ክቡር አርቲስት ለማ ጉያ

ክቡር አርቲስት ለማ ጉያ

ኢትዮጵያ ባሕረ ጥበባት፤ የበርካታ ጠቢባን መፍለቂያ ማዕከል ናት። በየዘመናቱ የሚነሡ፣ ከአብራኳ የወጡ ልጆችዋ፣ ከፍ ካለው ክብሯ እኩል ስማቸውንና ስሟን ከፍ በማድረግ ታሪክ፣ ትውልድና ዘመን የማይሽረው አሻራ አኑረው ያልፋሉ። በጥንታዊቷ ይኹን በዘመናዊቷ የኢትዮጵያ ታሪክ ተከሥተው የራሳቸውን ጡብ ለማኖር ብቅ የሚሉ፣ በዐዳዲስ መንገድ እየመጡ የሚያስደምሙ የአገር ዕንቁዎችን አገራችን አጥታ ዐታውቅም፤ ወደፊትም አታጣም።

በሥነ ጽሑፍ፣ በኪነ ሕንፃ፣ በሥነ ሥዕል፣ በሩጫ፣ በሙዚቃ ወዘተ. በተለያዩ ዘርፎች ኢትዮጵያን ያከበሩ፣ ኢትዮጵያም እያከበረቻቸው የሚገኙ በርካታ የአገር ባለውለታዎች አሏት። አቢሲንያ ባንክ እነዚህን የዘመን ክሥተቶች ቤዛነታቸውንና ዐርአያነታቸውን ማክበር ቀዳሚው ተግባሩ ነው።

ክቡር አርቲስት ለማ ጉያ ከአባታቸው ጉያ ገመዳና ከእናታቸው ማሬ ጎበና በደብረ ዘይት ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ፣ አድአ ሊበን ወረዳ ደሎ በምትባል ቀበሌ ነሐሴ ፲፪ ቀን፣ በ፲፱፻፳፩ ዓ.ም. ተወለዱ። የእርሳቸውን ማንነት ሊቀርፅ የሚችለውን ፈለግ፣ የሸክላ ጥበብ ባለሙያ ከሆኑት እናታቸው ወ/ሮ ማሬ እግር ሥር ቁጢጥ ብለው እየተማሩ የቅርፃ ቅርፅ እና የሥዕል ጥበብን እየተማሩ አደጉ። በጊዜው እንደልጅነት በጭቃ ከመጫወት ይልቅ የውስጥ ፍላጎታቸውን ሊገልጽ የሚችሉ የሰው፣ የእንስሳትና ሌሎች ቅርፃ ቅርፅን በመሥራት ብዙዎችን አስደመሙ።

ከቤት የተጀመረው ተግባራዊ ዕውቀት ከፍ በማለት፣ በ፲፭ ዓመታቸው ከአካባቢያቸው ዐሥር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የዐፄ ልብነ ድንግል ት/ቤት አደገ። በዘመኑ እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ ይሰጥ የነበረውን ዘመናዊ ትምህርት በመማር በ፲፱፻፵፫ ዓ.ም. አጠናቀቁ። ለጥቀውም ዐፄ ገላውዴዮስ የመምህራን ተቋም በመግባት በመምህርነት ሠልጥነው ሥራ ጀመሩ። ነገር ግን በዘመናዊ ትምህርት የከፈተው የዕውቀት ብርሃን የእርሳቸውን ልብ እያፈካ የነበረው ሥነ ጥበቡ ስለነበር ሥራውን ትተው ወደ ቀያቸው ተመለሱና የሥነ ሥዕልና የቅርፃ ቅርፅ ሙያቸውን አጠበቁ። ሥራዎቻቸውም በአካባቢው እየታወቀ መጣ። ሆኖም በዚህ ዘርፍም አንቱታን ለማትረፍ፣ ጥበቡን የበለጠ ሊያጎለብቱ የሚያስችልና በቴክሎጂ የታገዘ፣ ዘመኑ የደረሰበት ዕውቀት የሚገበዩበት ዕድል በአካባቢው ባለመኖሩ ሰርክ ያሳስባቸው ነበር።

በ፲፱፻፵፮ ዓ.ም. “ግርማዊነታቸው ከአረንጓዴ ባሕር ሲመለሱ” በሚል ርእስ የሥዕል ሥራቸውን ሀ ብለው የጀመሩት ክቡር አርቲስት ለማ ጉያ፤ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ደብረ ዘይት ከተማ በሚገጎበኙበት አጋጣሚ ወደ ሌላ ምዕራፍ አሸጋገራቸው፡፡ የጃንሆይን ወደ ከተማቸው መምጣት እንደዕድል ተጠቅመው እስካሁን ድረስ የሠሯቸው ሥዕላትና ቅርፃ ቅርፆ ለማሳየት በአየር ኃይል ማሰልጠኛ በአውሮፕላን መካኒክነት ስልጠናን እንዲወስድ በሩ ተከፈተ። በዚህ በአየር ኃይል ግቢ ቆይታቸውም የሥነ ጥበብ ሥራዎቻቸውን መሥራት በርካታ ዐውደ ርእዮን አዘጋጅተዋል። አስመራ ከተማ በሚገኝው የአየር ሃይል ጣቢያ በመምህርነትና በጦር መሐንዲስነት ሲመደቡም፣ በራሳቸው ወጪ አስመራ በሚገኘው የጣሊያኖች የሥዕል ትምህርት በመማር ሙያውን አዳበሩ። በ፲፱፻፷፰ ዓ.ም. ከአየር ሃይል በጡረታ ከተገለሉ በኋላ ራሳቸውን ለሥነ ጥበቡ በመስጠት በርካታ ሥራዎችን ለኢትዮጵያ አበርክተዋል።

ክቡር አርቲስት ለማ ጉያ በዘመኑ በአገራችን የሥነ ጥበብ ማሳያ ቦታዎች (ጋለሪዎች) በስፋት አለመኖራቸውን በማስተዋል ከ፴ በላይ የውጭ አገራት ዲፕሎማቶችን በመጋበዝና ሥራዎቻቸውን በማሳየት የሥዕል ማሳያ ማዕከል እንዲመሠረት አድርገል። በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ የመጀመርያ የኾነውን የሥዕል ማስተማርያ “ሥዕልን ያለአስተማሪ” የተሰኘ መጽሐፍን በማሳታም መጪው ትውልድ በጥበብ ራሱን እንዲያስተም በማገዝ የአገር ባለውለታ በመኾን ታሪክ ያወሳቸዋል።

ብዙ ጋለሪ ቤቶችን ባለቤት እንደሆኑ የሚታወቁት አርቲስት ለማ፣ “የአፍሪካ አርት ጋለሪ” የተሰኘና መታሰቢያውን በኔልስን ማንዴላ ስም በማድረግ የገነቡት ትልቅ ጋለሪ ዝናቸው በኢትዮጵያ ብቻ አልቀረም ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው ኘሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ለሦስት ጊዜያት ግብዣ በማድረግ አድንቀዋቸዋል። የፈጠራ ሥራዎቻቸውንም በወረቀት፣ በፋይዚት ቦርድ፣ በጋቢና በሸራ እንዲሁም በጨርቅም ላይ በመሳል ልዩ ችሎታ እንዳላቸው ለዓለም አሳይተዋል።

በአገር አቀፍና አህጉር አቀፍ ደረጃም ጠጒር ባለው ፍየል ቆዳ ላይ ሥዕልን በመሣል ቀዳሚ በመኾን የራሳቸውን የጥበብ አሻራ ለኢትዮጵያ አስቀምጠዋል። በዚህም የፈጠራ ውጤታቸው በኢትዮጵያ የሥነ ጥበባት ፈጠራ ዕድገት የበኩላቸውን ከፍተኛ ድርሻ ተወጥተዋል። ከኢትዮጵያ ውጪ በአሜሪካ፣ በስዊዲን፣ በኬኒያ፣ በእንግሊዝ፣ በናይጄሪያ ወዘተ. አሳይቷል። በተለያየ ጊዜ በርካታ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲኾን፣ በሰሜን አሜሪካ የውስጥ ቅርስ ማኅበር “ሦስት ትውልድ የተናገሩ የጥበብ ሥራዎችን የሠራ” በሊቢያ መሪ ሙአመድ፣ በፊደል ካስትሮም፣ ከሴኔጋል ፕሬዝዳንቶች የገንዘብና የክብር ሽልማቶች ተቀብለዋል።

ለ65 ዓመታተ ለኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ታሪክ ጉልህ አስተዋፅዖ ያደረጉት ክቡር አርቲስት ለማ ጉያ በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ጥቅምት 19 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ቢያርፉም፣ በሕይወት ዘመናቸው በፍየል ቆዳ ላይ ከ10 ሺህ በላይ የሣሏቸው ሥዕሎቻቸው ሕያው እንዲኾኑ አድርጓቸዋል፡፡

እነኾ ባንካችን፣ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ታላላቅ የጥበብ ሰዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉት ክቡር አርቲስት ለማ ጉያ ገመዳን፣ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ቢሾፍቱ ከተማ ዐዲስ ቅርንጫፉን በስማቸው ሰይሞ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ባንካችን አቢሲንያ እኚህን ታላቅ አርቲስት የአገር ባለውለታነታቸውን በማሰብ ዐዲስ ቅርንጫፍ በስማቸው በመሰየሙ ከፍ ያለ አክብሮት ይሰማዋል፡፡

አቢሲንያ ታላላቆችን በማክበር ለታላቅ ሥራ የሚተጋ ባንክ!

ምኒልክ ብርሃኑ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button