ገንዘብ መቆጠብ ለምን አስፈለገ?

ገንዘብ መቆጠብ ለምን አስፈለገ?

አለማየሁ ስሜነህ

ስለ ገንዘብ አያያዝና ማስተንተን ለማወቅ በርካታ ዓመታትን በትምህርት ብናሳልፍም አሁን ድረስ ብዙዎቻችን ገንዘብ ነክ ጉዳዮቻችንን በሚገባ ማስተዳደር ላይ የጎላ ክፍተቶች ይታዩብናል፡፡ ገንዘብ ማስተዳደር ሲታሰብ ትኩረት ሊሠጣቸው የሚገቡ በርካታ ቁምነገሮች አሉ፡፡ በዋናነት ግን ቁጠባ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ የቁጠባን ጥቅም ፈጽሞ በመረዳት እንዴት መቆጠብ፣ እንዲሁም ምን ላይ በሚገባ ሊውል ወይም ኢንቨስት ሊደረግ እንደሚችል ጠንቅቆ ያለማወቅ ችግር፤ አልያም ዐውቆም የመተግበር ችግር በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ለወደፊት የምንሠራበት ሆኖ ለዛሬ ቁጠባን እጅግ አስፈላጊ ከሚያሰኙት ዐበይት ምክንያቶች የተወሰኑትን ለመጠቋቆም ተሞክሯል፡
አንዳንዶቻችን መቆጠብ የምንችገርበት ትልቁ ምክንያት ዘወትር እንድንቆጥብ ሊያነቃቃን የሚችል እና የሚገፋፋን ግልጽ የሆነ የምንቆጥብበት ዓላማ በዕቅድ ባለማስቀመጣችን ነው፡፡ ስለሆነም ገንዘብ መቆጠብ ጠቃሚ የሆነባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች መረዳታችን ትርጉም ያለው የቁጠባ ዓላማ ወይም ምክንያት እንዲኖረን ከማገዝ ባለፈ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ የቁጠባ ልማድን ወይም ባህልን በሂደት ለማዳበር ሊረዳ ይችላል ተብሎ ይታመናል፡፡
ገንዘብ መቆጠብ ጠቃሚ ከሆነባቸው ዐበይት ምክንያቶች
የቤት ባለቤት ለመሆን
ቤት ለመግዛት ከፋይናንስ ተቋማት መበደር ይቻላል፡፡ ዳሩ ግን ለቤት ግዢ የሚጠበቅብህን 20%-40% የሚደርስ ተገቢ መዋጮ (Equity Contribution) እንዲሁም እንደ የቴምብር ቀረጥ (Stamp Duty)፣ አረቦን (Insurance Premium) ፣ ኮሚሽን፣ የአገልግሎት ዋጋ ..ያሉ ከቤቱ ግዢ ጋር ተያያዥ የሆኑ ክፍያዎችን ያለ ጭንቀት ለመሸፈን በቁጠባ ሒሳብ የተጠራቀመ ገንዘብ መኖሩ አስፈላጊ ነው፡፡ ወዳጄ! ከአበዳሪ ተቋማት የምትጠየቀውንና የሚጠበቅብህን ቆጥበህ ከተገኘህ (ለምሳሌ የቤቱን የግዢ ዋጋ ከ40% ጀምሮ በራስህ መሸፈን ከቻልክ) ከአበዳሪ ተቋማት የተሻለ ወለድ እንድታገኝ ከማስቻሉ ባለፈ የሚያስፈልግህ የብድር መጠን(Loan Amount) ያነሰ እንዲሆን እና እርሱንም ተከትሎ የብድር ክፍያ (Loan Repayment) መጠኑ የማይከብድህና በዕለታዊ የህይወት ጉዞህ ያለጭንቀት ለመኖር፣ ብሎም ለትውልድ የሚተርፍ ጥሪት የማቆየት ጥረትህን ያግዛል፡፡
መኪና እንዲሁም ሌሎች ትልልቅ ግዢዎችን ለመፈጸም
የመኪና ገበያ በተለያየ ምክንያት የዋጋ ማሻቀብ እየታየበት እንደመጣ ይታወቃል፡፡ አሁን የመኪና ዋጋ በአማካይ 450,000-750,000 ብር እንደሚደርስ ይነገራል፡፡ መኪና መግዛት ከፍተኛ ወጪ የሚፈልግ ጉዳይ እንደሆነ ይህ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ በሌሎች ሀገሮች እንደሆነው ከቤት ቀጥሎ በጣም ውድ የሆነ ከፍተኛ ገንዘብ የሚፈልግ ነገር ቢኖር የመኪና ግዢ ነው ሊባል ይችላል፡፡
የግዢ ሂደቱ ከተፈጸመ በኋላም ቢሆን መኪና ማንቀሳቀስ እንደ ነዳጅ፣ ዘይት፣ ኢንሹራንስ እንዲሁም ጥገና የመሳሰሉ ቀላል የማይባል የገንዘብ ወጪን በየጊዜው በተጨማሪ የሚፈልግ ውሳኔ ነው፡፡
ስለዚህ መኪና መግዛት ዕቅድህ ውስጥ የሚኖር ከሆነ እነዚህ ወጪዎች ከውሳኔ በኋላ የምታስወግዳቸው ባለመሆናቸው ለነዚህ ወጪዎችም ጭምር በቂ ቁጠባ የማድረግ ቅድመ ዝግጅት አስፈላጊ ነው፡፡ ግዢው በብድር የሚፈፀምም ከሆነ ከቤት ግዢው ጋር የተነሱት መንገዶችና ጥቅሞች ለመኪና እንዲሁም ለሌሎች ትልልቅ ግዢዎችም በተመሳሳይ መልኩ ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡
ለትምህርት እና ለስልጠና
አሁን ላይ እንደሚታየው የኮሌጅ ትምህርት (የልጆች ትምህርትንም ጨምሮ) ክፍያዎች እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ ለምሳሌ የትምህርት ደረጃህን ለማሻሻል ብታቅድና የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ለመከታተል ብትወስን ትምህርቱን ለመከታተልና ለመጨረስ በአማካይ ከ100,000.00 ብር ያላነሰ ገንዘብ መክፈል ይጠበቅብሀል፡፡ ትምህርትህን በውጪ ተቋማት ለመከታተል ከፈለግህ ደግሞ ከዚህ በጣም የጨመረ ገንዘብ እንዲኖርህ ይጠበቃል፡፡ ከዚህም በመነሣት ራስን በትምህርትና በስልጠና ብቁ ማድረግ አንድ ራሱን የቻለ በዓላማ መቆጠብን የሚፈልግ ጉዳይ እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡
ከሚመጣ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ አደጋ ለመከላከል
ከሥራ በተለያየ ምክንያት መቀነስ ወይም መገለል ቢያጋጥምህ ሌላ ሥራ እስክታገኝ ድረስ መሸፈን የሚኖርባቸው ወጪዎች ለመሸፈናቸው ማረጋገጫ የሚሰጠህ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩልም መሥራት ስላለብህ ሳይሆን በፍላጎትህ መሰረት የምትሠራበትን ዕድል እስክታገኝ ድረስ ጊዜ የሚገዛልህ ሲሆን፤ እንደዚሁም ያልታሰበ ህመም ቢከሰት የተሻለ ህክምና የማግኘት ምርጫም እንዲኖርህ ያደርጋል፡፡ ለዚህም ለድንገተኛና ለአስቸኳይ ጊዜ የሚሆን በአዳጊ አገራት ለሚኖር ሕዝብ በትንሹ የ6ወር ወጪን የሚሸፍን ተቀማጭ ገንዘብ እንዲኖርህ ብዙ የፋይናንስ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
ይህ ለሁሉ ይሳካል ባይባልም ገንዘብ የተወሰኑ ነጻነቶችን ሊሰጥ እንደሚችል ይነገራል፣ ነገር ግን ይህ ነጻነት ዝም ብሎ የሚገኝ አለመሆኑም ሊሠመርበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም ለዚህ ሁሉ በቂ የሆነ ገንዘብ እንዴት ማግኘት ይቻላል የሚለውን ጥያቄ ሲያስነሳና ወደ መፍትሔው እንድትመለከት የሚያደርግ ስለሆነ ነዋ! ከዚህ ጋር በተያያዘ አንደኛው መንገድ የሚሆነው የሚያስፈልገህ የገንዘብ መጠን እንዲከፈለህ ሆነህ መገኘት ወይም ማድረግ ሲሆን ፣ ሌላኛው እና አንደንዴም ብቸኛው መንገድ በጥቂት በጥቂቱ ለረጅም ጊዜ በመቆጠብ ጥሪት ማኖር ነው፡፡
በጡረታ ወቅት ሊፈጠር የሚችልን የበጀት ክፍተት ለመሙላት
አሁን ላይ በደመወዝ እንዲሁም ከጡረታ በኋላ ደግሞ በጡረታ ክፍያ ብቻ ለመኖር የሚያቅድ እንዲሁም በዚህ ስሌት የሚኖር አይጠፋም፡፡ በርግጥ በዚህ ወቅት ለምትሠራው ሥራ በሚከፈልህ ደሞዝ ለመኖር የሚያስችልህ ሁኔታ ይኖር ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለጡረታ በምትደርስበት ወቅት አሁን ላይ ያለህን የፍላጎት መጠንና ዐይነት ተመሳሳይ ባይሆንም የጡረታ ክፍያ የዛን ወቅት የኑሮ ሁኔታ እንዲሁም የገንዘብ የመግዛት አቅምን ባገናዘበ መልኩ በሚገባ ማስተካከያ የተደረገበት እና ለመሠረታዊ ፍላጎትህ በሚቀርብ መልኩ ተሰልቶ የሚደርስህ አይደለም፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ የሚሆነው አሁን ላይ በአገራችን የጡረታ ክፍያቸው ከ 2000 ብር በላይ የሆኑ ግለሰቦችን ቁጥር ግምት ውስጥ መክተት ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ወርሃዊ የጡረታ ክፍያቸው 19 ብር የነበረ ግለሰብን እንደ ተጨማሪ ምሳሌ ማንሣት ጉዳዩን በሚገባ ይገልጸዋል፡፡ መንግሥት የጡረተኞችን ክፍያ በቂ አለመሆኑን በመረዳት ማስተካከያ ባደረገበት በዚያ ወቅት 20 ሳንቲም ጭማሪ ነበር በማስተካከያነት የተደረገላቸው፡፡ በጊዜው ጭማሪው ወደ ኋላ የአንድ ዓመት በውዝፍ መልክ ተሰልቶ እንዲከፈላቸው ሲደረግ በእጃቸው የገባው ገንዘብ 2 ብር ከ 40 ሳንቲም ነበር፡፡ የክፍያ ማስተካከያውን በጉጉት ለዓመታት ለጠበቁ በዕድሜአቸው አገርን በትጋት ለአገለገሉ ግለሰብ በዚህ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉና ምን ዓይነት ስሜት እንደሚፈጠርባቸው እዚህ ጋር ማሰቡ በቂ ነው፡፡
ስለዚህ በጡረታ ጊዜ ሊፈጠር የሚችለውን የበጀት ክፍተት በግልህ ለመሙላትና ለማስተካከል ለጡረታ ጊዜ የሚሆን በቂ ገንዘብን መቆጠብ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻልክ በጡረታ ወቅት በምትፈልገው መልኩ ማረፍ ወይም ማሳለፍ በሚኖርብህ ወቅት የሚያስፈልጉህን ነገሮች ለሟሟላት ስትል ወደ ሥራ ለመሰማራት ትገደዳለህ ማለት ነው(እርሱም ሥራ የሚገኝ ከሆነ)፡፡
በ70 እና በ80 የሙት ዕድሜህ የአንተ ፍላጎት የውሃ ዳርቻ(የዋና ሥፍራ) ላይ ቁጭ ብለህ መጻሀፍትን ማንበብ፣ መጻፍ ወይም ሌላ ያልሠራሃቸውን የግል ሥራዎች መሥራት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እጅህ ላይ በቂ ገንዘብ ባለመኖሩ ምክንያት ያንን ወርቃማ ጊዜ በማትፈልገው መልኩ እንድታሳልፍ ይሆናል፡፡
ለጡረታ ጊዜ የምትጠቀምበት ገንዘብ ከወዲሁ ቆጥቦ ማስቀመጥ ጥሩ ነገሮችን እንዲኖሩህ ከማድረግ በተጨማሪ የደኅንነት ስሜትን (sense of wellbeing) ይገዛልሃል::
“በችኮላ የምትከማች ሀብት ትጎድላለች
ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች፡፡ “
ጠቢቡ ሰለሞን

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button