በዘመናችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና የተጠቃሚዎቹን ቁጥር በእጅጉ በመጨመር ላይ የሚገኘው የዲጂታሉ አለም ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ለተጠቃሚዎች የያዘ ነው፡፡ ሆኖም ይህ የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት በአገልግሎት ሰጪዎች እና ተጠቃሚዎች በቂ እና በየጊዜው የሚተገበሩ የደህንነት ጥበቃ ቅድመ ስራዎች ካልተሰራበት እጅግ ጉልህ የሆነ ኪሳራን ሊያስከትል እንደሚችልም አያጠያይቅም፡፡ ይህ አጭር ጽሁፍም በዲጂታሉ አለም እያደገ እና መልኩንም ከአዳዲስ የቴክኖሎጂ ለውጦች ጋር በመለዋወጥ የብዙዎችን የፋይናንስ ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል ላይ ስለሚገኘው የበይነ መረብ ስርቆት (Digital Scam) ምንነት፣ ቅድመ ጥንቃቄዎች እና የመፍትሔ ነጥቦች ላይ ዳሰሳ ያደርጋል፡፡
የበይነ መረብ ስርቆት በፋይናንስ ተቋማት
የበይነ–መረብ ማጭበርበር
ከላይ በመግቢያችን እንደተመለከትነው የተለያዩ የፋይናንስ አገልግሎቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ በበይነ-መረብ ዘዴዎች በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት መሰጠት መጀመራቸውን እና የተጠቃሚዎችም ቁጥር በእጅጉ በማሻቀብ ላይ መሆኑን ተከትሎ አጭበርባሪዎች ትኩረታቸውን በእነኚሁ የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ካደረጉ ሰንበትበት ብለዋል፡፡ በመሆኑም አጭበርባሪዎች በተጠና እንዲሁም ጊዜው የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የኢላማቸውን ግለሰባዊ ዝንባሌ ከግምት በማስገባት የተለያዩ የማጭበርበር ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ በአመት ብዙ ቢሊዮን ብሮችን በአለም አቀፍ ደረጃ ከተለያዩ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪዎች በዋነኛነት ደግሞ ከደንበኞቻቸው ያጭበረብራሉ፡፡ ይህን ተከትሎ እ.ኤ.አ በ2022 በአሜሪካ ባንከርስ አሶሴሽን የተደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው በአሜሪካ ብቻ ጥናቱ በተደረገበት ዓመት 2.2 ሚሊዮን የማጭበርበር ሪፖርቶች ሲመዘገቡ በሪፖርቶቹ ማጭበርበር ተደርጎበታል በመባል የተጠቀሰው ገንዘብም በጥቅሉ 8.8 ቢሊዮን የሜሪካን ዶላር ነበር፡፡
በአብዛኛው የፋይናንስ ማጭበርበር ሰለባ ሲሆኑ የሚስተዋሉት አረጋዊያን እና ዝቅተኛ የዲጂታል ፋይናንስ ግንዛቤ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ማለትም በጥቅሉ የማጭበርበር አደጋን በቅድሚያ ለመገንዘብ የሚያዳግታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ ይህንን ቅድመ ዳሰሳ በቁጥሮች በማስደገፍ ፋይናንሺያል ትራንስፓረንሲ ኮሚቴ እ.ኤ.አ በ2021 ይፋ ባደረገው ጥናት በአለም ዙሪያ በ2021 ብቻ ከ1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ከእነኚሁ የህብረተሰብ ክፍሎች በአጭበርባሪዎች መመዝበሩን ያትታል፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የፋይናንስ ማጭበርበር በአለም ዙሪያ እየተበራከተና መጠኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሻቀብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በፋይናንሱ ዓለም በፍጥነት ተቀባይነትን እያገኙ የመጡት የክሪፕቶ ከረንሲ እና የቶክን መገበያያዎች አጭበርባሪዎች ያለአግባብ ያገኙትን ገንዘብ ለማሸሽና ከተጠያቂነት ለመዳን የሚችሉበትን ውስብስብ የአሰራር ዘዴዎች ይዞ በመቅረቡ አሁን ላይ አጭበርባሪዎችን ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ፈታኝ አድርጎታል፡፡
የተለመዱ የማጭበርበሪያ ዘዴዎች
በዚህ ርዕስ ስር በአጭበርባሪዎች በተለያዩ ጊዜያት በአብዛኛው ጥቅም ላይ የሚውሉ የማጭበርበር ዘዴዎችን እንመለከታለን፡፡ ይህም አንባቢያን እራሳቸውን ለመከላከል ለሚያደርጉት ጥንቃቄ በወሳኝነት ሊያግዙ የሚችሉ ነጥቦችን ለመዳሰስ ይረዳል፡፡
1- መልዕክት በመላክ ማጭበርበር (phishing)፡ ይህ በአጭበርባሪዎች በአብዛኛው ጥቅም በመዋል ላይ የሚገኝ ሲሆን ለስርቆት ኢላማ ለሆነው ተቋም ወይም ግለሰብ የተለያዩ ኢሜይል ወይም የጽሁፍ መልዕክቶችን ልኮ ከትክክለኛ አገልግሎት ሰጪ እንደተላከ በማስመሰል ለሶስተኛ ወገን ሊተላለፍ ያልተገባ እንደ የባንክ ሂሳብ ዝርዝር መረጃ፣የሚስጥር ቁጥርና የመሳሰሉ ግለሰባዊ ይዘት ያላቸውን መረጃዎች እንዲያጋራና በማስከተልም የፋይናንስ ደህንነቱን አደጋ ላይ በመጣል ከደንበኛው ጋር በመደራደር ክፍያን መቀበል አልያም በሂሳቡ የሚገኘውን ተቀማጭ ያለ ፍቃዱ ወጪ ለማድረግ ብሎም የማንነት ስርቆት ለመፈጸም በሰፊው በአጭበርባሪዎች ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የጽሁፍ መልዕክቶች በአብዛኛው የስማርት ስልክ ተጠቃሚ የሆኑ ተገልጋዮችን ማዕከል በማድረግ ከባንክ የተላከ በማስመሰል የጽሁፍ መልዕክት በመላክ በውስጡ ያለውን ማስፈንጠሪያ (link) በሚጫንበት ወቅት ወሳኝ የተባሉ ግለሰባዊ መረጃዎቹ ለአጭበርባሪዎች ጠለፋ የሚጋለጡበትን መንገድ የሚያመቻች የማጭበርበር ዘዴ በስፋት በስራ ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡
2- የድምጽ ማጭበርበር(voice phishing): ይህ በሰፊው በሀገራችን የተለያዩ የባንክ ደንበኞችን የፋይናንስ ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን ከስሙ ለመረዳት እንደሚቻለው አጭበርባሪዎች የባንክ ወይም የሌላ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪን ሰራተኛ አልያም ተወካይ በመምሰል ኢላማቸ ለሆነ ሰው ስልክ በመደወል በባንክ ሂሳቡ ላይ የገጠመ የቴክኒክ ብልሽት አልያም የአሰራር ለውጥ እንዳለ በመንገር ይህ ችግር ይፈታ ዘንድ ደንበኛው በአገልግሎት ሰጪው ዘንድ ያለውን ሚስጥራዊ መረጃዎች እንዲያጋራ የሚጠይቁበት የማጭበርበር ዘዴ ነው፡፡
4- ሀሰተኛ መጠይቆች: በሰፊው በአጭበርባሪዎች ጥቅም ላይ በመዋል ላይ የሚገኝ ዘዴ ሲሆን ለጥቃቱ ኢላማ የሆነውን ግለሰብ በመምረጥ እውነተኛ ያልሆነ ጥናት ደንበኛ በሆነበት ባንክ እየተሰራ እንደሆነ ይህም በመሰረታዊነት በደንበኛው ሊመለሱ የሚገቡ መጠይቆችን እንደሚያካትት በመግለጽ የጥቃቱ ኢላማ ፍጹም ተገቢ ያልሆኑና በመደበኛ ጥናት መጠይቅ መዘርዝሮች ውስጥ ሊካተቱ የማይገባቸው ግለሰባዊ የፋይናንስ መረጃዎች እንዲሰጥ የማታለያ መንገድ በመሆን በጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን በአብዛኛው በአጭበርባሪዎች ጥቅም ላይ በመዋል ላይ የሚገኙትን ጨምሮ ሌሎች በዚህ ርዕስ ላይ ያልተካተቱ የማጭበርበር ተግባራት የደንበኛውን የባንክ ሂሳብ ከመዝረፍ ባለፈ ዘላቂ የሆኑ እንደ የማንነተት ስርቆት፣ ዝቅተኛ የብድር አመላለስ ታሪክና ስነ-ልቦናዊ ቀውስን በማጭበርበር ድርጊት ተጠቂው ላይ ጥለው ስለማለፋቸው ቀላል የማይባሉ ማሳያዎች ስለመኖራቸው የማይታበል ሀቅ በመሆኑ የባንካችን ደንበኞች በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚከተሉትን የጥንቃቄ እርምጃዎች በመከተል እራሳቸውን ከአጭበርባሪዎች መከላከል ይኖርባቸዋል፡፡
እራስዎን ከመጭበርበር ለመጠበቅ ሊያደርጓቸው የሚገቡ ነገሮች
1- ቀይ መስመርዎትን ይለዩ፡ በየትኛውም ሁኔታ የመጀመሪያው ራስዎን ከአጭበርባሪዎች የሚከላከሉበት መፍትሔ የማጭበርበር ኢላማ ስለመሆኖ ጠቋሚ ነጥቦችን መለየት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የትኞቹ ጉዳዮች እንደ ቀይ መስመር ሊወሰዱ ይችላሉ የሚለውን ከዚህ እንደሚከተለው እንመልከት፡፡
ችኮላ፡ አጭበርባሪዎች አብዛኛውን ጊዜ የጥቃት ኢላማቸው በተረጋጋ መንፈስ ከእነርሱ ጋር ስለሚያደርገው የመረጃ ልውውጥ እንዳያስብ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ ተጠቂውን በማዋከብና ችኮላ በተሞላበት ሁናቴ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የባንክ ቤት የደንበኞች አገልግሎት ሹም መሆኑን መግለጽ ለኢላማው የስልክ ጥሪ አልያም ኢሜይል የሚያደርግ አጭበርባሪ በአፋጣኝ ለሚጠይቀው ጥያቄ መልስ እንዲሰጠው ያለበለዚያ የደንበኛው ሂሳብ ሊታገድበት ወይም ሊዘጋ እንደሚችል ሊናገር ይችላል፡፡
ያልተጠየቀ ግንኙነት (unsolicited contact) ፡ ባንኮች የደንበኞቻቸውን የአገልግሎት ጥራት ለማረጋገጥ በየጊዜው ሊያደርጉ የሚችሉት ግንኙነት እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ አይነቱ ግንኙነት የአጭበርባሪዎች ድርጊት የሚለየው በግንኙነቱ ጊዜ በተለምዶ ሊጠየቁ የማይገባቸውን ሚስጥራዊ የሆኑ ግላዊ ይዘት ያላቸውን መረጃዎች ኢላማው እንዲሰጥ ይጠየቃል፡፡ ለምሳሌ አንድ የባንክ ደንበኛ ስለ አገልግሎት ጥራት ማሻሻል በሚያትት የኢሜይል ልውውጥ ላይ ግላዊ የሆነን እንደ የሞባይል ባንኪንግ ይለፍ ቃል ያለ መረጃ ቢጠየቅ ይህንን መረጃ ቆም ብሎ ሳያስብ ከመስጠት ሊቆጠብ ይገባዋል፡፡
የወል መጠሪያዎችን መጠቀም፡ ተቋማት ከደንበኞቻቸው ጋር ለመገናኘት በሚጠቀሟቸው በተለያዩ የግንኙነት ዘዴዎች ደንበኛውን በስሙና ልዩ መለያው በመጥቀስ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን በአብዛኛው ጊዜ አጭበርባሪዎች ካላቸው የመረጃ ውስንነት አንጻር ለጥቃት ኢላማ ያደረጉትን ግለሰብ በወል መጠሪያው በመጠቀም ለምሳሌ እንደ “የተከበሩ ደንበኛችን” የሚል አገላለጽ ሲጠቀሙ ይስተዋላል፡፡ ይህም ሌላኛው ቀይ መስመር ተብሎ ሊወሰድ የሚገባው ነው፡፡
2- ወደ ባንካችን የጥሪ ማዕከል ይደውሉ፡ አቢሲንያ ባንክ የደንበኞቹን የፋይናንስ ደህነት ለማረጋገጥ ባስተዋወቃቸው የዲጂታል ፋይናንስ መተግበሪያዎች ላይ ካካተታቸው አስተማማኝ የደህንነት መጠበቂያ አሰራሮች ጎን ለጎን ደንበኛው በየትኛውም ጊዜ መጭበርበር ሲፈጸምበት ወይም ጥርጣሬ ካለው በነጻ ስልክ መስመር 8397 በመደወል ሂሳቡ ስላለበት ሁኔታ ብሎም የመጭበርበር ጥርጣሬን ለማረጋገጥ ይችላል፡፡ እንዴት? እንደሚከተለው:-
ጥርጣሬ ባደረብዎት ግንኙነት የተሰጠዎትን ስልክ ቁጥር ወይም ሌላ የግንኙነት መስመር ከመጠቀምዎ በፊት በቅድሚያ ባንካችን ባዘጋጀው የነጻ የስልክ መስመር በመደወል አልያም በባንኩ ኦፊሴሊያዊ ድህረ-ገጽ ላይ በተመለከቱ ሌሎች የግንኙነት መስመሮች በመጠቀም ማረጋገጫዎችን ይጠቀሙ፡፡
ግልጽ ጥያቄዎችን ይጠይቁ፡ በባንኩ በቀረበው የነጻ ስልክ መስመር በመጠቀም ስላለዎት የመጭበርበር ጥርጣሬ ግለጽና ፈጣን የሆነን መልስ ከሚመለከተው የባንኩ ተወካይ ስለ ሂሳብዎ አሁናዊ ሁኔታ በቂ ማብራሪያና ምላሽን ለማግኘት ይችላሉ፡፡
አጠራጣሪ ተግባራትን ሪፖርት ያድርጉ፡ በማንኛውም አይነት የግንኙነት ዘዴ የመጭበርበር ኢላማ እንደሆኑ ከተጠራጠሩ ባንኩ ባዘጋጀው የነጻ ስልክ መስመር በመደወል ጥቆማዎትን ይስጡ፡፡ ይህም ሊወስዱ የሚገባዎትን የደህንነት ጥንቃቄ እርምጃዎች ብሎም በሂሳብዎ ላይ ስላሉ ያልተለመዱ እንቅስቃሴዎች በባንኩ ቁጥጥር እንዲደረግ ትልቅ እገዛ ያደርጋል፡፡
ተጨማሪ የቅድመ መከላከል እርምጃዎች፡ ከላይ በዋነኛነት ከተዳሰሰው ማጭበርበርን የመከላከያ መንገድ ጎን ለጎን ደንበኞች ከዚህ የሚከተሉትን ሌሎች አማራጮች ሊከተሉ ይችላሉ፡-
ጠንካራ የይለፍ ቃል ይጠቀሙ፡ ደንበኛው በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉና ተገማች የሆኑ እንደ የልደት ቀን፣ የስልክ ቁጥርና ሙሉ ስም የመሳሰሉ ይለፍ ቃላትን ከመጠቀም ይልቅ የፊደላት፣ ምልክቶችና የቁጥሮች ድብልቅ የሆኑ ጠንካራና በቀላሉ በአጭበርባሪዎች ሊገመቱ የማይችሉ የይለፍ ቃላትን በመጠቀም ራሱን ከአጭበርባሪዎች ለመታደግ ይችላል፡፡
ተደራራቢ የደህንነት ማንቂያን ይጠቀሙ፡ ይህም ሲባል ደንበኛው በሚጠቀመው አገልግሎት ላይ ቀድሞ ከሚጠቀመው የደህንነት ማንቂያ ለምሳሌ የይለፍ ቃል ይጠቀም ከነበር በዚሁ የደህንነት ማንቂያ ላይ ተደራቢ ለመሆን የሚችል ሌላ የደህነንነት መቆጣጠሪያን መጠቀም፡፡ ይህም የዲጂታል እንቅስቃሴዎን ከአጭበርባሪዎች ለመከላከል ተጨማሪ ዘዴን ለመቀየስ ያስችልዎታል፡፡
በየጊዜው ሂሳብዎ ስላለበት ሁኔታ ይከታተሉ፡ ከባንካችን የሚደርስዎትን የሂሳብ መግለጫና የዲጂታል ባንኪንግ መተግበሪያዎች ላይ ያሎትን እንቅስቃሴ በቋሚነት ይከታተሉ፡፡ ይህን ማድረግዎ በሂሳብዎ ላይ የሚስተዋሉ ያልተለመዱ የሂሳብ ልውውጦችን በቀላሉ ለመገንዘብና የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያስችሎታል፡፡
የግል መረጃዎን በጥንቃቄ ያጋሩ፡ በኢሜይል ወይም በሌላ ማንኛውም የግንኙነት ዘዴ ካልታወቁ ግለሰቦች አልያም ተቋማት የሚቀርቡልዎትን ግለሰባዊ ጥያቄዎች ከመመለስ ይቆጠቡ፤ የተለያዩ ካልተረጋገጡ መነሻዎች የሚላኩ መስፈንጠሪያዎችንም ከመጫን ራስዎን ይገድቡ፡፡ በዚህ አግባብ ምንግዜም ከማን ጋር የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ላይ እንዳሉ በትኩረት በማሰብ ያልተገቡ ግለሰባዊ ይዘት ያላቸውን መረጃዎች ለሶስተኛ ወገን ከማጋራት ይቆጠቡ፡፡
ደህነታቸው በተጠበቁ ኔትዎርኮች ይጠቀሙ፡ የሞባይል አልያም ኢንተርኔት ባንኪንግ በሚጠቀሙበት ጊዜ ለአጭበርባሪዎች ኢላማነት በቀላሉ የሚጋለጡ የጋራ ኔትዎርኮች እና ቪ.ፒ.ኤን ከመጠቀም ይልቅ የግል ኔትዎርኮችን ይጠቀሙ፡፡
የአንቲ ቫይረስ መተግበሪያዎች ዘመኑ ያላለፈባቸው መሆኑን ያረጋግጡ፡ ይህም በአጭበርባሪዎች በጥቅም ላይ ሊውሉ ከሚችሉና የደህንነት ጥሰት ተጋላጭነትን ሊጨምሩ ከሚችሉ እንደ ማልዌርና ቫይረሶች ራስዎን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሔ ነው፡፡
በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎችንና የአገልግሎት አሰጣጥን የተመለከቱ ጉዳዮችን በንቃት ይከታተሉ፡፡
የመፍትሔ ነጥቦች
በአጭበርባሪዎች ስለመታላለዎ እርግጠኛ ከሆኑና በባንካችን ያለዎት ሂሳብ ደህንነት አደጋ ላይ ከወደቀ ፣ የሚከተሉትን የመፍትሄ እርምጃዎች በመከተል የሚደርስብዎትን አሉታዊ ጫና ለማስቀረት ወይም በእጅጉ ለመቀነስ ይችላሉ፡፡
ወዲያውኑ ከባንካችን ጋር ግንኙነት ይፍጠሩ፡ በሂሳብዎ ላይ ያስተዋሉት እንግዳ ነገር አልያም ለማጭበርበር መጋለጥዎትን ካረጋገጡ፣ ወዲያውኑ ለባንካችን በማሳወቅ በሂሳብዎ ላይ የሚደረጉ ከእርስዎ ፍቃድ ውጭ ያሉ እንቅስቃሴዎች እንዲቋረጡ ማድረግ ይችላሉ፡፡
እንደ የይለፍ ቃልና የመሳሰሉትን ከባንክ ሂሳብዎ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባላቸው መገልገያዎች ላይ የሚጠቀሙባቸውን የደህንነት መጠበቂያዎች የጥቃት ኢላማ መሆንዎን ከተገነዘቡ ወይም ጥርጣሬ ካደረብዎ ወዲያውኑ ይቀይሩ ፡፡
በህግ ስልጣን ለተሰጣቸው አካላት ያሳውቁ፡ የማጭበርበር ሰለባ ከሆኑ የኮምፒውተር ወንጀልን ለመደንገግ በ2008 ዓ.ም በወጣው አዋጅ መሰረት መሰል የማጭበርበር ጉዳዮችን ለመከታተልና ለፍትሕ ለማቅረብ ስልጣን ለተሰጣቸው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት መስሪያ ቤት እና ሌሎች የፍትህ ተቋማት ስለ ጉዳዩ በፍጥነት ያሳውቁ፡፡
ማጠቃለያ
አጭበርባሪዎች በየጊዜው ቴክኖሎጂው የደረሰበትን ደረጃ በመከተል የተለያዩ የማጭበርበሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም የተራቀቁና ለእውነት የቀረቡ በሚመስሉ መደለያዎች የብዙዎችን የፋይናንስ ደህንነት አደጋ ላይ መጣላቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሆኖም ደንበኞች በየጊዜው መልኩን ከሚቀያይረው የአጭበርባሪዎች ወጥመድ እራሳቸውን ለመከላከል ይችሉ ዘንድ እራሳቸውን በተገቢው መረጃ በማዘመን ተገቢውን ጥረት ስለማድረጋቸው ዘወትር ማሰብ ይገባቸዋል፡፡
በተጨማሪም በየትኛውም ጊዜ የሚያጋጥሟችሁን አጠራጣሪ ሁኔታዎች የባንካችንን ነጻ የስልክ መስመር ብሎም ሌሎች ኦፊሲያላዊ የግንኙነት መስመሮችን በመጠቀም ማሳወቅ ለነገ የማይባል ሌላው መሰረታዊ ነጥብ ነው፡፡ በጥቅሉ ከላይ የቀረቡትን የደህንነት ቅድመ ጥንቃቄዎችና የእርማት እርምጃዎች በመከተል ወሳኝ የሆነውን የፋይናንስ ደህንነትዎን ይጠብቁ፡፡
Leave a Reply