7 ለዳያስፖራ ቤት መሥሪያና መግዣ ብድር ብቁ የሚያደርጉ መሠረታዊ ሂደቶችና መስፈርቶች

7 ለዳያስፖራ ቤት መሥሪያና መግዣ ብድር ብቁ የሚያደርጉ መሠረታዊ ሂደቶችና መስፈርቶች

ቤት መግዛት ወይም የቤት ባለቤት መሆን እጅግ አስደሳች ነገር ነው። ነገር ግን የቤት/የንብረት ግዢን በብድር የመፈጸም ሂደትን እንዲሁም ከብድር ጋር በተያያዘ ከመስፈርቶቹ ጀርባ ያለውን ዓላማ በሚገባ ወይም በበቂ ሁኔታ ላልተረዳ ሰው ግን ትንሽ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ሰዎች እንዲያውም ማሟላት የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች እንዲሁም ተያያዥ የወረቀት ሥራዎች ሲሰሙት ገና በማሰብ ብቻ የተወሳሰበ ሆኖ ይታያቸዋል።

ሆኖም ሒደቱን በሚገባ በመረዳትና በየደረጃው ምን እንደሚጠበቅ አስቀድሞ በማወቅ ትክክለኛ የቤት ግዢ ውሳኔን ብሎም ቤትን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶችን የማፍራት ጉዞን ቀላል ማድረግ ይቻላል።

የቤት ግዢን በሚመለከት በተለያየ ሀገራት በሚገኙ ኤምባሲዎች፣ በየኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ እንዲሁም በተለያዩ ሪል እስቴቶች በኩል የሚሰጡ የተለያዩ መረጃዎች ያሉ ሲሆን፣ ለዛሬ በዚህ ጽሑፍ ዳያስፖራ የቤት መሥሪያና መግዣ የብድር አገልግሎት በአቢሲንያ ባንክ በኩል ሂደቱ ምን እንደሚመስልና መሟላት ያለባቸው ብቁ የሚያደርጉ መሠረታዊ ጉዳዮችንና መስፈርቶችን በተወሰነ መልኩ እንደሚከተለው ለመዳሰስ ተሞክሯል።

የብድሩ አሠጣጥ ሂደትና መስፈርቶች፡-

1-የብድር ጥያቄ ማመልከቻ ለባንክ ከመቅረቡ እንዲሁም ሊገዛ የታቀደው ቤት/ንብረት ከመፈለጉና ከመመረጡ አስቀድሞ አመልካቹ የመበደርና የመግዛት አቅሙን ግምት የሚመለከታቸው የብድር ባለሙያዎች ጋር ቀርቦ ማሰላትና ማወቅን የመጀመሪያ ርምጃ አድርጎ ሊወስደው ይገባል። ይህን በማድረግ በዋጋ ግምት ልዩነት ሊፈጠር የሚችል ተጨማሪ ሂደትን ወይም ልፋትን መቀነስ ይቻላል።

2-በቀጣይም ከመበደር አቅም ጋር በተያያዘ ሌላ ውሳኔ የሚፈልገውን የቅድመ መዋጮ/Equity መጠንን በስምምነት መወሰንና በውጭ ምንዛሪ በሚከፈት የባንክ ሂሳብ ውስጥ ማስገባት ወይም መክፈል ይኖርበታል። በዚህም የመኖሪያ ቤት/የንብረት መግዣውን ዋጋ በመቶኛ ተሰልቶ ማዋጣት ይጠበቅበታል። አዚህ ጋር የተለያዩ አማራጮች ያሉ ሲሆን፣ ተያያዥ ጉዳዮችን ከባንኩ ጋር በመነጋገር ለደምበኛው ምቹና ቀላል የሆነ የግዢና የክፍያ መንገድ ሊመቻች ይችላል፡፡

3-ዳያስፖራው አገልግሎቱን ለመጠቀም የሚከተሉትን ዝርዝር ሰነዶችና ሁኔታዎች በሂደት ማሟላትም ይኖርበታል፡-

~ተቀባይነት ባላቸው የውጭ ገንዘቦች በአንዱ የሚከፈል መሆኑን፣ ጠቅላላ የደሞዝ መጠን እና የተጣራ ገቢን የሚገልጽ ከቀጣሪው የተሰጠ የቅጥር ደብዳቤ
~የቅጥር ደብዳቤው የቅጥር ቀን፣ ዓመታዊ/ወርሃዊ ገቢ፣ ቀድሞ የተወሰደ የብድር መጠን (ካለ) ተጠቅሶ እንዲገለፅበት ይፈለጋል፡፡ ይህን ሰነድ ጨምሮ ሌሎችም ከውጭ የሚገኙ ሰነዶች በኢትዮጵያ ኢምባሲ እና በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቢሮ በኩል ተረጋግጠው (Authentication) መምጣት ይኖርበታል፡፡
~ አመልካቹ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነ የውጭ ዜጋ ከሆነ የታደሰ ፓስፖርትና የትውልደ ኢትዮጵያዊያን መታወቂያ (ቢጫ ካርድ)
~ የጋብቻ የምስክር ወረቀት ወይም ያላገባ ከሆነ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ሰነድ
~ከውጭ ሀገር ባንክ የሚላክ ቢያንስ የአንድ ዓመት የሒሳብ መግለጫ
~አመልካቹ ኢትዮጵያዊ ከሆነ የታደሰ ፓስፖርት የመኖሪያ እና/ወይም የስራ ፈቃድ
~ አመልካቹ ሁለት የቅርብ ጊዜ የፓስፖርት መጠን ያለው ፎቶግራፍ
~የአገልግሎቱ ጥያቄ የቀረበው በወኪል አማካኝነት ከሆነ የተወካዩ የታደሰ መታወቂያ ኮፒ ፣ ሁለት የታደሰ ፓስፖርት መጠን ያለው የቅርብ ጊዜ ፎቶ ግራፍ እና የውክልና ማስረጃ
~ የቅጥር ውል ኮፒ
~አመልካቹ በንግድ ሥራ የሚተዳደር ከሆነ ቢያንስ የሦስት ተከታታይ ዓመታት የሒሳብ ዝርዝር መግለጫ
~የታደሰ የንግድ ፈቃድ እና የንግድ ምዝገባ የምሰክር ወረቀት እና
~የግብር ክፍያ ምስክር ወረቀት ማቅረብ ይኖርበታል
~የሽያጭ ሒደቱ ከተናቀቀ በኋላ ደንበኛው የሚጠበቅበትን ወርሃዊ ክፍያ በባንኩ ተቀባይነት ባላቸው የውጭ ገንዘቦች (ዶላር፣ ፓውንድ ወይም በዩሮ) ወይም እንደስምምነቱ በብር በወቅቱ መፈጸም ይጠበቅበታል
~የመድን ዋስትና/ብድሩ ከተፈቀደ በኋላ/
~ንብረቱን/ቤቱን በሚሸጠው አካልም በኩል የተወሰነ እንደ የጋብቻ ሁኔታን የሚገልጽ ሰነድ የመሳሰለ መሟላት የሚኖርባቸው ሰነዶች ይኖራሉ

ከሥራ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ወይም በተለያየ ምክንያት ከላይ የተጠቀሱትን ሰነዶቸ ማሟላት ያልቻሉ አመልካቾች (እንደ የቤት ሠራተኞች፣ የልጅ አሳዳጊዎች፣ የአስተናጋጅነት እና የጥበቃ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሊሆኑ ይችላሉ) የሚስተናገዱበት መንገድ ያለ ሲሆን፣ የመዋጮ ቁጠባው እንዲሁም ብድሩ ተከፍሎ የሚያልቅበት ጊዜ በስምምነት የሚወሰን ይሆናል።

ሆኖም ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎችና ሠነዶች እንደአሰፈላጊነታቸው ዝርዘሩ ሊያንስ ይችላል፡፡

4-በመቀጠልም ለግዢ የተመረጠው ቤት ወይም ንብረት ኦሪጅናል ካርታ እና ፕላን ኮፒ ባንክ ዘንድ ቀርቦ በባንኩ በኩል በቀጣይ በሚደረግ ቀጠሮ በምህንድስና ባለሙያ የንብረቱ ዋጋ እንዲተመን ይደረጋል።

5-የሽያጭ ስምምነቱም ከተፈጸመ በኋላ የሽያጭ ውሉ ከብድር ማመልከቻው ጋር ተሟልቶ መቅረብ ይኖርበታል። ነገር ግን የብድሩ ዓላማ ለግንባታ፣ ለእድሳት እንዲሁም ብድሩ ከወለድ-ነጻ የባንክ አገልግሎት ማዕከል በኩል የሚስተናገድ ከሆነ የብድር አሠጣጡ በተወሰነ መልኩ ከዚህ የተለየ ሂደት ይኖረዋል።

6- የሚገዛው ቤት ወይም ንብረት ለብድሩ መያዣ እንዲሆን፣ ከብድርና ከመያዣ ውል ፊርማ በኋላ በሚመለከተው የንብረት ምዝገባ ቢሮ በመያዣነት ይመዘገባል
7-በመጨረሻም ተያያዥ የኢንሹራንስ፣ የቀረጥና የአገልግሎት ክፍያዎች ተፈጽመው ብድሩ ለንብረት ሻጭ አካል (ሪል እስቴት፣ ማሀበር ወይም ግለሰብ ሊሆን ይችላል) እንዲለቀቅ ይደረጋል።

በአለማየሁ ስሜነህ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button