ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ከአቢሲንያ ባንክ ጋር በመተባበር ወገን ፈንድ የሚባል የኦንላይን የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ-ገፅ አስመረቀ!

ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ከአቢሲንያ ባንክ ጋር በመተባበር ወገን ፈንድ የሚባል የኦንላይን የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ-ገፅ አስመረቀ!

ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኃ.የ.ግ.ማ. ከአቢሲኒያ ባንክ ጋር በመተባበር ወገን ፈንድ የሚባል የኦንላይን የድጋፍ ማሰባሰቢያ መተግበሪያ ዛሬ ታህሳስ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. አስመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

በተዘጋጀው የቨርቹዋል የምረቃ ስነ ሥርዓት ላይ ጥሪ የተደረገለቻው የክብር እንግዶች፣ የግብረ ሰናይ ተቋማት ተወካዮች እና በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተገኙ ሲሆን፣ ወገን ቴክኖሎጂ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ካላቸው ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ አንጻር በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ደጋፊዎቻቸውን የሚያስተባብሩበት እና ድጋፍ የሚያገኙበት እንዲህ ያለ መተግበሪያ/platform/ መኖሩ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጿል።

አምባሳደር ተፈሪ መለሰ፣ በዩኬ እና አየርላንድ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር፣ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በሁሉም ዘርፎች ራሳችንን መቻል እንደሚገባን ገልጸው ነዋሪነታቸውን በውጪ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ፣ በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እና በሌሎችም መስኮች ለሀገራቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አድንቀዋል። በሌሎች የውጪ ሀገር የድጋፍ ማሰባሰቢያ ቴክኖሎጂዎች ላይ ከመመርኮዝ ይልቅ “የራሳችን በሆነው ወገን ፈንድ መጠቀምና ይኼንኑ ቴክኖሎጂ ማበረታታ ለዘላቂ ትልማችን አማራጭ የሌለው ስለሆነ ሁላችንም ይህንን ጅምር በማበረታታት ለጋራ እድገት በጋራ እንድንቆም” ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ወ/ሮ ፈሰሴ ገ/ሃና፣ የወገን ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስኪያጅ ባሰሙት ንግግር ደግሞ “ወገን ፈንድ ዋነኛ ትኩረቱ በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ በጎ አድራጎት ድርጅቶች፤ የሃይማኖት ተቋማት እና ማህበራት፣ እንዲሁም የጤና እክል ገጥሟቸው የወገን እርዳታ ከሚፈልጉ ግለሰቦች ጋር፣ የሀገራችን የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን ሕጋዊ ገቢ የማሰባሰቢያ እንቅስቃሴዎችን፣ በግሉ ዘርፍ በባንኪንግ ቴክኖሎጂ ግንባር ቀደም ከሆነው ከአቢሲኒያ ባንክ ጋር በመሆን መስራት ነው” ብለዋል።

አቶ አባይ ስሜ፣ የአቢሲኒያ ባንክ፣ የኦንላይን ባንኪንግ አገልግሎት ዳይሬክተር በበኩላቸው አቢሲኒያ ባንክ አለም አቀፍ የክፍያ ቴክኖሎጂን በኢትዮጵያ ለመጀመር ቀዳሚው ባንክ መሆኑን በማስታወስ “ልግስናን እንደ አንድ መገለጫው አድርጎ ለሚያይ ማኅበረሰብ ይኅንን መልካም ተግባሩን የሚያዳብርበት የቴክኖሎጂ መላ ማበጀት እጅግ የሚደነቅ ሥራ ነው” በማለት ለወገን ቴክኖሎጂ ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ “በጊዜ እና በቦታ ሳይገደብ ሁሉም ዜጋ የአቅሙን አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችልበትን መንገድ በማመቻቸቱ ሥራ ላይ አንድ ባለድርሻ አካል ሆነን ከወገን ቴክኖሎጂ ጋር በመሥራታችን እጅግ ኩራት ይሰማናል” ብለዋል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ከ350 በላይ የሚሆኑ የሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ስብስብ የሆነውን “የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ህዝብ” የተሰኘውን ጥምረት ጨምሮ የተለያዩ ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አባላት እና የቦርድ አባላት የተገኙ ሲሆን ለኢትዮጵያም ሆነ ለአህጉራችን አፍሪካ የሚድያ እና የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ፣ ሀገራችን ካለችበት ሁኔታ አንጻር ወገን ፈንድ ወሳኝ ወቅት ላይ እንደደረሰ እና ሳታዳሉ ሁሉንም የሲቪክ ማኅበራት ለማገልገል በመነሳታችሁ እናመሰግናለን የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።

የወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ዳይሬክተር እና መስራች ዶ/ር በላቸው ጨከነ እንዲሁም ሌላኛው መሥራች እና ዋና ዴቬሎፐር አቶ ሚሊዮን አጀበ ወገን ፈንድ ነባሩን የኢትዮጵያውያን የመረዳዳት ባህል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን፤ ወገን ቴክኖሎጂ የተመሠረተው በውጪው አለም፣ በተለያዩ መስኮች፣ ከአሥር አመት በላይ ልምድ ባካበቱ ባለሙያዎች እንደሆነ፤ እንዲሁም የወገን ቴክኖሎጂ አላማ ወደሃገራችን የሚደረገው የቴክኖሎጂ እና እውቀት ሽግግር ላይ አስተዋጽኦ ማበርከት በወደዱ ፣ የኢትዮጵያ ልጆች በሚያዘጋጇቸው ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን እንዲችሉ ማስቻል እንደሆነ ገልጸዋል።

ወገንፈንድን www.wegenfund.com ድህረ ገፅ ላይ ማግኘት ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button