የግል ገቢና ወጪያችንን እንዴት እናመጣጥን?

የግል ገቢና ወጪያችንን እንዴት እናመጣጥን?

ብዙዎቻችን በስም ለምናውቀውና በተደጋጋሚ ለምንሰማው ቃል እንግዳ አይደለንም፤ የምናውቀው ስለሚመስለን ደግሞ ለጉዳዩ ያለን ትኩረት ይቀንሳል፡፡ ግን ጉዳዩ ከምንም በላይ የሚያስፈልገንና የሚገባን ሆኖ ስናገኘውስ… ቅርባችን የኾነው ሩቅ ይኾንብናል፡፡ ዛሬ ላይ ቅርባችን የኾነውንና የበለጠ በቅርበት ልናጤነው ስለሚገባን ጉዳይ ልናወጋችሁ ወደድን፡፡

እንደምንተነፍሰው አየር በማይቀር የሕይወት ሕግ ውስጥ ኹላችንም በጉዳዩ ላይ አለንበት፡፡ ለተቀመጠው ለሚሮጠው፤ ለምንደኛውም (ለደሞዝተኛው) ለባለሀብቱም ከዚኽ ሕግ ውጪ አይኾንም፡፡ በጀት፣ የገቢና የወጪ ስሌት፡፡ የምናገኘው ገቢ ለብዙ ነገር የሚካፈል ነው፡፡ ለሚያስፈልገንና ለምንፈልገው፣ ለምንከፍለው (ብድር፣ ዕዳ)ና ለምቆጥበው፡፡ በጀት ገቢና ወጪያችንን በተገቢው ሥርዐት እንድናስኬድ የሚያግዘን ነው፡፡ ጊዜ ጠብቀን በምናገኘው ገቢ ለቤት ኪራይ፣ ለምግብ፣ ለትምህርት፣ ለትርንስፖርት፣ ለልብስ፣ ለመዝናናት ወዘተ. የሚውል ነው፡፡ በዚኽ የገቢና ወጪ ሒደት ውስጥ በጀት የምናገኘውን ገንዘብ እቅድ እንድናወጣበት የሚያደርግ ረድእ (ረዳታችን) ነው፡፡  

ገንዘብ እንደ የምንተነፍሰው አየር ነው፡፡ ሁላችንም ብንኾን የምናስወጣውና የምናስገባው አየር ባልተመጠነ ልክ፣ የአተነፋፈስ ሥርዐታችን ይዛባል፡፡ የምናገኘው ገቢ ከወጪያችን ማመጣጠን ካልተቻለ ወይ በዕዳ ውስጥ እንዘፈቃለን፤ አልያም ማጣት እየናጠን በሰቀቀን እንቆያለን፡፡ ግን ሁሉም ሥርዐት አለውና ገቢና ወጪያችን የምንመጥንበት ሥርዐት እናበጅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል?

የገቢና ወጪ ሥርዐታችንን ለማበጀት ከምንም ጊዜ በላይ በዕቅድ መኖርን ልማድ ማድረግ ግድ ይለናል፡፡ ከእንቅልፍ ስንነሣ ፊታችን ውኃ እንደማይቀርበት ሁሉ፣ ገንዘባችንም ላይ የምናደርገውን ነገሮች ሕግን (ዕቅድን) በማበጀት ልማድ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ምክንያቱም ገንዘብ ለማግኘት የምንፈጀው ማንኛውም ጊዜ ከእድሜአችን የሚቀነስ ነው፡፡ በጊዜ የተቀነሰው እድሜ ተሰልቶ የሚመጣው ገንዘብ/ብር አግባብ ላይ ካልዋለ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን እድሜም እንደባከነ ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ እድሜአችንን ገብረን ያገኘነውን ገንዘብ ገቢና ወጪን ለማስላት በጀት መላ ነው፡፡ በጀት ደግሞ በጭንቀት የምንኖርበትን ሕይወት በመቀነስ በገንዘባችን በነጻነት እንድንኖር ያደርገናል፡፡ በጣም ቀላል ነው……

እንዲህ ብናደርግስ…..

  • ከተለያየ ቋት በየቀኑ፣ በየሳምንቱና በየወሩ የምናገኘውን ገንዘብ እናስላ፤
  • ዐላማ ያለው ሰው ልጓም እንደተበጀለት ፈረስ የሚሔድበትን ያውቃልና ለምን ዐላማ በጀት ማዘጋጀት እንዳለብን እንወቅ፤ ምክንያቱም ብዙ ወጪ የምናወጣ ሰዎች ዐላማችንን ቀድመን ካስቀመጥን አላስፈላጊ ነገሮችን (ወጪዎችን) እንቀንሳለን፡፤
  • ቅድሚያ መስጠት ያለብንን ወጪዎቻችንና ለምን ዐላማ እንደምናወጣ እንለይ፡፡ ምክንያቱም የምንፈልገውንና የሚያስፈልገንን (NEED & WANT) መረዳት ካልቻልን የምናገኘው ገቢ የሚሸፍነውን ዐቅም ለማወቅ እንቸገራለን፡፡ ስለዚኽ በጀት በቀላሉ የምናገኘው ገንዘብ ዐቅሙን እንድናውቅ ይረዳናል፡፡
  • ከድንገተኛ ወጪዎች እንቆጠብ፤
  • የምናገኘውን ገቢ በ 50/30/20 ሕግ መሠረት ብናውለውስ፡፡ ሕጉ ቀላ ነው…  
  • 50% – መሠረታዊ/ቋሚ/ ለኾኑ ወጪዎች፣
  • 30% – መሠረታዊ/ቋሚ/ ላልኾኑ ወጪዎች፣
  • 20% – መልሰን ለምናገኘው ገቢ (ቁጠባ፣ ዕቁብ…).

ይኽን በማድረጋችን ገንዘባችን ምን ላይ እንደሚውል እናውቃለን፣ የሚባክነውን እንቀንሳለን፣ በተለይ ደግሞ በየጊዜው አልያም በየወሩ ለግባችንና ለዐላማችን ዛሬ ላይ እየሠራን እንደኾነ እንረዳለን፡፡ በቃ በጀት ይኽን ያኽል ቀላል ዘዴ ነው፡፡

  • በስተመጨረሻም በጀትን ባህላችን ማድረግና በማይቋረጥ ሒደት ውስጥ ልማዳችን እንዲኾን መጣር ያስፈልጋል እንላለን፡፡

አቢሲንያ የሁሉም ምርጫ!

አሠናኝ ምኒልክ ብርሃኑ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button