ከስዊፍት (SWIFT) ጋር ይተዋወቁ

ከስዊፍት (SWIFT)  ጋር ይተዋወቁ

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅን  ተከትሎ የቴክኖሎጂ አብዮት በምድራችን ተቀጣጥሏል ማለት ይቻላል፡፡ በጦርነቱ የተሳተፉ አካላት የደረሰባቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቡና ቀውስ ለመጠገን በርካታ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡ ፊታቸውንም ወደ ለውጥ በማዞር በኢኮኖሚ የበለጸጉ አገራትን ለመፍጠር ችለዋል፡፡

በጦርነቱ በአገራት መካከል የተፈጠረውን ርርቆሽ ለማቀራረብ፣ የእርስ በእርስ ትስስርና ግንኙነትን ፈጥረዋል፡፡ ለዚህም እንዲረዳ በኔትዎርኪንግ ቴክኖሎጂ የተለያዩ የመገናኛ አውታሮችን ፈልስፈዋል፡፡  “ዓለም መንደር ሆናለች” የሚል ዜማ መደመጥ የጀመረውም ከዚህ ወቅት ጀምሮ ነው፡፡  

አሁን ግን ሁሉም ነገር ተለውጧል፤ ዓለም ከመንደርም በላይ ጠባለች፡፡ ከዓለም ጥግ እስከ ጫፍ ድረስ መረጃዎች ለመሠራጨት ደቂቃ ይበዛባቸዋል፡፡ ምስጢራዊ ተግባቦቶችን ለመሸሸግ የሚደረጉ ጥረቶችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳሰቡ መጥተዋል፡፡

ቴክኖሎጂ የሚፈጥራቸው አዳዲስ ግኝቶች ከመፍትሔው እኩል ችግሮችን ይዘው መምጣታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የሚፈጠሩት ክሥተቶችም ያንተ ቤት ሲንኳኳ ከመሰማትም በላይ ሰላምን የሚነሡ ናቸው፡፡ ይኽ የሰሞኑ የዓለማችን ኹነት መገለጫ ነው፡፡  

እንደሚታቀው ዓለም ከፈጠራቸው የቴክኖሎጂ ሽግግሮች መካከል በጉልህ የሚጠቀሰው የባንክ ሥርዐት ነው፡፡ ዘመኑ የፈጠረው የባንክ ስርአት ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ  የገንዘብ ዝውውርን ህጋዊና ጤናማ እንዲሆን በማድረግ ከአንዱ የዓለም ጫፍ ወደ ሌላኛው ገንዘብ እንዲደርስ ማድረግ ነው፡፡

የገንዘብ ዝውውር ለማዘመንና ለማቀላጠፍ ከተዘረጉ አዳዲስ አሠራሮች መካከል Society of Worldwide Interbank Financial Telecommunications (SWIFT) በዋነኛነት ይጠቀሳል፡፡ ስዊፍት የባንክ ሥርዐትን በማዘመን በዓለም ላይ ያሉ ባንኮች የፋይናንስ መረጃዎችን በፍጥነት እና በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲላላኩ ያስችላል።

ዋና መሥሪያ ቤቱን ቤልጅየም ያደረገው ስዊፍት፣ እ.አ.አ በ1973 ከ15 አገሮች በተውጣጡ 239 ባንኮች የተቋቋመ ዓለም አቀፍ ሕብረት ሥራ ማኅበር (Global member-owned cooperative) ነው። እ.አ.አ በ1977 ከድንበር ተሻጋሪ ዝውውር ጋር የተያያዙ መመሪያዎችን ለማስተላለፍ ባንኮች በስፋት ይጠቀሙበት የነበረውን የቴሌክስ ቴክኖሎጂን (Telex technology) በመተካት የመልእክት መላላኪያ አገልግሎት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከ11,000 በላይ የፋይናንስ ተቋማትን በማገናኘት፣ ትእዛዞች የሚላላኩበት እና የሚቀባበሉበት የግንኙነት መረብ ሆኗል። በዚህ ሥርዐትም ባንኮች የንግድ፣ የፋይናንስ እና የውጭ ምንዛሪ ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል።

ስዊፍት (SWIFT) ባንኮች፣ የኢንቨስትመንት ተቋማትና ድርጅቶች የመተማመኛ ሰነዶችን ለመክፈት፣ የገንዘብ ዝውውር ትእዛዛትን ለማስተላለፍ እና ገንዘባቸውን እንዲዘዋወር ለማዘዝ፣ ክፍያዎችን ለማዘዝ እና ለመፈጸም፣ ትልልቅ ኮርፖሬሽኖች የከበሩ ማእድናትና የአክሲዮን ግዢዎችን የሚፈጽሙበት የኤሌክትሮኒክስ አውታር ነው፡፡ አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ በመሆኑ በተቋማት መካከል ያለውን የመረጃ ልውውጥ ግልጽ እና ቀልጣፋ በማድረግ ወጪን እና ሥጋትን ይቀንሳል።

ስዊፍትን (SWIFT) በበላይነት የሚቆጣጠሩት የጂ-10 አገራት ባንኮች ሲሆኑ የቤልጂየም ብሔራዊ ባንክ ደግሞ በበላይነት ይቆጣጠራል። በእነዚህ አገራት ውስጥ የሚከወኑ መሠረታዊ የፋይናንስ ግብይቶች ላይ ቁጥጥር ያደርጋል። በሁሉም አገራት ላይ የሚጣሉ የማዕቀብ ሕጎችን (sanctions laws) ሙሉ በሙሉ ያስከብራል፡፡ ስለዚህ በዚህ አገልግሎት የሚጠቀሙ ማንኛውም አገራት ከስዊፍት ቢሰረዙ ወይም ቢታገዱ የሚፈጥርባቸው ተጽዕኖ ከባድ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በቅርቡ የጀመረውን የራሺያ እና የዩክሬን ጦርነት ተከትሎ  የምዕራባውያን አገሮች በሩሲያ ላይ የጣሉት የፋይናንስ ማዕቀብ ነው፡፡

አቢሲንያ የሁሉም ምርጫ!

 ምኒልክ ብርሃኑ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button