸውን ደግሞ ማደስ ይችላሉ።

፰. የፋይናንስ አፈጻጸምን (Financial Performance) ይጠቀሙ፤

የፋይናንስ አፈጻጸም አንድ ድርጅት ንብረቶቹን እንዴት እንደሚጠቀምና ገቢዎችን ማመንጨት እንደሚችል የሚያሳይ ነው። አጠቃላይ ስለድርጅቱ ደኅንነት ለማወቅ፤ እያከናወነ ስላለውና ስለወደፊቱ ግንዛቤን ለማግኘት፤ የአሠራሩ ሒደቱን፣ ትርፉ እያሳደገ ስለመሆኑ፣  ከተመሳሳይ ድርጅቶች ጋር ለማነጻጸር፤ የፋይናንስ አፈጻጸም የኢኮኖሚያዊ ደህንነት ለመወሰን፣ ለመከታተል እና ለመንደፍ የሚያገለግል ነው። በተለይም ኩባንያው ምን ያህል ጥሩ እየሠራ እንደሆነ፣ የድርጅቱ ጥንካሬዎችና ድክመቶች የት እንዳሉ ለመለየት እንደ መሣሪያ ያገለግላሉ።

፱.  የሥራ ችሎታዎን ያሻሽሉ፤

በንግዱ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስፈልጉት ክህሎቶች መቅሰም፤ መስኩ የደረሰበትን ዕውቀት ማወቅ፤ ብቁ የሚያደርግዎትን የተለያዩ ሥልጠናዎችን መውሰድ ገቢያችንን በማሻሻልና ምርጥ ሆኖ መቅረብ ያስችላል።

፲.  ባለሞያዎችን ያማክሩ፤

የገንዘብ ፍሰትዎን ለማሻሻልና የተሸሉ መንገዶችን ለመጠቀም እንዲሁም በፋይናንስ ግቦችና ስልቶች ላይ ስለሚያጋጥሙ አደጋዎች ባለሞያዎችን ያማክሩ።

እነዚህን የመሳሰሉት አማራጮችን በመጠቀም የፋይናንስ አቅምዎን ማሳደግ ይችላሉ፡፡

አቢሲንያ የሁሉም ምርጫ!

ምኒልክ ብርሃኑ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button