በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ (Money Laundering)

በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ (Money Laundering)

እንደ የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት በዓለማችን  ከ800 ቢሊዮን እስከ 2 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገንዘብ በሕገ ወጥ መንገድ በአንድ ዓመት ውስጥ ይዘዋወራል፡፡ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሽያጭ፣ ኮንትሮባንድ፣ የተደራጁ ወንጀሎች ተግባራት፣ ዕፅ አዘዋዋሪዎች፣ አሸባሪዎችና ሙሰኛ ፖለቲከኞች የፋይናንስ ወጪያቸውን ለመሸፈን ይጠቀሙበታል። እነዚህ ድርጊቶች ከፍተኛ ትርፍ በሚያስገኙበት ጊዜ፣ ተሳታፊዎች ገንዘቡን የሚቆጣጠሩበት መንገድ መፈለግ አለባቸው። ይኽን የሚያደርጉት ምንጮቹን በመደበቅ፣ ቅርጻቸውን በመቀየርና ትኩረትን መሳብ በማይችሉበት ቦታ በማዛወር ነው። ታዲያ በዚህ መንገድ የተከማቸው ገንዘብ ሊታወቅ ስለሚችል፤ ሕጋዊ ገንዘብ ሆኖ እንዲታይ “ሕጋዊ በሚመስል መልኩ” ያሸሻሉ፡፡ አጠቃላይ ይኽ ሒደት ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር (Money Laundering) በመባል ይታወቃል፡፡

በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ በተለምዶ ሦስት መሠረታዊ ሒደትን ይከተላል። የመጀመሪያው ምደባ (Placement) የሚባለው ሲሆን፤ በዚህ ሒደት በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘቡ ወደ ፋይናንሺያል ሥርዐቱ የሚገባበት ነው። በተለያዩ የሒሳብ መዝገቦች በመመዝገብ የገንዘቡ ምንጭ ይደበቃል። የገንዘቡ ምንጭ በተሳካ ሁኔታ ከተደበቀ በኋላ ገንዘቡን በማውጣት መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ የሚችሉበት ስልት ነው፡፡

በኹለተኛው ደረጃ በጣም የተለመደው ዘዴ፤ በጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሠረተ ንግድ ማካሔድ (Cash-Based Business) ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት አብዛኛው ሕገ ወጥ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ሰዎች የትላልቅ ድርጅቶች ባለቤት ናቸው። ከድርጅቱ የሚገኘውን ሕጋዊ ትርፍ በሕገ ወጥ ከሚገኘው ገንዘብ ጋር ይዋሐዳል፤ ምንጩን ሳይታወቅ ይደብቃል ማለት ነው። 

የመጨረሻው ሒደት ደግሞ ቴክኒክ ማዋቀር (Structuring) ይባላል፤ ይኽም ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ገንዘቦች በትንሽ መጠን የመከፋፈል በበርካታ መለያዎች ላይ የማሰራጨት ተግባር ነው። በተለያዩ አነስተኛ ዘርፎች ላይ ገንዘቡን በማዋል ምንጩ መደበቅ የሚቻልበት ሒደት ነው፡፡

በእነዚህ መንገዶች ሕጋዊ የሚመስሉ ሕገ ወጥ ገንዘቦችን ከደበቁ በኋላ፤ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ጥሬ ገንዘቦች ግልጽ ወደ ሆኑ ትናንሽ ገንዘቦች በመከፋፈል በቀጥታ ወደ ባንክ ሒሳብ ገቢ በማድረግ ወይም ተከታታይ የገንዘብ ሰነዶችን (ቼኮችን፣ የገንዘብ ማዘዣዎችን፣ ወዘተ) በመግዛት፤ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ የሪል እስቴት፣ የኢንቨስትመንትና የፋይናንስ አገልግሎት ድርጅቶች ያንቀሳቅሳሉ፤ ወደ ውጭ ሀገራት ያሸሻሉ። ወንጀለኞችም በሕገ ወጥ መንገድ የተሰበሰበውን ገንዘብ ከሕጋዊ አካውንቶች አውጥተው ሽብርተኝነትን፣ የተደራጁ ወንጀሎችን፣ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የመሳሰሉ ተግባራትን በገንዘብ መደገፍ ላይ ሊያውሉት ይችላሉ።

ባንኮች ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እንዴት ይከላለካሉ?

ባንክ በታማኝነት፣ በከፍተኛ ሕግ ጥበቃ፣ በሞያና ሥነ ምግባር የሚቋቋሙ በመሆናቸው ለአንድ አገር ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። ሆኖም፤ ሕገ ወጥ ገንዘብ በቀላሉ በእነዚህ ተቋማት በኩል ማስተናገድ የሚቻል ከሆነ የፋይናንስ ተቋም ታማኝነት በመጉዳት አደጋ ላይ ይጥላሉ፤ በሕጋዊ የፋይናንስ ግብይቶች ላይ ብክለት ያስከትላሉ፤ የዓለም አቀፍ የካፒታል ፍሰቶችና የምንዛሪ ዋጋ መጨመርን ሊያከትሉ ይችላሉ። የአንድ አገር የንግድና የፋይናንስ ዘርፎች በተደራጁ ወንጀሎች ተፅዕኖ ሥር ናቸው ተብሎ በሚታሰብበት ጊዜ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል። ስለዚህ ባንኮች በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን የሚከላከል (Anti-Money Laundering-AML) ሥርዐት መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡

AML ወንጀለኞች ሕገ ወጥ ገንዘቦችን ወደ ሕጋዊ ገንዘብ እንዳይቀይሩት የሚከለክል ደንብ፣ ሕግና አሠራር ነው። ይኽም ባንኮች የገንዘብ ወንጀሎችን እንዲቋቋሙ ይረዳል፤ የደንበኞችን መረጃ እንዲሰበስቡ፣ ግብይቶቻቸውን እንዲቆጣጠሩና እንዲያጣሩ፣ እንዲሁም አጠራጣሪ ድርጊቶችን ለፋይናንስ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት እንዲያሳውቁ ይረዳል።

ባንኮች በፋይናንስ መስክ ውስጥ ካሉ ትላልቅ ተቋማት መካከል ናቸው፡፡ በዓለም ዙሪያ ያሉ ባንኮች ቀኑን ሙሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግብይቶችን ስለሚያስተናግዱ፣ እነዚህ ተቋማት ለሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር ወንጀሎች ከፍተኛ ተጋላጭ ናቸው። በመሆኑም ባንኮች በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን የሚከላከል (Anti-Money Laundering-AML) ሥርዐት መሠረት በሚከተሉት መንገዶች መካከል ይችላሉ፡፡

  • ደንበኞቻቸውን በማወቅ፤ Know Your Customer (KYC)

ይኽ አሰራር ደንበኞች የባንክ አካውንት ሲከፍቱ ማንነቱን መለየትና ማረጋገጥን ያመለክታል። KYC ለባንኮች አስገዳጅና በፀረ-ገንዘብ ማጭበርበር ፕሮግራም ውስጥ የመጀመሪያው ወሳኝ እርምጃ ነው። በዚህ አሠራር ባንኮች የደንበኞችን መታወቂያ በመሰብሰብ ትክክለኛነቱን ያረጋግጣሉ። በሒደቱም የመታወቂያ ሰነድ ማረጋገጫ፣ የገጽ ማረጋገጫና የአድራሻ ማረጋገጫ (ሒሳቦች ወይም የባንክ መግለጫዎች) በመጠቀም ያከናውናሉ።

  • የደንበኛውን እንቅስቃሴ የስጋት ደረጃ መለየት፤ Customer Due Diligence (CDD)

ባንኮች የደንበኛ የስጋት ደረጃ መለየት የሚባል የቁጥጥር ሒደት ይተገብራሉ፤ በዚህም የደንበኛውን ጠቃሚ መረጃ የሚሰበሰብበትና የገንዘብ ማጭበርበር አደጋን (terrorist financing risk ጨምሮ) የሚገመግሙበት ነው። የCDD አሠራሮች ከአገር አገር ቢለያዩም፣ ዋና ዓላማቸው አደጋዎችን መለየት ነው። ከKYC ቁጥጥር በኋላ ባንኮች ለአዲሶቹ ደንበኞቻቸው የአደጋ ግምገማን ይተገብራሉ። የደንበኛው መረጃ በመንግሥት መዝገቦች ላይ ይጣራሉ። በነዚህ ዝርዝሮች ውስጥ የተካተቱት ሰዎች በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና በአሸባሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ከፍተኛ ስጋት አላቸው ማለት ነው። 

  • የደንበኛና የግብይት ማጣሪያ፤ Customer and Transaction Screening

ባንኮች ሰፊ የደንበኛ ፖርትፎሊዮ አላቸው፡፡ በዚህም የደንበኞች ተቀማጭ ገንዘብና ሌሎች ግብይቶች (የገንዘብ ማጭበርበር እቅድ አካል አለመሆናቸውን) መከታተል፤ በገንዘብ ዝውውር ላይ የተሳተፉ ሰዎችን የመቆጣጠር፤ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ከየት እንደመጣ ማረጋገጥ አለባቸው። 

  • አጠራጣሪ እንቅስቃሴ ሪፖርት ማድረግ፤ Suspicious Activity Reporting

ከላይ በተጠቀሱት ሦስት መንገዶች ተፈትሸው የሚታዩ አጣራጣሪ እንቅስቃሴዎችን በገንዘብ ዝውውር ምርመራዎች ላይ ለሚሠሩ ሕግ አስከባሪ አካላት ሪፖርት በማድረግ የሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውርን መከላከል ይቻላል ማለት ነው፡፡

ባንካችን አቢሲንያ በባንክ አሠራር ሒደት ውስጥ ያለውን ሕጋዊ ሥርዐት በመከተልና ደንበኞቹን ከማንኛውም አደጋ ለመከላከል የሚያችል አሠራር በመዘርጋት፤ በትጋት፣ በታማኝነት በአዳዲስና በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ቀልጣፋ፣ ምቹና አስተማማጭ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

አቢሲንያ የሁሉም ምርጫ!

አሰናኝ ምኒልክ ብርሃኑ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button