አቢሲንያ ባንክ የ2025/26 የግማሽ ዓመት የአፈጻጸም ምዘና ጉባዔውን ጥር 14 ቀን፣ 2018 ዓ.ም በሃይሌ ግራንድ አዲስ አበባ ሆቴል አካሂዷል፡፡
በጉባዔው ላይ የባንካችን የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በስትራቴጂና ሪሰርች ዳይሬክተር በአቶ ዮሴፍ ታምራት ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ባንኩ በዋና ዋና የአፈፃፀም መለኪያዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡ ተገልጿል፡፡
የተመዘገበውን ውጤት አስመልክቶም የባንካችን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ በቃሉ ዘለቀ እንደተናገሩት የባንካችን ውጤት ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ እንዲሁም ከተቀመጠው ዕቅድ አንጻር የተሻለ ሆኖ የተመዘገበበት መሆኑን ጠቅሰው በሚቀጥሉት ስድስት ወራትም ተመሳሳይ ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም ሠራተኛ የበኩሉን ጥረት ማድረግ እንዳለበት በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
አቶ በቃሉ አክለውም ገበያው እየሰጠ ያለውን መልካም አጋጣሚ ወደ ውጤት መለወጥ እንደሚገባና በተለይም የዲጂታል ቴክኖሎጂው ላይ የበለጠ በመስራት ለደንበኞች ምቹ ከባቢን መፍጠር እጅግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በተጨማሪም ዋና ዋና የሆኑትን የባንኩን ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችም በስፋት አብራርተዋል፡፡
የባንካችን የተለያዩ ዲስትሪክቶችም ባለፉት ስድስት ወራት የነበሯቸውን መልካም ተመክሮዎች እንዲሁም ለስራቸው ተግዳሮት የሆኑባቸውንም ዋና ዋና ጉዳዮች አንስተው ሰፊ ውይይት ተካሂዶባዋል፡፡
በቀጣዮቹ ስድስት ወራትም ሊበረታቱና ሊሻሻሉ የሚገባቸውን ሥራዎች በመለየትና ልክ እንደሁልጊዜውም የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚገባ በዋና ስራ አስፈፃሚው አቅጣጫ የተሰጠ ሲሆን ሁሉም ዲስትሪክቶች ለውጤቱ መሳካት የዲስትሪክቶችን ቡድን ከምንግዜውም በላይ በማጠናከር እና የየዕለት ክትትል በማድረግ ለተፈጻሚነቱም እንደሚተጉ ቃል ገብተዋል፡በተጨማሪም ከሁሉም የዋናው መ/ቤት የስራ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት ከወትሮውም የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ገልጸዋል፡፡
ለተገኘው ውጤት መሳካት የዋናው መ/ቤት የስራ ክፍሎችም ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን በቀሪዎቹ ወራትም በየደረጃው ያለ ሁሉም ሠራተኛ የሚቻለውን ሁሉ ጥረት እንዲያደርግ በማሳሰብ ስብሰባው ተጠናቋል፡፡










Leave a Reply