ማኅበራዊ ኃላፊነት ተፈጥሮአዊ ዕሴታችን፤

ማኅበራዊ ኃላፊነት ተፈጥሮአዊ ዕሴታችን፤

እንደ ሐረግ ለተጠላለፈው ኢትዮጵያዊ ማንነት፤ ክሩም፣ ማጉም አንድ ነው፡፡ በዚህ የአንድነት ማግ የተጠናከረው ኢትዮጵያዊነት፤ ዛሬ ያልተጀመሩ፣ በነገ የማይጠናቀቁ የብዙ ትላንቶች ባለቤት እና በማይሰበር ዐለት ላይ የተዋቀረ “አገር” እንድንሆን አድርጎናል፡፡

በዚህ ዓምድ የተገነባው ባንካችን፣ የቀድሞውን የኢትዮጵያን ስም በመዋስ በታላቋ አገር ታላቅ ተቋም ሆኖ ለመውጣት ከዛሬ 26 ዓመት በፊት “አቢሲንያ” በሚል ስም ተመሠረተ፡፡  መልካም ስም ከመልካም ተግባር ጋር ሲዋሐድ ሁሉ ይሠምራልና በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የነበሩ በርካታ ተግዳሮቶችን በመቋቋም አቢሲኒያ ባንክን ከፍ ከፍ ወዳለው ማማ ማውጣት ችለናል፡፡

ከታላቅ ስም ስንነሣ፤ ታላቅ የመሆን ዐላማና ግብ ሸክፈን በመሆኑ፤ በታላቅነት መለኪያዎች አገርን በመምሰል፣ አገርን በመውደድና አገርን በመከተል እንመዘናለን፡፡  

አገርን በመምሰል መመዘኛ፣ ታላላቆቻችንን ማክበር ዋነኛ ግዴታችን በመሆኑ፤ በተለያዩ መስኮች የኢትዮጵያ “ስም” ከፍ ብሎ እንዲጠራ ላደረጉ የአገር ባለውለታዎች ታሪካቸው ለልጅ ልጅ እንዲተላለፍና በሕያው መዝገብ ተሰንዶ እንዲቀመጥ በስማቸው ቅርንጫፍ በመክፈት አገርን መስለናል፡፡ ለሌሎች ተቋማትና ለአቻ ድርጅቶችም አርአያ በመሆን በግንባር በቀደምትነት ተጠቃሾች ነን፡፡

አገርን በመውደድ ፅንስ የተወለደው ባንካችን፤ ግዴታዎቹ ከራሱ ተፈጥሮአዊ ዕሴት የሚመነጩ ናቸው፡፡ እነኾ! ከምሥረታው ጀምሮ ላለፉት 26 ዓመታት በትጋትና በባለቤትነት ስሜት ማኅበራዊ ኃላፊነት ሲወጣ ቆይቷል፡፡

አቢሲንያ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምርጫ እንደ መሆኑ መጠን፤ ከመንግሥት፣ ከግብረ ሠናይ ድርጅቶች፣ ከልማት ማኅበራትና ግለሰቦች ለሚቀርቡለት የድጋፍ ጥያቄዎች በጎ ምላሽ በመስጠት አገርን የመውደድ ውዴታውን ተወጥቷል፡፡

አገርን በመከተል የታላቅነት መለኪያ ደግሞ፤ ለአገር በመድከም እየሠሩ ከሚገኙ ተቋማት ጋር በመሰለፍና የክብር አባል በመሆን ውጥናቸው እንዲሳካ፣ ራእያቸው እንዲሠምር እያበረታቸው ይገኛል፡፡ የክብር አባል ከሆናቸው ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለ አደራ ማኅበርና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የሚጠቀሱ ሲኾኑ፤ የተቋቋሙበትን ዐላማ በመደገፍና ቋሚ ዓመታዊ የአባልነት መዋጮ በማዋጣት ተጨማሪ ድጋፎች ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህ ዓመትም አገርን በመውደድ ለሚጥር “የሜሪጆይ ኢትዮጵያ” ግብረ ሰናይ ድርጅት የክብር አባል በመሆን አገርን ሆኗል፡፡

አቢሲንያ አገራዊ ድርሻና ኃላፊነት፣ የአገር ልጅ በመሆን የሚገኝ መሆኑን በማመን በአጠቃላይ  ባሳለፍነው ዓመት ለተለያዩ የድጋፎች ለቀረቡለት ጥያቄዎች ከብር 30 ሚሊዮን በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከመንግሥትና የመንግሥት ተቋማት ብር 20.1 ሚሊዮን በላይ፤ በትምህርትና ጤና ዘርፍ የተደረገ ድጋፍ ብር 4.6 ሚሊዮን በላይ፤ ለቅርስና አካባቢ ጥበቃ ከብር 2.1 ሚሊዮን በላይ፤ ለግብረ ሠናይ ድርጅቶች ከብር 800 ሺህ በላይ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከተደረገው ከፍተኛ ድጋፍ በተጨማሪ ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ ከብር 2.6 ሚሊዮን በላይ ድጋፍ በማድረግ በጎ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ለአገር መድከምና ለአገር መሥራት ተፈጥሮአዊ ዕሴታችን፣ ማኅበራዊ ግዴታችን በመሆኑ በቀጣይም በአገር እድገት ላይ አስተዋጽዖ በሚያደርጉ፣ ቅርስና አካባቢ ጥበቃ ላይ በሚያተኩሩ፣ የተለያየ በጎ ዐላማን አንግበው ከሚንቀሳቀሱ ተቋማትና ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ጎን በመሰለፍ ድርሻውን ይወጣል፡፡

ውድ ደንበኞቻችን! አቢሲንያ የሁሉጊዜ ምርጫሁ ባንክ ስላደረጋችሁት ከልብ እናመሰግናለን፡፡

አቢሲንያ የሁሉም ምርጫ!

ምኒልክ ብርሃኑ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button