የገና በዓል የመጠያየቅ እና ስጦታ የማበርከት ትውፊት

የገና በዓል የመጠያየቅ እና ስጦታ የማበርከት ትውፊት

በሰው ልጆች ላይ የደረሰው የዘመናት ፍዳ፣ ከተስፋ በስተቀር ነገን አሻግረው የሚያዩበት ቀዳዳ ትንሽ ነው፡፡ የብሥራቱን ዜና ለመስማት፣ ወደ አዲስ ዘመን ለመሸጋገር ብዙ ሥቃይ እና ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ ግድ ብሏል፡፡ በዚህ የፍዳ ወቅት በየጊዜው የተነሡ ነቢያት፣ ሰዎችን በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዳይወድቁ ቢያበረቱም፤ ጊዜው የመርገም በመሆኑ አንዳቸውም ለጽድቅ አልበቁም፡፡
በኀዘን ውስጥ ደስታን ማሰብ፤ በመውደቅ ውስጥ መነሣትን፤ በጨለማ ዓለም ውስጥ ዘለዓለማዊውን ብርሃን መናፈቅ እንዴት ይቻላል? ግን ይኽ ለሰው ልጆች የተሰጠ የመቻል ጸጋ ነው፡፡ ከሚናፈቀው ዓለም ለመድረስ፣ ከአድማስ ባሻገር ለማየት ያቺን ቃል ማሰብ በቂ ነበር…. “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለሁ”….፡፡
የመወለዱን ብሥራት ከእረኞች ጀምሮ እስከ ሰብዓ ሰገል ድረስ የሚናፍቁት ብዙ ናቸው፡፡ ቃል በያዘው ተስፋ ሕያው ሆኖ ድኅነት በሰው ልጆች ላይ ይደረግ ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ፡፡ እነኾ! ይኽንን ዜና መስማት የሚፈልጉ፣ ድቅድቁን ይገለጥ ዘንድ ጮራውን የናፈቁ ብዙዎች ወደ ቤተ ልሔም ተመሙ፡፡ ጌታችንን በከብቶች በረት አገኙት፡፡ መልካም ልደት በማለት ስጦታ አበረከቱለት፡፡
የዕልፍ ዘመናት ባለቤት ኢትዮጵያ፣ በጨለማም በብርሃንም የተጓዘችባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው፡፡ ችግርና መከራ፤ ጦርነትና ስደት፤ ረኀብና ጥማት አገርን ከመሥራት፣ ለመጨው ትውልድ አይረሴ ቅርስና ታሪክ ከማውረስ ኢትዮጵያውያንን አላስቆማቸውም፡፡ ሰማይን ጠቅሰው አክሱምን ማቆም፤ ምድርን ቧጥጠው ላሊበላን መገንባት፤ ለጠላት እጅ ከመስጠት የሞት ጽዋዕን መጠጣት፤ ወራሪን በማዋረድ ዐድዋን መትከል አላገዳቸው፡፡ ምክንያቱም የሥቃዩ ዘመን ተስፋ ባለመቁረጥ መጪውን ጊዜ አሻግረው በማየት ብቻ ሳይሆን በመኖርም ጭምር አገር መገንባት ያውቁበታል፡፡
በአያቶቻችን ቅብብሎሽ እዚህ የደረሰችው ኢትዮጵያ፣ የለውጥ ጀንበሯን ለማዘቅዘቅ እና ወደ ጨለማው ዘመን ሊዶሏት ጠላቶችዋ ዛሬም አላንቀላፉላትም፡፡ ባልደረቀ ቁስሏ ላይ ከአኩሪ ታሪኮቿ እኩል መጥፎ ጠባሳን ለማንበር ሰርክ እየደከሙ ነው፡፡ በተለይም ሰሞነኛው የአገራችን ሁኔታ በርካቶችን ለሞት፣ ለስደት እና ለረኀብ ዳርጓል፡፡ ነገር ግን ንጉሡን በከብቶች በረት መወለዱ ከፍታውን አላስቀረውምና ኢትዮጵያ ከገባችበት ቀውስ ተዘፍቃ የምትቀርበት አንዳች ምክንያት አይኖርም፡፡ ትንሣኤዋ በመናፈቅ የሚተጉት ልጆችዋ ከገባችበት አዙሪት ያወጧታል፡፡
የገና በዓል የመጠያየቅ እና ስጦታ የማበርከት ትውፊት ያለው በመሆኑ ለአገር እና ለወገን ያለን ፍቅር በእንኳን አደረሳችሁ ብቻ ሳይወሰን በተለያዩ የስጦታና የዕርዳታ ተግባራት ልንገልጠው ይገባል፡፡ ከሩቅ አገር እንኳን ተወለድህ በማለት ለጌታ መብዓ ይዘው እንደ አመጡት ሰብዓ ሰገሎች፤ እኛም ከሀገር ውስጥም ሆነ ከሩቅ ወደ አገር ቤት ለበዓል የምንመጣው ኢትዮጵያውያን የእኛ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በተመሳሳይ አንድ ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
የነገ ትውልድ የሚሠራው በዛሬ ልጆች ጥረት ነውና ከድል ብሥራት ጀርባ ያለው መውደቅ አያስቆመንም፡፡ እንደ ትጉኃን ያለመታከት ያለንን ለአገራችን እንሰጣለን እናበረክታለን፡፡
አቢሲንያ ባንክ የታላቂቷን ስም በመሸከም ማኅበራዊ ግዴታን በመወጣት አገር የምትገነባበትን ጠጠር እያቀበለ ይገኛል፡፡ በዚህም በተለያዩ የዕርዳታ ሥራ ላይ ከተሠማሩ ስመ ጥር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየሠራ ይገኛል። እረስዎም ለፈለጉት የበኩሉዎትን እንዲያበረክቱ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፣ ይጎብኙ! donate.bankofabyssinia.com እነኾ! የልደት ብሥራት ሰምተው ያመሰገኑትን እረኞች እንድንሆን እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገና በዓል አደረሳችሁ አያለ መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡

ጸሐፊ ምኒልክ ብርሃኑ
ታኅሣሥ ፳፯ ቀን፣ ፳፻፲፬ ዓ.ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button