ስለዓለም አቀፍ የንግድ ፋይናንስ አሠራርና ሂደትሊታወቁ የሚገባቸው መሠረታዊ ነጥቦች
የአገራችን የውጭ ንግድ ተሳትፎና አፈፃፀም ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መምጣቱንና ወደ ውጪ የላክናቸው እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባናቸው ምርቶች እና አገልግሎቶች ጠቅላላ ዋጋ ድምር 27.6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደ ደረሰ በ2020/21 የታተመው የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ያሳያል፡፡ በእዚህ ለኢኮኖሚ ብልፅግና ቁልፍ የሆነ ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፎአችንን ከዚህ በላይ ማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ ይታመናል፡፡
ሆኖም ዓለም አቀፍ ንግድ ከሩቅ ሲታይ ቀላልና ቀጥተኛ ቢመስልም፣ በሂደቱ በርካታ ነገሮችን የሚያካትት እጅግ ሠፊ እንዲሁም መሥፈርቶችና ቅድመ-ሁኔታዎች ተሟልተው ሻጩ ወይም ላኪው ክፍያ ተቀብሎ ፣ ገዢው ምርቶቹን ወይም አገልግሎቶቹን አግኝቶ ግብይቱ እስኪፈፀም ድረስ ባለው ሂደት ውስጥ የተለያዩ ተግዳሮቶች ሊያጋጥሙ የሚችሉባቸው በርካታ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን፣ እንዴት ይከናወናል የሚለውም አሁን ድረስ የአንዳንዶች ጥያቄ ነው::
ዓለም አቀፍ የንግድ ፋይናንስ/አገልግሎት ሥርዓት የባንክን እንዲሁም የሌሎች ተቋማትን ምርቶችና አገልግሎቶችን ጭምር አጠቃሎ የሚመለከት ጉዳይ ሲሆን፣ እንደ የዓለም ንግድ ድርጅት ገላፃ ከ80-90 በመቶ የሚሆነው የዓለም ንግድ፣ በንግድ ፋይናንስ ወይም በባንኮች የንግድ አገልግሎት ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡
በመሆኑም አሠራሩን፣ በየአገራቱ የሚኖሩትን ወይም የዓለም አቀፍ ተያያዥ የንግድ ህግጋትን፣ አገልግሎቶችን፣ ፅንሰ-ሃሳቦችን፣ የዓለም አቀፍ ንግድ ምክር ቤት የሚያሳትማቸውን /ICC Publications የአሠራር ሥርዓት (Incoterms 2010, UCP-600, URC-522, UCP 500, URDG 758, ISP 98, …) ጭምር በመገንዘብ ከሽያጭ ውል ስምምነት አንስቶ፣ በእያንዳንዱ ደረጃ የተለያዩ ተፈጥሮአዊ ስጋቶችን /Inherent Risk በሚገባ መገምገምና በምን መንገድ ስጋቶችን መቀነስ እንደሚገባ አስቀድሞ መረዳት ያስፈልጋል፡፡
በዚህ ፅሁፍም ለዛሬ የውጭ ንግድ ፋይናንስ እንዴት እንደሚሠራ፣ በመሠረታዊ ደረጃ መታወቅ የሚገባቸውን ሂደቶች እና ከአሠራሩ ጀርባ ያለውን ፅንሰ-ሐሳብ እንደመነሻ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡
የውጭ ንግድ /Foreign Trade አገልግሎት እንዴት ይከናወናል?
የውጭ ንግድ ፋይናንስ ወይም አገልግሎት የሚሠራው ባንኮችን እንዲሁም ሌሎች ተቋማትን የንግድ ሂደቱ ውስጥ በማሳተፍ ሲሆን፣ በዚህም ባንኮች ወይም የገንዘብ ተቋማት ምርቶችን ወደ ዉጪ ለሚልኩና ከውጪ ለሚያስገቡ ኩባንያዎች ወይም ግለሰቦች ዓለም አቀፍ ንግድ ለማከናወን የሚያግዙ የተለያዩ አገልግሎቶችን በማቅረብ ንግድ በቀላሉ እንዲሳለጥ ያደርጋሉ፡፡
የእነዚህ የንግድ ፋይናንስ አገልግሎቶች መኖር ዋናው ምክንያት የገዢንና የሻጭን በግብይት ሂደቱ ሊገጥሙ የሚችሉ ጋሬጣዎች እንዲሁም ተግዳሮቶች መቀነስ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆን አንድ ምሳሌ እንመልከት፡-
አንድ በኢትዮጵያ የሚገኝ የመኪና ባትሪ አከፋፋይ ኩባንያ፣ የተለያዩ የመኪና ባትሪ ምርቶችን በህንድ ከሚገኝ አምራች ወይም ሻጭ ሊገዛ ይፈልጋል እንበል፡፡ በህንድ የሚገኘው ላኪ ወይም ሻጭ ምርቶቹን ለመሸጥ ቢፈልግም የምርቶቹን ሙሉ ክፍያ አስቀድሞ ካላገኘ ምርቶቹን መላክ አይፈልግም፡፡ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኘውም የባትሪ አስመጪና አከፋፋይ ምርቶቹን ሳይረከብ አስቀድሞ መክፈል አይፈልግም፣ ይህ የሚሆንበት ግልፅ ምክንያት ደግሞ፣ ሻጩ ምርቶቹን ከሚፈልግበት ጊዜ በላይ ሊያዘገይበት ወይም ገንዘቡን ተቀብሎ ከእነ ጭራሹ ምርቶቹን ላይልክ ለሚችልበት አደጋ ስለሚጋለጥ ነው፡፡
ስለዚህም በሁለቱም ወገን በኩል በሚኖር አሳማኝ ምክንያት፣ ቀጥታ ግንኙነት እና ልውውጥ ንግዱ ወይም ግብይቱ ሊከናወን አይችልም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የሁለቱ ድርጅቶች ግብይት ሊከናወን የሚችልበት መንገድ የሚሆነው፣ ሁለቱም ወገኖች የባንኮችን እንዲሁም የሌሎች ተቋማትን የንግድ አገልግሎት መጠቀም ሲችሉ ነው፡፡ ለዚህ ነው የግድ የባንኮች እንዲሁም የሌሎች ተቋማት ተሳትፎ አስፈላጊ የሚሆነው፡፡ እነዚህ ግብይቶች እንዲከናወኑ ደግሞ በባንኮች በኩል የሚቀርቡት በርካታ የውጭ ንግድ ፋይናንስ እና ሌሎች የአገልግሎት አማራጮች ዓይነተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡
በመሆኑም፣ ከላይ እንደ ማሳያ ያነሳናቸውን የኢትዮጵያና የህንድ ድርጅቶችን ጉዳይ መለስ ብለን ስንመለከት፣ የባንኮች በንግድ ሂደት ውስጥ መሳተፍ በገዢና ሻጭ በኩል የነበረውን፣ ምርቶቹን ልኮ ያለመከፈልና አስቀድሞ ክፍያውን ፈጽሞ ምርቶቹን ያለማግኘት አደጋን በከፍተኛ ደረጃ ከመቀነስ ባለፈ ንግዱ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ያስችላል፡፡
በዓለም አቀፍ ወይም የውጭ የንግድ ፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ እንደ ቅድመ ክፍያ/Advance Payment፣ ካሽ አስቀድሞ አስገብቶ ሰነድ የሚለቀቅበት/ Cash Against Document/፣ የዱቤ ሽያጭ/Open Account/፣ ኮንሳይመንት/ Consignment/ የመሳሰሉ፣ የተለያዩ የክፍያ ዘዴዎች/Modes of Payments/ ያሉ ሲሆን፣ ለተነሳንበት ርዕሰ ተስማሚ የሆነውን እና ዕቃ ለማስመጣት በኢትዮጵያ ከተፈቀዱ የግብይት መንገዶች መካከል አንዱን በመጠቀም የንግድ ፋይናንስ ሂደት ምን እንደሚመስል እንመለከታለን፡፡
የመተማመኛ ሰነድ/Letter of Credit
የመተማመኛ ሰነድ (L/C) በጣም የተለመደ እና ከብዙ አመታት በፊት ጀምሮ ሲሰራበት የቆየ ሲሆን፣ አንድ ገዢ ምርቶቹ እና ተያያዥ አስፈላጊ ሰነዶች ተሟልተው ከተላኩ እንዲሁም ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ በኋላ፣ መከፈል የሚገባው ሙሉ ክፍያ በወቅቱ እና በትክክለኛው መጠን ለሻጭ እንደሚደርሰው ገዥን ወክሎ ባንኩ ዋስትና የሚሠጥበት፣ እንዲሁም ገዢው ክፍያውን መፈፀም በማይችልበት ጊዜ፣ ሙሉውን ወይም ቀሪውን የግዢ ክፍያ መጠን እንዲሸፍን የገዢውን ባንክ የሚያስገድድ የውል ስምምነት ነው፡፡
ምንም እንኳን በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ አሁን ላይ የመተማመኛ ሰነድ በፊት የነበረው መጠነ ሠፊ ግልጋሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ቢመጣም፣ አሁንም ድረስ ብዙዎች የሚመርጡትና የሚጠቀሙበት መገልገያ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ወደ አሠራሩ ወይም ዝግጅቱ ስንመጣ፣ በርካታ የመተማመኛ ሰነድ አይነቶች ያሉ ሲሆን፣ ዋና ዋናዎቹ Irrevocable L/C, Revocable L/C, Stand-by L/C, Confirmed L/C, Unconfirmed L/C, Transferable L/C, Back-to-Back L/C, Payment at Sight L/C, Red Clause L/C በመባል ይታወቃሉ፡፡
የንግድ ፋይናንስ አሠራር ሂደት
በገቢ/Import በኩል፣ የውጭ ምንዛሬ ፈቃድ ከተገኘና ተገቢው የውጭ ንግድ ፈቃድ/Permit በብሔራዊ ባንክ አሠራር መሠረት ከተሰጠ በኋላ የሚኖረው የውጭ ንግድ አገልግሎት አሠራርና ሂደት፡ –
የመጀመሪያው እርምጃ የሚሆነው ገዢና ሻጭ ወደ ባንኮቻቸው ከመሄዳቸው አስቀድመው ስለ ግብይቱ አከፋፈልና አላላክ ዝርዝር ሁኔታዎችን በውል አማካኝነት ስምምነት ያደርጋሉ፡፡ በርግጥ በሁለቱ ወገኖች መካከል እንደሚኖረው መተማመንና ትውውቅ ስምምነቱ በቃል፣ እንደ አሰፈላጊነቱ በኤሌክትሮኒክስ ወይም በወረቀትም ሊሆን የሚችል ሲሆን፣ ብዙውን ጊዜ በመጨረሻ የተስማሙበት እና የተፈራረሙበት ፕሮፎረማ ኢንቮይስ/Performa Invoice እንደ ውል/Contract የሚያገለግልበትም አጋጣሚ ይኖራል፡፡
ቀጥሎም ገዢው የውጭ ምንዛሬ ፈቃድን ተከትሎ ደንበኛ ወደ ሆነበት ባንክ ቀርቦ ለመተማመኛ ሰነድ/ L/C ማመልከት ወይም ባንኩ የሚያዘጋጀውን ቅፅ መሙላትና የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን ወደሚቀነስበት ሂሳብ ገቢ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ለዚህም የመተማመኛ ሰነድ ማመልከቻ ቅፅ ላይ መገለፅ የሚገባቸውን ዝርዝር ነገሮች አስቀድሞ ከሻጭ ጋር በተስማሙበት መሠረት ማድረግ እንዲሁም በፊርማና ማህተም ማረጋገጥን የሚጨምር ሲሆን፣ ከመተማመኛ ሰነዱ ጋር ፕርፎርማ ኢንቮይስ እንዲሁም ኢኒሹራንስ የተገባበት ሰነድ ተያይዞ የሚቀርብ ይሆናል፡፡
የገዢው ባንክ የመተማመኛ ሰነዱን ባንኮች በሚግባቡበት ሰነድ ቅርፅ፣ አስመጪው ደንበኛ የሞላውን ቅድመ ሁኔታዎችና መሥፈርቶች መሠረት አድርጎ እና አዘጋጅቶ ለሻጩ ወይም ለላኪው ባንክ ስዊፍትን በመጠቀም ይልካል፡፡ እዚህ ጋር የገዢ ባንክ ይህን የሚተገብረው የግብይቱን ሙሉ ገንዘብ እና ተያያዥ ክፍያዎችን አስቀድሞ በመሰብሰብ እንዲሁም ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠውን አሠራር ወይም መመሪያ በመከተል የሚስተናገድ ይሆናል፡፡በተጨማሪም እንደ ሁኔታው እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን የሰነዱን ዋጋ፣ ለአንድ ጊዜ ወይም በተዘዋዋሪ /Revolving/ መልኩ ሊጠቀምበት የሚችል በብድር መልክ ለገዢው ለአጭር ጊዜ ሊያመቻችለት ይችላል፡፡ ይህም የንግድ ፋይናንስ አገልግሎት L/C Margin Facility በመባል የሚታወቅ ነው፡፡
የሻጭ ባንክም /Advising bank/ መተማመኛ ሰነዱ እንደደረሰው የአገልግሎት ክፍያውን በመሰብሰብ ለሻጭ ወዲያውኑ የሰነዱን መድረስ ያሳውቀዋል ወይም የመተማመኛ ሰነዱን ይሰጠዋል፡፡
ከዚህ በመቀጠል ሻጩ ምርቶቹን ወይም ዕቃዎቹን የመተማመኛ ሰነዱ ላይ በተገለጸው መሠረት እንደ /Chamberized Commercial Invoice, Bill of Lading, Certificate of Origin, Packing List/ የመሳሰሉትን አሰፈላጊ ሰነዶች በማዘጋጀት ጭምር ፣ ምርቶቹን ወይም ዕቃዎቹን ከጫነ በኋላ ሰነዶቹን ለባንክ ያቀርባል፡፡ የሻጭም ባንክ ዝርዝር ቅድመ ሁኔታዎችን በመተማመኛ ሰነዱ ላይ በተቀመጠው መሠረት መከናወናቸውንና መሥፈርቶች መሟላታቸውን ካረጋገጠ በኋላ፣ ሰነዶቹን ለገዢ ባንክ /Issuing Bank በመልዕክት አስተላላፊ/Courier Service በኩል ይልካል፡፡ እንዲሁም ለሻጭ፣ ክፍያውን ከገዢ ባንክ ጋር ባለው ግንኙነትና መተማመን ከገዢ ባንክ ሳይደርሰው ወይም ክፍያውን ሳይጠብቅ ወዲያውኑ ለሻጭ ሊከፍለው ይችላል፡፡ ይህም Outward Bills Purchased (DOBP) በመባል ይታወቃል፡፡ ወይም ሌላኛው አማራጭ መንገድ የሚሆነው ፣ የላኪው ባንክ፣ ላኪው ሰነዶቹን ባቀረበበት ወቅት ክፍያውን ወዲያው ሳይከፍለው አቆይቶ ፣ ገንዘቡ ከገዢ ባንክ ገቢ መደረጉን ካረጋገጠ በኋላ ሊያስተላለፍለት ይችላል /Outward Bills for Collection (ODBC)፡፡
የገዢ ባንክም ሰነዶቹ ሲደርሱት፣ መስፈርቶችና ሁኔታዎች መሟላታቸውን ካረጋገጠ በኋላ ሰነዶቹን ለገዢ በማስተላለፍ፣ የሽያጩን ክፍያ በውጭ ምንዛሬ ለላኪ ባንክ እንዲከፈል ያደርጋል፡፡ አዚህ ጋር ገዥው ሂደቱን ያካሄደው የብድር ፋሲቲ ተመቻችቶለት ከነበረ፣ ሰነዱን ለመረከብ ብድሩን እንዲሁም የምንዛሬ ተመን ልዩነቱን በዚህ ወቅት አስቀድሞ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ በዚህም ሂደቱ ፍጻሜ ያገኛል ማለት ነው፡፡
ይህ ጠቅለል ያለ እንዲሁም አንዳንድ ነጥቦች በአጭሩ የተቀመጡ እንደመሆኑ በቀጣይ ሌሎች መሠረታዊ እንዲሁም ከላይ የተጠቀሱትን የሚያብራሩ ፅሁፎችን እናደርሳችኋለን፡፡
በአለማየሁ ስሜነህ
Leave a Reply