ባንካችን አቢሲንያ ትናንት ጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም በጋምቤላ ከተማ በድምቀት በተጀመረው የፋይናንስ ዕውቀት ሳምንት (Financial Literacy Week) የመክፈቻ መርሃ-ግብር ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡
“የፋይናንስ ትምህርትን ማጎልበትና የደንበኞች ጥበቃን ማጠናከር” በሚል መሪ ቃል በሃገር-አቀፍ ደረጃ እየተካሔደ በሚገኘው በዚህ የመክፈቻ ፕሮግራም ላይ የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ-መስተዳድር ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድን ጨምሮ፣ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛል፡፡
የባንካችን ተወካዮችም ባንካችን አቢሲንያ በደንበኞች ጥበቃ ዙሪያ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነና ከእነዚህም መካከል የደንበኞች የጣት አሻራና የፊት-ገጽታ መረጃ ምዝገባ ዋነኛው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ባንካችን በቅርቡ የጀመረውን የወረቀት አልባ የባንክ አገልግሎትና ለህብረተሰባችን ይበልጥ ተደራሽ ለመሆን በየጊዜው የሚያወጣቸውን ፕሮዳክቶች በዋናነትም የአፖሎ ዲጂታል ባንክን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡
መርሃ-ግብሩ ሃገር አቀፉን የፋይናንስ ትምህርት ስትራቴጂ መሰረት በማድረግ የሴቶችንና ተጋላጭ የሆኑ ህብረተሰብ ክፍሎችን የሞባይል ፋይናንስ እና የዲጂታል ባንኪንግ ዕውቀት ከፍ ማድረግን አላማው ያደረገ እንደሆነ በመድረኩ ተገልጿል። በዚህም ወደ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶች ከነሱም ውስጥ ግማሽ የሚሆኑ ሴቶችን የትኩረት ማዕከል አድርጓል።
እስከ መጪው አርብ ጥቅምት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በሚቆየው በዚህ መርሃ-ግብር የማህበረሰብ አቀፍ ወርክሾፕ፣ የመድረክ ውይይቶች፣ የመስክ ጉብኝቶች፣የተለያዩ ስልጠናዎች እና አውደ ጥናቶች ተካትተዋል።

Leave a Reply