የአቢሲንያ ባንክ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት እና የቦርድ አባል አቶ ተካልኝ ገዳሙ ጋር የነበረ ቆይታ!

የአቢሲንያ ባንክ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት እና የቦርድ አባል አቶ ተካልኝ ገዳሙ ጋር የነበረ ቆይታ!

በአለማየሁ ስሜነህ እና ሰብለ ከበደ
አቶ ተካልኝ ገዳሙ ከባንካችን መሥራቾች አንዱ ሲሆኑ፣ የባንካችን የመጀመሪያ ፕሬዚደንትና እንዲሁም የቦርድ አባል የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ ከ11 ዓመት የውጭ ሀገር ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ከሚኖሩበት አሜሪካን ሀገር ለአጭር ጊዜ እረፍት በመጡበት ጊዜ (ከጥቂት ወራቶች በፊት)፣ ስለ ባንካችን ጠቃሚ ታሪካዊ መረጃ ሊሠጡን መልካም ፈቃዳቸውን አግኝተን ከአረፉበት ሒልተን አዲስ አበባ ሆቴል ተገኝተን አነጋግረናቸው ነበር፡፡ በቆይታችንም በርካታ ጉዳዮችን (የባንካችን ምስረታ እና ተያያዥ ታሪኮች፣ በወቅቱ ስለነበረው የባንክ ዘርፍ ቅርፅ፣ ከእዛ በፊት ስለነበሩ ድንቅ የባንክ ባለሙያዎች፣ ስለባንክ ሙያ፣ ስለ ድርጅት ባህል፣ ስለ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ስለነበረው ስቶክ ኤክስቼንጅ ገበያ (Stock Exchange Market)፣ አሁን ላይም አሜሪካን ሀገር ስለመሠረቱትና ስለሚያስተዳድሩት በአሜሪካ የመጀመሪያው የዲያስፖራ ባንክ…እና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች) አንስተንባቸው ብዙ አጫውተውናል፡፡ ከእዛ ውስጥ አቶ ተካልኝ ገዳሙ ማን ናቸው ከሚለው ጀምሮ፣ የባንካችን ቅድመ ታሪክ ጋር የሚያያዘውን እንደሚከተለው ለማጋራት ወደድን፡፡
ጥያቄ፡ አቶ ተካልኝ ገዳሙ እንኳን ወደ ሀገርዎ በሰላም መጡ፣ ከአሜሪካን ሀገር ለአጭር ጊዜ ቆይታ በመጡበት በዚህ ወቅት ጊዜዎን አብቃቅተው ስለባንካችን ጠቃሚ መረጃ እንዲኖረን፣ የባንካችን ታሪካዊ ዳራ እንዲያጫዉቱን ፈቃደኛ ሆነው በመገኘትዎ እጅግ ተደስተናል፡፡
መልስ፡ ከጥያቄአችሁ በፊት እኔም ዕድል ይሰጠኘና፤ በዚህ አጋጣሚ በምታቀርቡት ጥያቄ መልስ በመስጠት መረጃ አንድ አስተዋፅኦ እንዳደርግ ስለጋበዛችሁኝ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ፡፡
ጥያቄ፡ ስለረጅም የሕይወት ጉዞዎ፣ መቼና የት እንደተወለዱ፣ አስተዳደግዎ፣ የሥራ ህይወትዎ እንዲሁም የትምህርት አፈፃፀምዎ ምን እንደሚመስል በአጭሩ ይግለፁልን?
መልስ፡ ኦሆ! ይሄ የሰማይ ስባሪ የሚያህል ጥያቄ ነው፡፡ ቶሎ በአጭሩ መመለስ ያስቸግረኛል፣ ልሞክር፡፡ እኔ እንግዲህ የተወለድኩት በእኛ አቆጣጠር በ1926 ዓ.ም. ነው፣ ጣሊያን ኢትዮጵያን ሊወር ሁለት ዓመት ሲቀረው እንደማለት ነው፡፡አሁን እንግዲህ ይኸው 86ኛ ዓመቴን ጨርሼ 87 ሊሄድ ነው፡፡ የተወለድኩት በምዕራብ ኢትዮጵያ ጎሬ የምትባል ከተማ ነው፡፡ ከዚያ የመጀመሪያ ትምህርቴን ያጠናቀኩት እዚያ ነው፣ በዚያ ጊዜ በጠቅላይ ግዛቶች ወይም ክፍለ ሀገሮች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ስለሌሉ ተማሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ወደ አ.አ. ይመጡና በመንግሥት ወጪ አዳሪ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ይገባሉ፡፡ እና ያኔ እኔ እንደማስታውሰው በእኛ አቆጣጠር በ1940 ዓ.ም. አ.አ. መጥቼ ዳግማዊ ምንሊክ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አዲስ መቋቋሙ ነው፣ ከተለያየ ከተማ ከመጡ ተማሪዋች ጋር አንድ ላይ የመጀመሪያዎቹ ሆነን ገባን፡፡
ከዚያ ስንጨርስ ዪኒቨርስቲ ኮሌጅ የሚባል ነበር ያን ጊዜ የ4 ዓመት ኮርስ ተከታትለን የባችለር ዲግሪ አገኘን፡፡ አሁን ደግሞ በመንግሥት ኪሳራ ውጭ ሀገር ተልከን እኔ ኢኮኖሚክስ ተምሬአለሁ፡፡ እዛ እንዳለሁ ትምህርቴን ስጨርስ የተባበሩት መንግስታት ውስጥ ተቀጠርሁ፡፡ ስምንት ዓመት እዚያ ሠራሁኝ (ይህም ከፊሉን UN, Newyork በተቀጠርኩበትና የተቀረውን አዚህ ECA, Addis Ababa)፡፡ ስምንተኛ ዓመቴን እንደጨረስኩ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሃ/ወልድ ሀገርህን ማገልገል አለብህ ብለው የመንግሥት ሥራ ውስጥ እንድገባ አደረጉ፡፡ መጀመሪያ የዛን ጊዜ ፕላንና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ነበር የሚባለው፣ አቶ ሐዲስ አለማየሁ ነበሩ ሚኒስትሩ፣ በእርሳቸው ስር ፕሮጀክትን እያዘጋጀ የልማት በጀት የሚያቀርብ አንድ ድርጅት ነበረ፡፡ ትንሽ እዛ እንደሠራሁ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆንኩኝ፡፡ እዛ ሁለት ዓመት ከሠራሁ በኋላ ለተጨማሪ ትምህርት ወደ ውጪ ሀገር ሄጄ ተመለስኩ፡፡ የፕላንና ልማት ኮሚሽን የሚባለው አቶ ሐዲስ አለማየሁ ከሄዱ በኋላ የፕላን ኮሚሽን ተባለ እኔም የፕላን ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆንኩኝ፡፡
ከዚያ እንደምታውቁት አንድ ሶስት አራት ዓመት ከሠራሁ በኋላ አብዮቱ ፈነዳ (ተቃጠለም የሚሉ አሉ)፣ በ1966 ዓ.ም. መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ ለአንድ ዓመት ያህል ከጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት (ደርግ) ጋር ሠራሁ፡፡ ብዙ ችግር ስለነበረ እኔም ስላልተመቸኝ አሰናብቱኝ ብዬ ደብዳቤ አስገብቼ አሰናበቱኝ፡፡ ከዚያ በኋላ አፍሪካ ልማት ባንክ አስራ ስድስት ዓመት ተኩል ሠራሁኝ፡፡ ከእዛ ከተመለስኩ በኋላ ከጥቂት ሰዎች ጋር ሆነን አቢሲንያ ባንክን አቋቋምን፣ ከማስታውሳቸው ሰዎች መካከል ከመጀመሪያ አቶ ደበበ ሐብተ ዮሐንስ፣ አቶ ኃይሉ ሻውል፣ ጀነራል ታፈሰ አያሌው የሚባል በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የኢትዮጵያ አየር ሐይል ጀነራል የነበረ ሆነን ሥራውን ጀመርን፡፡ እዚህ አንድ ስድስት ሰባት ዓመት ከሠራሁ በኋላ አሜሪካን ሀገር ተመልሼ ይኸው 11 ዓመት እዛ ቆይቼ ለመጀመሪ ጊዜ መመለሴ ነው፡፡ ይሄ ነው እንግዲህ በአጭሩ፡፡
ጥያቄ፡ በጣም እናመሰግናለን፡፡ UN, Newyork እንዲሁም ECA, Addis Ababa ከዛም በኋላ በነበርዎት ኃላፊነት ሲቀጠሩ፣ ሥራዎችን የተቀላቀሉት፣ አመልክተው በውድድር ሳይሆን፣ እርስዎን የሚያውቁ ሰዎች ጠቁመዎት ወይም (Recommend) አድርገዎት እንደሆነ ሰምተናል፣ እስቲ ስለዚህ ዝርዝሩን ያጫውቱን፡፡
መልስ፡ አዎ! በመሠረቱ ዕውነት ነው፡፡ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልጀምርና፣ አሜሪካን ሀገር ተማሪ ቤት እንዳለሁ የማስተርስ ዲግሪ በኢኮኖሚክስ ለማግኘት ተምሬ ልጨርስ ስል፣ አንድ ቀን የእኔ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሠር ይጠራኝና ከተባበሩት መንግስታት አንድ ደብዳቤ ደርሶኛል፣ በኢኮኖሚክስ መስክ የሚመረቁ ጥሩ ጥሩ የሆኑ የአፍሪካ ተማሪዎች እንዳሉ ከእነሱ መርጠህ ስማቸውን ላክልኝ ተብያለሁ፣ እናም የአንተን ስም ልልክ ነው አለኝ፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ የተባበሩት መንግሥታት ማለት የሀገር መሪዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተሰብስበው ዲስኩር የሚያደርጉበት፣ ሲጋጩ የሚውሉበት ነው፣ እናም እኔ ከየተባበሩት መንግስታት ጋር ምንም ጉዳይ የለኝም፡፡ አይ ተሳስተሃል፣ የተባበሩት መንግስታት ውስጥ ልዩ ልዩ ክፍሎች አሉ፣ ከነዚህም አንዱ የኢኮኖሚ ክፍል ነው፡፡ እዛ ብትሄድ ጥሩ ልምድ ታገኛለህ አለኝ፡፡ እኔ እንዲህ ያለ ሐሳብ የለኝም ፣ ይህን ትምህርት ስጨርስ ሳልውል ሳላድር በቀጥታ ወደ ሀገሬ መሄድ ነው የምፈልገው፣ መንግሥት ነው ያስተማረኝ እና የተማርኩበትን ወጪ ትንሽም ቢሆን ለማካካስ እፈልጋለሁ፣ ደግሞ ግርማዊ ንጉሰ ነገሥት ወደዚህ ሀገር ስመጣ ሲሸኙኝ፣ በሉ ተምራችሁ ተመልሳችሁ ሀገራችሁን አገልግሉ ብለዋል፡፡
ሀገሬን፣ ተመልሼ ማገልገል ነው የምፈልገው፣ ብዬ ትንሽ ተከራከርኩኝ፡፡ አንተ ምን አስጨነቀህ፣ እኔ ስምህን ልላክ ካልፈለግክ እኔ አልፈልግም በላቸው፣ የሚያስገድድህ የለም አለኝ፡፡ ደግሞም ብታስተውል ለየተባበሩት መንግሥታት መሥራት ማለት ለኢትዮጵያ መሥራት እንደማለት ነው፡፡ የአንተ ሀገር እኮ ይህንን የተባበሩት መንግሰታት ድርጀትን ከአቋቋሙት ሀገሮች መካከል በቅድሚያ የምትነሳ ናት፡፡ የእናንተን ሀገር ታሪክ አውቃለሁ፣ ስለዚህ ኢትዮጵያን እንደ መርዳት ነው፡፡ አይ እኔ ምንም አልጣመኝም አይሆንም አልኩት፣ ግን ተጫነኝ፣ ሲጫነኝ ከጭቅጭቁ ለመገላገል በል እንግዲህ ላከው አልኩት፡፡ ከሁለት ወር በኋላ ከየተባበሩት መንግስታት ደብዳቤ ይደርሰኛል፡፡ ትምህርትህን ስትጨርስ ጥቂት ሳምንታት ሲቀሩህ ደውልልኝ ወይም ደብዳቤ ላክልኝ የሚል ነበር፡፡ ትምህርቴን ጨርሼ ወደ ኢትዮጵያ ልመለስ ስል፣ ያን ጊዜ ትምህርታችንን ስንጨርስ እንደምናደርገው፣ ዋሽንግተን ዲሲ ላለው የኢትዮጵያ ኢምባሲ የትምህርት ክፍል አታሼ ሐላፊ ትምህርቴን መጨረሴንና ወደ ሀገሬ የምመለስበትን ትኬት እንዲሁም በዛ ጊዜ የምትሰጥ የኪስ ገንዘብ ነበረች እሷንም ጨምሮ እንዲልክልኝና ጓዜን የምልክበትን ሁኔታ እንዲያመቻችልኝ ፃፍኩለት፡፡
ያው የተለመደ ነገር ስለሆነ ወዲያው እኔ ከነበርኩበት ቺካጎ Chicago አካባቢ University of Illinois, Urbana chanpaign ከምትባል ትንሽ ከተማ በ Newyork አድርጎ እንዲሁም በእንግሊዝ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገባ የአውሮፕላን ትኬት ከእቃ አጓጓዥ ድርጅት ስም ጋር ላከልኝ፡፡ ስለዚህ የምመለሰው በ Newyork በኩል እንደመሆኑ Colombia University, Newyork ይማር የነበረ ሙሉጌታ ወዳጆ የሚባል ወዳጄ ወደ ኢትዮጵያ መመለሴ ነው፣ ስመለስ ደግሞ በNewyork በኩል ስለሆነ አንተ ዘንድ አንድ ሁለት ሶስት ቀን አድራለሁ አልኩት፣ በጣም ደስ ይለኛል ና አለኝ፡፡ እዛ እንደደረስኩ የተባበሩት መንግስታት ጉዳይን አነሳሁበት፣ እንዲህ ያለ ወረቀት ልከውልኛል፣ ምን ይመስልሃል አልኩት፣ ጠይቃቸው ደስ ካለህ ትቀበላለህ ደሰ ካላለህ ትመለሳለህ አለኝ፡፡ እኔም የተባበሩት መንግሥታት መሥሪያ ቤት ሄድኩኝና እንደአጋጣሚ ደብዳቤውን የጻፈችውን ሴትዮ አገኘኋት፣ ደብዳቤውንም አሳየኋት፡፡ ኢንተርቪው ልናደርግህ ነው አለችኝ፡፡ እኔ ለኢንተርቪው ጊዜ የለኝም፣ ብዙ ገንዘብም ስለሌለኝ እዚህ ብቆይ ሁለት ሶስት ቀን ነው፣ ወደ ሀገሬ እየተመለስኩ ነው፣ እግረ መንገዴን ምንድን ነው ብዬ ለመጠየቅ ነው የመጣሁት አልኳት፡፡ እሷም ጉዳዩን በአጭሩ አስረዳችኝ፣ የተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚ ዲፓርትመንቱ እንደ አንተ ያሉ ወጣት ኢኮኖሚስቶችን ይፈልጋል፡፡
በቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ECA የሚባል አንድ ትልቅ ድርጅት ይቋቋማል፣ ብትፈልግ እዛ ትሠራለህ፣ እኛ ጋርም ብዙ የአፍሪካ ኢኮኖሚስቶች ስለሌሉንና የአፍሪካ ኢኮኖሚስት ስለምንፈልግ እኛ ጋር ትሠራለህ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢንተርቪው አዘጋጅቼ እነግርሀለው አለችኝ፡፡ ኢንተርቪው የሚያደርጉ አንድ አራት አምስት ሰው በሚቀጥለው ቀን አዘጋጅታ፣ ኢንተርቪው ተደረግኩኝ፡፡ ብዙዎቹን ጥያቄዎች አሁን ላይ አላስታውሳቸውም፣ በዕውነት፣ አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ግን አስታውሳለሁ፣ ብዙ ጥያቄዎች ከጠየቁኝ በኋላ፣ አሁን አንተ የተባበሩት መንግስታት ውስጥ ብትቀጠር፣ የምታገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች አሉ፣ ከነዚህም መካከል አንዱ የህይወት ኢንሹራንስ የሚባለው ነው፣ እንግዲህ አንድ አደጋ ደርሶብህ ከዚህ ዓለም በሞት ብትለይ ገንዘቡ ለማነው የሚሄደው? ለአባትህ፣ ለእናትህ …አሉኝ፣ አይ እንዲህ ያለ ነገር ካለ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት፣ ለትምህርት ሚኒስትር ይሂድልኝ አልኳቸው፡፡ አባት እናት የሉህም፣ አሉኝ አልኳቸው፣ ወንድም እህት ዘመዶች የሉህም፣ ወንድም እና እህት የሉኝም ግን ያሉኝ ዘመዶቼ ራሳቸውን የቻሉ ናቸው፣ ይህ የእኔ ጥቅማ ጥቅም አያስፈልጋቸውም፣ ይህ የሚያስፈልጋቸው የኢትዮጵያ ህጻናት ናቸው፡፡ እኔ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ እስከ አሁን ያስተማረኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፣ በነጻ ማለት ነው፣ እኔ ደግሞ የአቅሜን ያህል አንድ አይነት አስተዋፅኦ ማድረግ ስላለብኝ ይህ ገንዘብ ሄዶ አንድ ተቋም ተቋቁሞ ወይም ደግሞ ትምህርት ሚንስትር ተማሪዎችን ውጪ እየላከ ሲያስተምር ሊጠቀምበት ይችላል አልኳቸው፡፡ዝም አሉ፡፡ በማግስቱ ተደውሎ ተቀጥረሃል ተባልኩኝ፡፡እኔ አሁን ሳስብ እነዛን ጥያቄዎች መልሼ ይሆናል፣ አይሆንም፣ ግን በጣም የመታቸው ግን ይህ መጨረሻ ላይ የሰጠሁት መልስ ይመስለኛል፡፡ ከዛ ሥራ ጀመርኩ፡፡ ሥራ የመጣልኝ ተማሪ ቤት ሳለሁ ነው ለማለት ይቻላል፡፡

እዚህ 8 ዓመት ካገለገልኩ በኋል፣ ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃ/ወልድ ይፈልጉሃል ተብዬ  ቢሮአቸው ሄጄ፣ ለምንደነው አንተ ሀገርህን የማታገለግለው  ብለው ከአቶ ሐዲስ አለማየሁ ጋር እንድሠራ ቅድም እንደጠቀስኩት አሾሙኝ፡፡ አንድ 9 ዓመት እንደሠራሁ፣ በ10ኛው ዓመት ደርግ መጣ፣ጥቂት እንደሠራሁ ተሰናብቼ ቁጭ አልኩኝ፣ ከእዛ ደግሞ ከአፍሪካ ልማት ባንክ አንድ ወረቀት  ይመጣል፣ ለአፍሪካ ልማት ባንክ አዲስ ፕሬዚዳንት ተሹሟል፣ የእሱ የኢኮኖሚ አማካሪ እንድትሆን እንፈልጋለን ይላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሥራ ነው የምትሠራው፣ ደሞዙ ይህን ያህል ነው ይላል፡፡ እንዴ ምንድን ነው ይሄ፣ እርግጥ ሥራ አፈልጋለሁ፣ ግን አልጠየቅኳቸውም ብዬ አንድ አሁን ስዊዲን የሚገኝ በላቸው አስራት የተባለ ወዳጄን፣ እንዲህ ኣይነት ጥያቄ መጣ፣ ምን ልበላቸው ስለው፡፡ አይ አንተ ደግሞ የማይጠየቅ ጥያቄ ነው የምትጠይቀው፣ አሰናብቱኝ ብለህ ከደርግ ወጥተሃል፣ ደሞዝና ሥራ አሁን የለህም፣ ዝም ብለህ ሂድ፣ ከሆነ ሆነ ካልሆነ ሌላ ቦታ ትሄዳለህ አለኝ፡፡ ዕውነቱን ነው ብዬ  የአፍሪካ ልማት ባንክ ሄድኩኝ፡፡ ፕሬዚዳንቱን አገኘሁት፣ ነገር ግን በምን ምክንያት የቅጥር ኮንትራት ወረቀት እንደተላከልኝ አልነገረኝም፡፡   እንደምገምተው ግን ሰዎች የእኔን ስም ሰጥተውት እንደሚሆን ነው፡፡

እዛ 16 ዓመት ተኩል ያህል ከሠራሁ በኋላ፣ ከሀገር ውጪ ከዚህ ጊዜ በላይ መቆየትም ስለሰለቸኝ ጭምር፣ ወደ ሀገር መመለስ አለብኝ ብዬ ተመለስኩ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሰመለስ ደግሞ እነ አቶ ሐይሉ ሻወል፣ አቶ ደበበ ሐ/ዮሐንስ፣ ጀነራል ታፈሰ አያሌው ባንክ ልናቋቋም ነውና እባክህ አብረን እንሥራ ተቀላቀለን አሉኝ፡፡ አሁን ጡረታ ላይ ነኝ፣ ነገር ግን አንድ የታሪክ ማስታወሻ ለመፃፍ እንዲሁም በየጊዜው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚያጠና ፈረንጆቹ Think Tank የሚሉትን  የኢኮኖሚ ጥናት ድርጅት ማቋቋም እፈልጋለሁ በማለት ትንሽ ተከራከርን፣ ተጫኑኝ ለማለት አችላለሁ፣ መቼም ሰው ሲጫነኝ እምቢ ማለት ትንሽ ያስቸግረኛል፡፡ ለሀገራችን የሚያስፈለግ ነው እያሉ ነበር የሚነግሩኝ፣ ይህን ደግሞ አለመቀበል ማለት ሀገሬንም ህዝቤንም አላገለግልም እንደማለት ሆኖ ተሰማኝ፡፡ ይህን ሥራ ለአንድ ዓመት ከሠራሁ በኋላ የማስበውን ሥራ ከዚያ በኋላ እሠራለሁ ብዬ ኃላፊነቱን ተቀበልኩ፡፡

 ያላችሁት ነገር ዕውነት ነው፣ እስከአሁን ተቀጥሬ የሠራሁባቸው መሥሪያ ቤቶች ሁሉ የእኔን ስም አየሰሙ ዕድሉን የሰጡኝ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ እንደ አጋጣሚ አሜሪካን ሀገር የዛሬ 11 ዓመት ስመለስ፣ እዛ ያሉ ኢትዮጵያውያን አዲስ ባንክ ማቋቋም እንፈልጋለን ብለው ኃላፊነቱን እንድቀበል ጠየቁኝ፣ በዚህም ጥያቄ ተሸንፌ እሺ ብዬ ተቀበልኩ፡፡ አሁን ላይ እሱን በመሥራት ላይ ነው ያለሁት፣ ይሄንን እንደ ዕድል ነው የምቆጥረው፡፡ የእኔ ረጅም የህይወት ጉዞ ይህን ይመስላል፡፡

….ይቀጥላል!

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button