ባንካችን እጅግ በተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ስም ቅርንጫፍ ከፈተ!

ባንካችን እጅግ በተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ስም ቅርንጫፍ ከፈተ!

አዳዲስ ቅርንጫፎችን በአገር ባለውለታዎች ስም እየሰየመ የሚከፍተው ባንካችን አቢሲንያ፤ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ዕንቊዎች በመጀመሪያ ረድፍ ላይ በተቀመጡትና ስማቸውን በወርቅ ቀለም ባጻፉት ታላቁ የኪነ ጥበብ ሊቅ፣ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈ ወርቅ ተክሌ ስም ቅርንጫፉን ከፍቶ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

አርቲስት አፈ ወርቅ ተክሌ በአንኮበር ከተማ፣ ከአቶ ተክሌ ማሞና ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ ጥቅምት 13 ቀን፣ 1925 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ ዘመኑ ፋሺሽት ጣልያን አገራችንን በግፍ የወረረበት ዘመን በመኾኑ፣ አፈ ወርቅ በጨቅላ እድሜያቸው በሰው፣ በንብረትና ባህል ላይ የደረሰው ጥፋት በአእምሮአቸው ታትሞ ቀረ፡፡ ለዛም ይመስላል፤ በ1940 ዓ.ም. ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ለንደን ተጉዘው፣ የሥዕልን ጥበብ ተምረው ከተመለሱ በኋላ፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍላት እየተዘዋወሩ ታሪክን፣ የብሔረሰቦችን ባህልና ወግ ሲያጠኑ የከረሙት፡፡

በ1944 በሃያ ሁለት ዓመታቸው የመጀመሪያ የኾነው የሥዕል ዐውደ ርእይ በዐዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አቀረቡ፡፡ ከዐውደ ርእይ ባገኙት ገቢ፣ ወደተለያዩ የአውሮፓ አገራት በመዘዋወር የሥዕል ጥበብን ቀሰሙ፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትን አጠኑ፡፡ ሎሬት በኢትዮጵያ የመሥታወት ሥዕልን (Stained Glass Art) ያስተዋወቁ ቀዳሚው የጥበብ ሰው ናቸው፡፡ በዚህ ጥበብ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቤተ ክርስቲያንን መስኮቶች በመሥታወት ሥዕላት አስጊጠዋል፡፡ በሐረር ከተማ የዐፄ ኀይለ ሥላሴ አባት የራስ መኮንን ሐውልትን ገንብተዋል፡፡

ሥራዎቻቸው በአገር ውስጥና በዓለም ዐቀፍ እጅግ ዝናን ያተረፉ በመኾናቸው በርካታ ሽልማቶችን አስገኝተውላቸዋል፡፡ በ1971 ዓ.ም. የአልጀርስ የጥበብ ፌስቲቫል የወርቅ ሽልማት፤ በፈረንሳይ በተደረገው የሥዕል ውድድር አንደኛ በመውጣት የኖቤል የሎሬት ክብር መዓርግ በማግኘት ኢትዮጵያን አስጠርተዋል፡፡ በ2000 ዓ.ም. የዓለም ሎሬትነት ክብርን በዋሽንግተን ዲሲ በተደረው 27ኛው የአሜሪካ ባዬግራፊካል ኢንስቲትዩት ዓለም ዐቀፍ ጉባዔ ላይ ተቀዳጅተዋል፤ በ2004 ዓ.ም. በአየርላንድ ለጥበብ ዕድገት ለዓለም ላበረከቱት አስተዋጽዖ “የዳቬንቺ አልማዝ ሽልማት” እና “የጀግና ክብር ኒሻን” ተበርክቶላቸው፡፡

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈ ወርቅ ተክሌ በተወለዱ በ79 ዓመታቸው ሚያዝያ 2 ቀን፣ 2004 ዓ.ም. በሥጋ ሞት ቢለዩንም፤ እነኾ በራሳቸው ቀለምና በሀገርኛ ሥራዎቻቸው በዓለም መድረክ ላይ የኢትዮጵያን ስም ከፍ በማድረጋቸው፣ ለእኚህ የአገር ዋልታ ባንካችን አቢሲንያ ዐዲስ የከፈተውን ቅርንጫፍ በስማቸው ሰይሞ ዘክሯል፡፡

ባንካችን ብዙ መሰናክሎች ሳይበግራቸው አገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ የሥራ መስኮች ማለትም በመንግሥት አስተዳደር፣ አገርን በመጠበቅ፣ በታሪካዊ ኩነቶች፣ ቅርስ በማሰባሰብ፣ በስፖርት፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በቴአትር፣ ሙዚቃ፣ ፋይናንስና አገልገሎት፣ በበጎ አድራጎት ሥራዎች፣ በማስታወቂያ ሞያ፣ በንግድ ሥራና በመሳሰሉት ዘርፎች ስሟን ከፍ ላደረጉ ባለውለታዎች በስማቸው ቅርንጫፎችን በመሰየም እየዘከራቸው ይገኛል፡፡ ይኽም ለአገራችን ዘመን አይሽሬ አበርክቶ ያደረጉ ባለውለታዎችን ስማቸውንና መልካም ተግባራቸውን በመዘከር ለቀጣዩ ትውልድ ለማሳወቅና አርዓያ እንዲኾን በማመን ጭምር ነው፡፡

አቢሲንያ የሁሉም ምርጫ!

ምኒልክ ብርሃኑ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Call Now Button