5 በበጀት ለመንቀሳቀስ የሚረዱ ወሳኝ እርምጃዎች

5 በበጀት ለመንቀሳቀስ የሚረዱ ወሳኝ እርምጃዎች

በጀት መበጀት ወጪዎቻችንን ለመከታተል እና ገንዘባችንን በብልሃት ለማስተዳደር ከሚረዱ ወሳኝ መንገዶች ውስጥ አንዱ ነው። በጀትን መጠቀም በርካታ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን፣ በዋናነት ግን ገቢና ወጪን በመከታተል የወደፊት ወጪን ለማቀድ፣ የወጪ ልማዶችን በማወቅ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ ለማድረግ ፣ እንደ ምግብ፣ ልብስ፣ ትራንስፖርትና መዝናኛ የመሳሰሉ የወጪ ምድቦች ላይ የበጀት ገደብ በማበጀት የገንዘብ ወጪን ለመቆጣጠር እንዲሁም ላልተጠበቁ ወጪዎች በተሻለ ሁኔታ ለመዘጋጀት ይገኙበታል፡፡ በዕለት ተዕለት ወጪያችን እና በቁጠባችን ላይ የምናደርጋቸው እያንዳንዱ ጥቃቅን ውሳኔዎች በረጅም ጊዜ ግባችን ላይ ዘላቂ ተፅዕኖ አላቸው። በበጀት አወሳሰን ላይ ቀድሞም ልምድ ያለን ቢሆንም እንኳ፣ የፋይናንስ ዕቅዳችንን በየጊዜው መልሶ መቃኘት እና አሁን ያለንበትን ሁኔታ በመረዳት ማስተካከያዎችን ማድረግ አስፈላጊ ነው። በበጀት መመራት ውስንነት ያለበት አና አስቸጋሪ ቢመስልም፣ እንደ ህይወት መመሪያ ስንከተለው ግን፣ በሚገርም ሁኔታ ሀይልን የሚያጎናፅፍ እና በገንዘብ አስተዳደር እጅግ ውጤታማ የሚያደርገን ነው።
ለዛሬ በበጀት ለመመራት የሚረዱ አምስት ወሳኝ እርምጃዎችን ለማንሳት እንሞክራለን፡-

  1. ገቢን ማስላት
    የበጀት አሠራር የመጀመሪያው እርምጃ አጠቃላይ አማካይ ወርሃዊ ገቢን ማወቅ ሲሆን ይህም በመደበኛነት የምንቀበለውን ደመወዝ፣ ቦነስ እና ከሌሎች የገቢ ምንጮች የምናገኘውን ይጨምራል፡፡ ይህም ከታክስ እና ሌሎች ተቀናሽ በኋላ የሚቀረን ሲሆን፣ ገቢያችን ከወር ወር የሚለያይ ከሆነ፣ ያለፉትን ከስድስት እስከ 12 ወራት ያገኘነውን የገቢ መጠን በአማካይ መገመት ወይም ማስላት ይቻላል። በጀታችንን ጠበቅ ያለ ለማድረግ፣ በተጠቀሱት ጊዜያት ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ካገኘንበት ወር የገቢ መጠን በመነሳት ማስላት ይቻላል፡፡ የግላችንን ሥራ የምንሠራ ከሆነም፣ የምንከፍለውን ታክስ እና ሌሎች የንግድ ሥራ ወጪዎችን ከጠቅላላ ገቢያችን ላይ መቀነሳችንን ማረጋገጥ ተገቢ ይሆናል።
  2. ቋሚ ወጪዎችዎን መዘርዘር
    ይህም ሁሉንም ተደጋጋሚ ወርሃዊ ወጪዎች ማለትም እንደ የቤት ኪራይ ወይም የመገልገያ ዕቃዎች ግዢ፣ የትራንስፖርት/የነዳጅ ወጪ፣ የገበያ እና ሌሎች መደበኛ ሂሳቦችን በዝርዝር ማስቀመጥ ማለት ነው። ቋሚ ወይም የተወሰነ ወጪ የሚባለው ከወር ወደ ወር ብዙም በማይለዋወጡ ዕቃዎች ግዢ ወይም የወጪ ምድቦች ላይ የምናወጣው ገንዘብ ነው። ከእነዚህም ውስጥ ከቤት አስተዳደር ጋር የተገኛኙ ወጪዎች ሲሆኑ፣ የቤት ኪራይ ወይም የብድር ክፍያ ሊካተቱበት ይችላል:: እንዲሁም እንደ የውሃ፣ ኤሌክትሪክ፣ ኢንተርኔት እና ሞባይል የመሳሰሉ የፍጆታ ክፍያዎች፣ የኢንሹራንስ አረቦን፣ የንብረት ታክስ እና እንደ የመኪና ብድር ያሉ የዕዳ ክፍያዎችንም ሊጨምር ይችላል።
  3. ወጪዎችን በምድብ መከፋፈል
    ወጪዎችዎን በቋሚ እና ተለዋዋጭ ምድቦች መከፋፈል አንዱ አስፈላጊ እርምጃ ነው:: ቋሚ ወጪዎች የማይለወጡ (ወይም ብዙ የማይለወጡ) ሲሆኑ፣ ተለዋዋጭ ወጪዎች ከወር ወደ ወር በመጠን ሊለዋወጡ የሚችሉ ናቸው።
    እንደ ቋሚ ወጪ ሁሉ ቁጠባ ማድረግም አንድ ሊታሰብበት የሚገባ ሌላ ወሳኝ ጉዳይ ሲሆን፣ ይህን ለማድረግ፣ በየወሩ ለመቆጠብ የሚፈልጉትን የገቢዎን መቶኛ በመወሰን እና መከፈል እንዳለበት እንደ አንድ ወጪ ወይም ሂሳብ በመቁጠር፣ ቁጠባን መለማመድ ያስፈልጋል። ለቋሚ ወይም መሠረታዊ ወጪዎች፣ የተወሰነ ወርሃዊ የገንዘብ መጠን ለመቆጠብ፣ አውቶማቲክ በሆነ መልኩ ገንዘብ ተቀማጭ የሚሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ማቀድም አንዱ ትኩረት ከሚፈልጉ ጉዳዮች መካከል ሊጠቀስ የሚችል ነው።
    ተለዋዋጭ ወጪዎች ከወር ወደ ወር በሚለዋወጡ ምድቦች ላይ የሚያወጡት ገንዘብ ሲሆን፣ ለምሳሌ ከቤት ውጭ ለመብላት፣ ለገበያ ወይም ለትራንስፖርት፣ በእያንዳንዱ ምድብ ውስጥ በየጊዜው ምን ያህል እንደምናወጣ ለማወቅ ያለፉትን የካርድ ወይም የባንክ ሂሳብ መግለጫዎችን መመልከት በቂ ነው። በተያያዘም አስፈላጊ ለሆነ ወርሃዊ አማካይ ወጪ ከየትኛው ምድብ ላይ መቀነስ እንዳለብንም በቀላሉ ለማወቅ ይቻላል።

ሌላው ለሥጦታ እና በእረፍት ጊዜያት በየወሩ የማይከሰቱ ወጪዎች ግምት ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ ለእነዚህ ጉዳዮች በዓመት ምን ያህል እንደምናወጣ በመገመት ማካተት የሚቻል ሲሆን። ከዚያም በ12 ወራት በማካፈል እና በጀት በመመደብ ገንዘቡን በየወሩ መቆጠብ ያስፈልጋል።

  1. የፋይናንስ ግቦችን ማስቀመጥ
    ገቢ እና ወጪን ካሰላን በኋላ ለግላችን የተወሰኑ የፋይናንስ ግቦችን ማስቀመጥ ሌላው በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ይህም ለቤት ግዢ ቅድመ ክፍያ፣ ለትምህርት፣ ለኢንቨስትመንት ወይም ዕዳ ለመክፈል ሊሆን ይችላል።
  2. ወጪያችንን በመከታተል ለውጥን መገምገም
    ከበጀት ውጪ ላለመንቀሳቀስ፣ ወጪያችንን መከታተል እና እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ ሲሆን፣ ይህን በቀላሉ ለማድረግ የሚያግዘንን ማንኛውም አይነት አጋዥ መሳሪያዎችን መሞከርና መጠቀምም ያስፈልጋል፡፡
    ከአስፈላጊ ወጪዎች በኋላ ከበጀት ማንኛውንም ተጨማሪ ገንዘብ እንዴት መጠቀም እንደምንችል ለማወቅ እንዲረዳን ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች በዝርዝር መያዝ። እንደ ግቦቻችን ፣ ለችግር ጊዜ ወይም ለኢንቨስትመንት የሚሆን ገንዘብን ማጠራቀም ለአንዳንድ ሰው የበለጠ ትርጉም ያለው ሊሆን ይችላል። ሌሎች ደግሞ ለጡረታ ጊዜ የሚሆን ገንዘብ ማጠራቀምን ሊመርጡ ይችላሉ፡፡ ዕዳ ለመክፈል ፣ ለልጆች የትምህርት ወጪ ወይም ቤት ለመግዛት የምናቅድ ደግሞ እንደዚሁ፡፡
    ባጠቃላይ ግን፣ በጀታችንን በየጊዜው መከታተል እና ስለ ወርሃዊ የቁጠባ እና የወጪ ልማዶቻችን ጥሩ ግንዛቤ ማግኘቱ በረዥም ጊዜ ብልህ የፋይናንስ ወይም ገንዘብ ነክ ውሳኔዎችን እንድናደርግ ብሎም በዚህ ረገድ ስኬታማና የተረጋጋ ህይወትን እንድንመራ ያስችለናል። ስለዚህ በዚህ አዲስ ዓመት የፋይናንስ ዕቅዳችን የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን እነዚህን ከበጀት ጋር የተያያዙ እርምጃዎች ለእያንዳንዳችን በሚበጀን መልኩ እንድንጠቀምባቸው እናበረታታለን፡፡

በአለማየው ስሜነህ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button